ፓስፖርት በጸሎት!

አዲስ ፓስፖርት ለማውጣት ከ6 ወራት በፊት አሰራሩ በሚፈቅደው መሰረት በኦንላይን ተመዘገብኩ። ግንቦት 7 ቀን 2016 ዓ.ም ከቀኑ 5፡00 እስከ 6፡00 ባለው በኤጄንሲው ተገኝቼ አሻራና ፎቶ መስጠት እንዳለብኝ የተመዘገብኩበት ሰነድ ነገረኝ። የተቀጠርኩበትን ቀን ስጠብቅ ቆይቼ በዋዜማው (ግንቦት 6 ማለት ነው) ‹‹ነገ ኢሚግሬሽን አሻራ ልሰጥ እሄዳለሁ›› ያልኩት አንድ ባልደረባዬ ‹‹ሌሊት 11፡00 ወይም 12፡00 እዚያው መድረስ አለብህ›› አለኝ። እኔም የሀገሬን ነባራዊ ሁኔታ ባለማወቅ ‹‹ እንደ ድሮው መሰለህ እንዴ? አሁን እኮ ሁሉ ነገር በቴክኖሎጂ ነው፤ 5፡00 ላይ ነው የተቀጠርኩ›› ስለው በረጅሙ ከሳቀብኝ በኋላ ‹‹በል እንግዲያውስ ተገትረህ ዋል! 12፡00 ደርሰህ ራሱ ከደረሰህ ዕድለኛ ነህ!›› አለኝ።

መወዛገብ ጀመርኩ። ከ5፡00 እስከ 6፡00 የቀጠሩኝ እንደሚቻል ቢያውቁ ነው። ከዚያ በፊት ብሄድ ‹‹ምን ትሰራለህ ባልተቀጠርክበት ሰዓት?›› ቢሉኝስ? እያልኩ ስወዛገብ ቆይቼ በኋላ ግን በአንድ ውሳኔ ፀናሁ። ቢያንስ በመደበኛው የሥራ መግቢያ ሰዓት (2፡30) መድረስ አለብኝ። ቢሮውን፣ መስኮት ቁጥሩን መፈለጉም ሥራ ነው፣ ካገኘሁት በኋላ ‹‹በተቀጠርክበት ሰዓት ብቻ ነው!›› ካሉኝ በአካባቢው በሚገኝ ካፌ እቆያለሁ በሚል ውሳኔ 2፡30 ከቦታው ደረስኩ።

ቢሮውንና መስኮቱን መፈለጉም ሥራ ነው የሚለው ውሳኔዬ በጣም ትክክል ነበር። ገና ከበሩ ላይ ነው ውጣ ውረዱ የጀመረኝ። ከዚህ በፊት በማውቀው በዋናው በር ልገባ ስል ጥበቃው ሌላ በር ጠቆመኝ። ወደ ጠቆመኝ በር ስሄድ መጀመሪያ ልገባበት የነበረውን በር ጠቆመኝ። ‹‹እሱ ነው ‹በዚህ ነው› ያለኝ›› አልኩት። የዚህኛው ጠባቂ ፌዴራል ፖሊስ ነው። ሳቅ እያለ ‹‹እሱ ራሱ ነው ሂድ›› አለኝ። ተመልሼ ሄጄ ‹‹ኧረ እሱም በዚህ ነው አለኝ›› አልኩት መጀመሪያ ልገባበት የነበረው በር ላይ ላለው ጥበቃ። ለምን እንደሆነ ሲጠይቀኝ መጀመሪያ የነገርኩትን ጉዳዬን ነው የነገርኩት። እንደገና ወደታች ሌላ መግቢያ ጠቆመኝ። ልብ ሳይለኝ ነበር የነገረኝ አልኩና ወደተባለው አቅጣጫ ሄድኩ።

አሁን የጠቆመኝ አቅጣጫ ትክክል መሆኑን ያረጋገጠልኝ ግን የአካባቢው ወከባና ግርግር ነበር። ‹‹ለፓስፖርት ቀጠሮ ነው? ኮፒ ነው? ፕሪንት ነው?….›› የሚሉ ጥያቄዎችን የሚጠይቁ ብዙ ወጣቶች ይከታተሉኛል። ይሄ ነገር ቀድሜ መምጣቴ ትክክል ነው እያልኩ ወደ በሩ ተጠጋሁ። በሩ ላይ ያለው ተቆጣጣሪ ሰነዶቼን ከመረመረ በኋላ እንድገባ ፈቀደልኝ።

