አምና ብዙ የተባለለትና በተማሪዎች ውጤት ዝቅተኛነት ከሰው አፍ ውስጥ የገባው የአስራ ሁለተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና እንሆ ዘንድሮም ለተማሪዎች ሊሰጥ ቀን ተቆጥሮለታል። አምና በዚህ ሀገር አቀፍ ፈተና 3 ከመቶ ብቻ የሚሆኑ ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተናውን እንዳለፉ የሚታወስ ነው። በዚህም ውጤት አንገቱን ያልደፋ ወላጅ፣ መምህርና የሚመለከታቸው የትምህርት አመራሮች የሉም። በዚህ አስደንጋጭ ውጤት ያልተከፋ የለም። ለዛም ይመስላል የአምናው ዘንድሮ እንዳይደገም በተማሪዎች፣ ወላጆች፣ መምህራንና የትምህርት አመራሮች ለአስራ ሁለተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ትኩረት ተሰጥቶ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ሲከናወን የቆየው።
የዘንድሮው የአስራ ሁለተኛ ክፍል ፈተና የሚሰጥባቸው ቀናት በትምህርት ሚኒስቴር አማካኝነት ይፋ ተደርጓል። ምን ያህል የተፈጥሮና ማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ፈተናውን እንደሚወስዱም ተገልጿል። ፈተናው ልክ እንደአምናው በወረቀትና በኦንላይን እንደሚሰጥም ታውቋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በትምህርት ቤቶች፣ በወረዳ፣ ክፍለከተማና ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤቶች ብሎም በትምህርት ሚኒስቴርና በትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት በኩል የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ታዲያ ከትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎቱም ሆነ ከሌሎች የትምህርቱን ዘርፍ ከሚመሩት አካላት የቅድመ ዝግጅት ሥራ ባልተናነሰ መልኩ የተማሪዎች ዝግጅትም ወሳኝ መሆኑ ይነገራል። ምክንያቱም በብሔራዊ ፈተና የተሻለ ውጤት እንዲመጣ የተማሪው ቅድመ ዝግጅት ከሁሉ በላይ ድርሻው የጎላ በመሆኑ ነው።
ተማሪ ኤርሚያስ ኪዳኔ የፊት አውራሪ አባይነህ መተኪያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአስራ ሁለተኛ ክፍል ተማሪ ነው። የዘንድሮውን ፈተና ለመውሰድ ቢቂ ዝግጅት ማድረጉን ይገልጻል። ፈተናው በኦንላይንም ይሁን በወረቀት መሰጠቱ ለእርሱ ምንም ለውጥ እንደማያመጣ ያምናል። በቂ ዝግጅት ማድረጉን እና ባሉት ጥቂት ቀናትም ዝግጅት እያደረገ እንደሚቀጥል ይናገራል። ተፈታኝ ተማሪዎች እንወድቃለን የሚል ፍርሀታቸውን አስወግደው በቂ ጥናት በማድረግ ያለማንም ድጋፍ በራሳቸው ጥረት ማለፍ እንደሚቻላቸውም ያስረዳል።
ሌላኛዋ ተማሪ ሀሴት በላቸው ትባላለች። የተፈጥሮ ሳይንስ አስራ ሁለተኛ ክፍል ተማሪ ናት። በከንባታ ጠንባሮ ዞን ‹‹አንገጫ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት›› ነው የምትማረው።እርሷ እንደምትገልጸው ፤ እርሷም ሆነች ሌሎች ጓደኞቿ የፈተናው ቀን እስከሚቃረብ በቂ ዝግጅት ማድጋቸውን ቀጥለውበታል። የአስራ ሁለተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በዩኒቨረስቲዎች መሰጠት ከተጀመረ ጀምሮ ከዚህ በፊት ከነበሩ ተፈታኞች በርካታ ልምዶች ቀስመንበታል የምትለው ተማሪ ሀሴት፤ ተፈታኝ ተማሪዎች በርትተው እንዲያጠኑ ልምድ ይሰጣቸዋል ትላለች። ፈተናው በኦንላይንም ተሰጠ፤ በወረቀት ምንም የሚፈይደው ነገር የለም።ዋናው ነገር በቂ ዝግጅት ማድረግ ብቻ ነው የሚያስፈልገው የምትለው ተፈታኟ፤ መምህራን ለተማሪዎቻቸው ምዕራፎችን በመከለስ ጥሩ ውጤት እንዲያመጡ ማገዝ እንዳለባቸው ትጠይቃለች።
