በሚቀጥሉት ቀናት በአብዛኛዎቹ በልግ አብቃይ አካባቢዎች ዝናቡ ተጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፡- በሚቀጥሉት ስምንት ቀናት በአብዛኛዎቹ በልግ አብቃይ አካባቢዎች የበልግ ዝናብ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡ በሚቀጥሉት ቀናት የሚጠበቀው እርጥበት የመኸር ሰብሎችን ወቅቱን ጠብቆ ለመዝራት ምቹ ስለሚሆን አርሶ አደሮች አስፈላጊውን የግብዓት ዝግጅት ማድረግ እንዳለባቸው ተጠቁሟል፡፡

በሚቀጥሉት ስምንት ቀናት የበልግ ዝናብ በአብዛኛዎቹ በልግ አብቃይ አካባቢዎች በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ለኢፕድ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

በተለይም የምድር ወገብን አቋርጦ ወደ ኢትዮጵያ ከሚገባው እርጥበት አዘል የአየር ሁኔታ ጋር ተያይዞ የተሻለ የደመናና የዝናብ ሥርጭት በደቡባዊው አጋማሽ፣ በመካከለኛውና በምሥራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ቀጣይነት እንደሚኖራቸው ተጠቁሟል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘም በደቡብ፤ በደቡብ ምሥራቅ፣ በሰሜን ምሥራቅ፣ በምሥራቅ፣ በመካከለኛው፣ እንዲሁም በስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች የተሻለ ዝናብ የሚያገኙ ይሆናል፡፡ የበልግ አብቃይ አካባቢዎች በርካታ ቦታዎቻቸውን የሚሸፍን ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ተመላክቷል፡፡

በተጨማሪም በውሃ አካላትና በከባቢ አየር ውስጥ ከሚጠናከሩት የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ላይ በመነሳት በደቡብ ምሥራቅ፣ መካከለኛው፤ በምሥራቅና በሰሜን ምሥራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል የሚችል ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ አኃዛዊ የትንበያ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ከኦሮሚያ ክልል ሁሉም የሸዋ ዞኖች፣ አርሲና ምዕራብ አርሲ፣ ባሌና ምሥራቅ ባሌ፣ ጉጂና ምዕራብ ጉጂ፤ ቦረና፤ ምዕራብና ምሥራቅ ሐረርጌ፣ እንዲሁም ሐረሪ እና ድሬዳዋ፤ አዲስ አበባ፤ ከአማራ ክልል የሰሜንና የደቡብ ወሎ ዞኖች፣ የሰሜን ሸዋና የኦሮሚያ ልዩ ዞን፣ የአፋር ክልል ዞኖች፤ ከትግራይ ክልል የደቡብ፣ የደቡብ ምሥራቅ፣ ማዕከላዊ፤ የምሥራቅ ትግራይ ክልል ዞኖች፤ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፤ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፤ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፤ የሲዳማ ክልል ዞኖች፤ የሶማሌ ክልል ዞኖች ብዙ ቦታዎቻቸውን የሚያዳርስ የተስፋፋ ዝናብ እንደሚኖራቸው ተጠቅሷል፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች በአንዳንድ ስፍራዎቻቸው ላይም ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ተጠቅሷል፡፡

ከኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ፣ ምዕራብ ወለጋ፣ ቡኖ በደሌ፣ ጅማ፣ ኢሉባቦር፤ ከአማራ ክልል የደቡብ ጎንደር ዞን፣ የባሕርዳር ዙሪያ፣ የዋግኸምራ ዞኖች፣ የጋምቤላ ክልል ዞኖች፤ ከቤንሻንጉል ክልል የአሶሳ፣ የማአኮሞ ልዩ ወረዳ፤ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸው በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

በአፋር ክልል፣ በሐረር፣ በድሬዳዋ፣ ምሥራቅ ሸዋ፣ የሶማሌ ክልል ዞኖች፣ አዲስ አበባ እና በምሥራቅ አማራ አካባቢዎች ከሚኖረው ተደጋጋሚነት ያለው ከባድ መጠን ያለው ዝናብ በመነሳት ቅጽበታዊ ጎርፍ የሚያስከትል አቅም ስለሚኖረው ከወዲሁ አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ተመላክቷል፡፡

በሌላ በኩል በሚቀጥሉት ስምንት ቀናት የሚጠበቀው የመኸር ሰብሎችን ወቅቱን በጠበቀ ሁኔታ ለመዝራት አመቺ በመሆኑ አርሶአደሮች የሚገኘውን እርጥበት ለመጠቀም አስፈላጊውን የግብዓት ዝግጅት ሊያደርጉ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

የሚጠበቀው እርጥበት ቀደም ብለው ለተዘሩ የበልግ ሰብሎችና ለቋሚ ተክሎች የውሃ ፍላጎትን ለማሟላት፣ ለእንስሳት መኖና የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማሻሻል እንዲሁም ለኃይል ማመንጫነት የሚያገለግሉ ግድቦችን የውሃ መጠንም ለማሻሻል ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡

በተለይም በመደበኛ ሁኔታ ውሃ አጠር የሆኑ አካባቢዎች በማሳም ሆነ ከማሳ ውጪ የውሃ እቀባ ሥራዎችን በማከናወን በየመሐሉ ለሚከሰቱ ደረቅ ሰሞናት ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል ዝግጅት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል።

ሄለን ወንድምነው

 አዲስ ዘመን ሚያዝያ 16/2016 ዓ.ም

 

 

 

 

 

Recommended For You