ከቀጠሮው ሰዓት ቀድሜ በመምጣቴ መደሰት የጀመርኩት ሰው በማርፈዴ መፀፀት ጀመርኩ። የሰልፉ ነገር ‹‹ረጅም ነው›› በሚል የሚገለጽ አይደለም፤ ምክንያቱም ርዝመቱን ማየት አይቻልም። ትልቅ የገጠር የገበያ ቦታ ታውቃላችሁ? ልክ የእህል ተራ፣ የፍየል ተራ፣ የከብት ተራ፣ የልብስ ተራ፣ የአትክልትና ፍርፍራ ተራ… እየተባለ እንደሚመደበው ማለት ነው። በአንደኛው ተራ ብቻ ብዙ ሕዝብ ያለበት ማለት ነው። ስገባ ልክ እንደዚያ ነው። መጨረሻውን ማግኘት አስቸጋሪ ነው። የጠየኩት ሁሉ ‹‹ወደዚያ ነው!›› እያሉ አቅጣጫውን ብቻ ነው የሚናገሩ እንጂ መጨረሻውን ማየት አይቻልም። አንድ ቦታ ክብ የሰሩ፣ አንድ ቦታ የተበታተኑ፣ አንድ ቦታ በየእንጨቱ ላይ የተቀመጡ፣ አንድ ቦታ አግዳሚ ወንበር ላይ የተቀመጡ፣ አንድ ቦታ የመንገዱ ጠርዝ ላይ የተቀመጡ… ናቸው የሚታዩት። መቀመጫ ወይም መቆሚያ ለማግኘት ሲባል ምቹ ባልሆኑ ቦታዎች ላይ ክፍተት አለ። ይሄ ነው መጨረሻው፣ ከኋላ ያለው ሌላ ሰልፍ (የሌላ ጉዳይ) ሊሆን ይችላል ብሎ በማሰብ በክፍተቱ ውስጥ ሊገባ ያሰበ ሰው ‹‹ከኋላ ነው›› የሚል የሰልፈኞች ትዕዛዝ ይሰጠዋል።

እንዲህ እንዲህ ሳቆራርጥ ቆይቼ የመጨረሻ ነው የሚባለው ላይ ደረስኩ። ከኋላዬም ከፊቴም ያሉ ሰዎች መረጃ ጠያቂዎች ናቸው። አስቂኙ ነገር ከ20 ደቂቃ በላይ ተሰልፈው ቆይተው ‹‹የፓስፖርት አሻራ ለመስጠት ነው አይደል?›› ብለው ከኋላቸው ወይም ከፊታቸው ያለውን ሰው የሚጠይቁ አሉ። ጠይቀው የሚያረጋግጡበት መንገድ አጥተው በግምት ነበር የቆሙት ማለት ነው። ፍርሃታቸው ትክክል ነው። ያ እንደ ጉሊት ገበያ የተቆራረጠ ሰልፍ ምኑም አያስተማምንም። ምናልባትም የሌላ ጉዳይ ላይ የተሰለፉ ሊመስላቸው ይችላል። አንደኛው ቁራጭ ላይ ስህተት ቢያጋጥም ብዙ ሰው ይሳሳታል ማለት ነው።

ከግማሽ ሰዓት መቆም በኋላ ትንሽ አንድ አራት እርምጃ ሰልፉ ፈቀቅ አለ። እንዲህ እንዲህ እያለ ጠዋት 2፡40 አካባቢ የተሰለፍኩ 5፡00 አካባቢ ጣሪያ እና አግዳሚ ወንበር ያለው ክፍል ማየት ቻልኩ። ምሳ ሰዓት (6፡00) ሰአት ላይ ከዚህ ክፍል ውስጥ መግባት ቻልኩ። በአግዳሚ ወንበሮቹ ላይ ዝግዛግ የሚሰራ ሰልፍ አለ። አንድ ዙር ሰዎች ሲሄዱ መጠጋጋት ይኖራል። ዝግዛግ ከመሆኑ የተነሳ ቦታ ስንቀይር ከግራዬ የነበረ ሰው ከቀኜ ሊሆን ይችላል። እዚህ ቦታ ላይ ጎበዝ እና ፈጣን አስተባባሪዎች ስላሉ የተሻለ ቦታ ነው።

ምሳ ሰዓት ላይ ትርምስ ነገር ተፈጠረ። ከውጭ የሚመጡ ሰዎች የሰልፍ ክፍተት እየፈለጉ አጭበርብረው ለመግባት ይሞክራሉ። በዚህ ሁኔታ ለአስተባባሪዎች በጣም አዘንኩ። አደገኛ ባህሪ ያላቸውን እንስሳት መጠበቅ ‹‹በስንት ጣዕሙ!›› ያሰኛል። ‹‹አይቻልም!›› ሲሏቸው አይሰሙም። ከተነቃባቸው በኋላ እንኳን ቢቻል ይቅርታ ጠይቆ፣ እሱን እንኳን ባይችሉና ቢያፍሩ ድምጽን አጥፍቶ ሹልክ ብለው መሄድ ሲገባቸው ጭራሽ ደረታቸውን ነፍተው የሚቆጡ እና የሚጣሉ አሉ። ባይሆን ሳያስነቁ መሞከር እንጂ ከተነቃ በኋላ ሰው እንዴት ካላጭበረበርኩ ብሎ ይጣላል?

ግርግሩን አረጋግቶ ትንሽ ፋታ ሲያገኝ አስተባባሪውን አንድ ጥያቄ ጠየቅኩት። ‹‹ለመሆኑ ይህ ችግር የተፈጠረው በሰው ብዛት ነው ወይስ በተቋሙ የአሰራር ችግር ነው?›› አልኩት። እንደነገረኝ ከሆነ፤ በቀን 1,500 ሰው ለፓስፖርት አሻራ ይሰጣል። የአሁኑ የሰው ብዛት ለእነርሱም አስገራሚ ሆኗል። ከዚህ በፊት እስከ 600 ሰው ነበር። አሁን ከእጥፍ በላይ ሆነ ማለት ነው። ስለዚህ አጋጣሚ ሆኖ እኔ የሄድኩበት ቀን እጅግ ከፍተኛ የሚባል ቁጥር እየተስተናገደ ያለበት ወቅት ነው። እንዲያውም ከዓመታት በፊት ፓስፖርት ያወጡ ሰዎችን ስጠይቅ አንድ ሰዓት የሞላ እንኳን አልቆዩም። አሁን ለምን ይህ ችግር ተፈጠረ? የፍላጎት መጨመር ነው ወይስ የአሰራሩ መጓተት? የሚለው ነገር ልብ ሊባል ይገባል።

በሰልፉ ላይ ያሉ ሰዎች በጣም ከመማረራቸው የተነሳ የየእምነታቸውን ስም እየጠሩ የሚማጸኑ ብዙ ናቸው። ወደ አሻራ መስጫው የተጠጉ ሰዎች የፈጣሪያቸውን ስም እየጠሩ ማመስገን ይጀምራሉ። አሻራ ሰጥተው ጨርሰው የሚወጡ ሰዎች የእምነታቸውን ስም እየጠሩ ያመሰግናሉ። ፓስፖርቱ እጃቸው የገባ ሰዎች ደግሞ በምን አይነት ደስታ ስሜታቸውን ሲገልጹ እንደነበር በማህበራዊ ገጾች አይተናል። ፓስፖርት በጸሎት ሆነ ማለት ነው።

ጠዋት 2፡40 የተሰለፍኩ፤ አሻራ ሰጥቼ የሰነድ ማረጋገጫ ተደርጎልኝ ከመጨረሻው ቢሮ ስወጣ ከቀኑ 9፡27 ነበር። ለሰባት ሰዓታት ያህል ተሰልፌያለሁ ማለት ነው። በሰልፉ ላይ የነበሩ የባንክና መሰል ነገር ሰራተኞች በመምሰል የማታለል ሙከራ የሚያደርጉትን በተመለከተ በሌላ የትዝብት ጽሑፍ እመለስበታለሁ!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ግንቦት 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You