የዘንድሮ የአስራ ሁለተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የሚሰጥባቸው ቀናት በትምህርት ሚኒስቴር ይፋ ተደርጓል። የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ፈተናውን ከሐምሌ 3 እስከ ሐምሌ 5 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚወስዱ ተረጋግጧል። ለተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ደግሞ ከሐምሌ 9 እስከ ሐምሌ 11 ቀን 2016 ዓ.ም ፈተናው ይሰጣል። የ2016ቱ የአስራ ሁለተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከዚህ በፊት በተለየ መልኩ በኦን ላይን እና በወረቀት ይሰጣል። ከዚህ ጋር ተያይዞም በወረቀት የሚፈተኑ የማህበራዊ ሳይንስ ተፈታኞች ወደ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገቡበት ቀን ከሰኔ 30 እስከ ሐምሌ 01 ቀን 2016 ዓ.ም መሆኑ ታውቋል። የተፈጥሮ ሳይንስ ተፈታኞች ደግሞ ሐምሌ 6 እና ሐምሌ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡበት ቀን መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር አረጋግጧል።
የዘንድሮውን የአስራ ሁለተኛ ክፍል ፈተና በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመስጠት ጥቂት ቀናቶች ብቻ ቀርተውታል። ይህንን ተከትሎም ፈተናው በስኬት እንዲጠናቀቅ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በመንግሥት በኩል ብቻ ሳይሆን በተማሪዎች በኩልም እየተከናወኑ ይገኛሉ።
አቶ ተፈራ ፈይሳ የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ናቸው። እርሳቸው እንደሚገልጹት፤ አሁን ላይ በዋናነት እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ፈተናውን ለመስጠት የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ናቸው። ከቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መካከል የፈተና ዝግጅት አንዱ ሲሆን፤ ይህም ዝግጅት ተጠናቋል። ሁለተኛው ቅድመ ዝግጅት ድግሞ የተማሪዎች ምዘገባ ሲሆን ይህም በጥሩ ሁኔታ ተጠናቋል። ሌላው ሥራ ተፈታኞችን በሚፈተኑበት የዩኒቨርስቲ ማዕከል መመደብ ሲሆን ምደባው ተጠናቆ ለዩኒቨርስቲዎችና ለክልሎች ተገልጿል።
የአስፈጻሚዎች ምልመላ ማለትም የማዕከል ኃላፊ፣ አስተባባሪ፣ ፈታኝ እና ሌሎችንም የመመልመል ስራ በርካታ ሰዎች ይሳተፉበታል። አስፈጻሚ አካላት ቁጥራቸውን በተማሪዎች ልክ ተለይቶ ክልሎች እና ዩኒቨርስቲዎች ምልመላ እንዲያከናውኑ ተነግሯቸዋል። የፈተናውን ህትመት በተመለከተም በአጭር ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃሉ። የዘንድሮው ፈተና የሚሰጠው በወረቀት እና በኦን ላይን እንደመሆኑ ከዚህ በፊት ከነበረው ሥርዓት ለየት ያደርገዋል። በሁለቱም አማራጮች ፈተናውን ለመስጠት የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። በተመረጡ ከተሞች እና ምቹ ሁኔታዎች ባሉባቸው አካባቢዎች ሁሉ ተማሪዎች ፈተናውን በኦንላይን እንዲወስዱ ለማድረግ ዝግጅት ተደርጓል።
እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ መረጃው ተጠናቆ ሲመጣ ምን ያህል ተማሪዎች በኦንላይን ፣ ምን ያህሎቹ ደግሞ ፈተናውን በወረቀት ይወስዳሉ የሚለው ዝርዝር ጉዳይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይገለጻል። ከዚህ ጋር ተያይዞም ሁለቱንም አሠራሮች በተናጠል የሚያስፈጽም ትልቅ አደረጃጀት ከመኖሩ ባሻገር እንዴት ተቀናጅተው ይሰጡ? የሚለውን የሚመልስ አደረጃጀት ተዘጋጅቷል።
አቶ ተፈራ እንደሚገልፁት የ2016 ዓ.ም የአስራ ሁለተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን 369 ሺ 60 የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች፣ 332 ሺ 229 የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች በድምሩ 694 ሺ 534 ተማሪዎች ይወስዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከፈተናው ጋር በተያያዘም ‹‹የጸጥታ ችግር ያጋጥም ይሆን?›› የሚል ስጋት እና ጥያቄ ከተለያዩ ሰዎች ሊነሳ ይችላል። ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ የዘንድሮውን ፈተና ለመውሰድ የሚከለክል አንዳች ነገር የለም። እንዲያም ሆኖ ግን ከዚህ ቀደም በጸጥታ ችግር ምክንያት በጥቅምት ወር ላይ ትምህርት ያልጀመሩ ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን ተከትሎ ተማሪዎች መማር ያለባቸውን ትምህርት ካጠናቀቁ በኋላ በመጪው መስከረም ፈተናውን እንዲወስዱ ይደረጋል። በሁለተኛ ዙር ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች ቁጥርም ስድስት ሺ 759 ነው።
