“የበጎነት ተግባራት በበዓል ቀናት ብቻ ተወስነው ሊቀሩ አይገባም”አቶ ቢንያም በለጠ

አዲስ አበባ፦ የበጎነት ተግባራት በበዓል ቀናት ብቻ ተወስነው ሊቀሩ እንደማይገባ የመቄዶንያ የአእምሮ ህሙማንና አረጋውያን መርጃ ማዕከል መስራች አቶ ቢንያም በለጠ ገለፁ።

አቶ ቢንያም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብም የትንሳዔ በዓል እንኳን አደረሳችሁ መልዕክቱን አስተላልፈው፤ በበዓል ቀናት የሚስተዋሉ የመረዳዳት፣ የመተዛዘንና የመደጋገፍ ተግባራት መልካም ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።

የበጎነት ሥራዎችን ለመከወን ቀን እየጠበቁ ሳይሆን የሁልጊዜም ተግባር ሊሆን ይገባል ያሉት አቶ ቢንያም፤ የመረዳዳት ልምዱን ቋሚ አድርጎ መቀጠል እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

በሁሉም ኃይማኖቶች በበዓል ወቅት ትብብር ማድረግና አቅመ ደካሞችን መርዳት መልካም ቢሆንም ችግረኞች ግን ሁልጊዜም ስላሉ በዘላቂነት መደገፍ እንጂ የመልካምነት ተግባራት በዓመት ሁለትና ሶስት ቀናት ብቻ ተወስነው ሊቀሩ አይገባም ብለዋል።

በክርስትና እምነት አስተምህሮ መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ የሕይወት ዋጋን ሰጥቷልና የእምነቱ ተከታዮች ደግሞ ስለ መልካምነት የሚከፈል መስዋዕትነትን እለት እለት መክፈል ይገባቸዋል ሲሉ አቶ ቢንያም ተናግረዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ሆኖ ሰው መሆንን ሳይፀየፍና ሳይንቅ ወደ ምድር ወርዶ እስከ ሞት በደረሰ ፍቅር ለሰዎች መልካም ከሆነ የሰው ልጅ ደግሞ እርስ በርስ በመደጋገፍና በመረዳዳት አንዱ ለአንዱ ሊኖር እንደሚገባው አቶ ቢንያም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከበጎነት ርምጃዎች ዋነኛውና የመጀመሪያው ሰዎችን አለመጉዳት ነው ያሉት አቶ ቢንያም፤ በቀጣይም ከዚያ አልፎም ለሰው መኖር መቻልና ችግረኞች ቋሚ ድጋፍ እንዲኖራቸው መሥራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝቧል።

አቶ ቢንያም እንዳመላከቱት፤ በሀገሪቷ በተለያዩ ምክንያቶች በርካታ ሰዎች በየቤታቸው የተለያዩ ችግሮችን እያስተናገዱ ይገኛል። በበሽታ የተያዙ የአልጋ ቁራኛዎች፣ ጎዳና ላይ የተፈናቀሉ በቤተሰብ ደረጃ የሰው ፍቅርና መፅናናትን የሚሹ አሉ እነዚህን በየቀኑ መጠየቅና ማገዝ ያሻል ብለዋል። እንደ መቄዶንያ ያሉ የመርጃ ማዕከላትን መደገፍም ከመላው ሕዝብ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።

የበጎነት ሥራዎች ሰማያዊ ዋጋንም ጭምር የሚያሰጡ ናቸው ያሉት አቶ ቢንያም ያንን ምድራዊ ርካታንና ሰማያዊ ዋጋን ለማግኘት ሁልጊዜ በበጎነት መንገድ መበርታት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

አቶ ቢንያም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብም የትንሳዔ በዓል እንኳን አደረሳችሁ መልእክቱን በማስተላለፍ ለመቄዶንያ የድጋፍ ጥሪውንም አስተላልፏል።

ከአዲስ አበባ ውጪ 27 ቅርንጫፎች ያሉት መቄዶንያ የአዕምሮ ህሙማንና አረጋውያን መርጃ ማዕከልም ለበርካታ ተረጂዎቹ በየቀኑ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ወጪ የሚያደርግ በመሆኑ የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ትብብር የሚጠይቅ መሆኑንም አቶ ቢንያም ገልጿል።

ዳግማዊት ግርማ

አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You