በወረቀት የሚሰጠው ፈተና ሁሉ በዩኒቨርሲቲ የሚሰጥ ነው። የዘንደሮውን ፈተና ከሚወስዱት ውስጥ በወረቀት ፈተናውን የሚወስዱ ተፈታኞች ቁጥር ብልጫ አለው። በኦን ላይን የሚፈተኑ ተማሪዎች ቁጥር በየትምህርት ቤቶቻቸውና በዩኒቨርሲቲ የሚፈተኑትን በሚመለከት ወደፊት በዝርዝር ይገለጻል። የዘንድሮ የአስራ ሁለተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ለመስጠት 122 የፈተና ማዕከላት ተዘጋጅተዋል። ለማዕከላቱ የሚያስፈልጉ ሰዎችም እየተዘጋጁ ነው።
ሌላው ለፈተናው ከሚደረጉ ቅድመ ዝግጅቶች በተጨማሪ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተደረገው የፈተናው ሥርዓት መቀየርን ተከትሎ የለወጣቸው በርካታ ነገሮች መኖራቸው ይነሳል። ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ከስርቆት ነፃ የሆነ ፣ ተቀባይነት እና ተአማኒት ያለው ፈተና መስጠት ስለሆነ ዋናው ጉዳይ ይህን ለማድረግ ሲባል ፈተናውን በዩኒቨርሲቲዎች መስጠት አስፈልጓል። ‹‹ለፈተናው ፈተና የነበረው ኩረጃ እና ሥርቆት ነው ያሉት አቶ ተፈራ፤ ይህንንም ባለፉት ሁለት ዓመታት ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ተችሏል ብለዋል። ይህን ሂደት መከተል አንድ ስኬት ነው። ዘንድሮም ቢሆን በዚህ አግባብ ይፈጸማል የሚል ዕምነት አለ።
ምንም እንኳን ተማሪዎችን ከቦታ ቦታ ለማጓጓዝ ሲባል የሚወጣው ገንዘብ ከፍተኛ መሆን ግልጽ ቢሆንም ዘላቂው መፍትሔ ፈተናውን ወደ ኦን ላይን መቀየር ነው። ወደ ኦንላይ መቀየሩ ሰዎችን ከቦታ ቦታ ማንቀሳቀስ ግዴታ ካለመሆኑ በተጨማሪ ከፍተኛ የሆነ የበጀት ወጪ ላይጠይቅ ይችላል።
ሌላው የፈተና ወረቀቶችን ለማመላስም ይሁን ተማሪዎች ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ የጸጥታ ችግር እንዳይገጥማቸው ከጸጥታ አካላት ጋር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተሠርተዋል። ከፈተና ዝግጅቱ ጀምሮ ተማሪዎች ፈተና እስከሚወስዱበት ድረስ ሥራው ከጸጥታ ኃይሎች አይነጠልም። ፈተናው ታርሞ ውጤት እስከሚገለጽ ድረስም ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከክልል የጸጥታ አካላት ፣ የትራንስፖርት አመራር እና ሌሎችም ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲ ላይ በሚኖራቸው ቆይታ በቂ ጥበቃ ይደርግላቸዋል።
በአጠቃላይ በፌዴራሉ መንግሥት፣ በትምህርት ሚኒስቴር፣ በአገልግሎቱ እና በሌሎች ተቋማት በኩል በተቻለ መጠን የ2016 ዓ.ም የአስራ ሁለተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በተሳካ ሁኔታ፣ ከጥራት በሻገር በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለው እንዲሆን ለማስቻል ከፍተኛ ዝግጅት እየተደረገ ነው። ነገር ግን ይህ ውጤታማ የሚሆነው በየደረጃው ያለ የትምህርት አመራር፣ ወላጆች፣ ተፈታኝ ተማሪዎች እና የዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ትልቅ እገዛ ሲያደርግ እንደመሆኑ ሁሉም የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ እንፈልጋለን ብለዋል አቶ ተፈራ።
አቶ ተፈራ እንደሚሉት፤ ፈተናው በሁሉም ክልሎች ይሰጣል። የዚህ ፈተና ዋናው ግቡ ብቃት ያለው ዜጋ መፍጠር ነው። ብቃት ያለው ዜጋ ለሀገር ምሰሶ ነው። ስለዚህ ተማሪዎች በቁርጠኝት በራሳቸው በመተማመን፣ ኩረጃን ተጸይፈው፣ ፈተናውን ከሚረብሹ ነገሮች ራሳቸውን ቆጥበው በተረጋጋ እና በራስ መተማመን በተሞላበት መንፈስ ፈተናዎችን መውሰድ ይኖርባቸዋል።
እየሩስ ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም