የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በማበራከት የአየር ብክለትን የመከላከል ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተጀመሩ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በማበራከት የአየር ብክለትን የመከላከል ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።

ከንቲባዋ ከተማ አስተዳደሩ 150 የኤሌክትሪክ ሚኒ ባስ ተሽከርካሪዎችን በስሩ ላሉ መሥሪያ ቤቶች ባስተላለፈበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ከተማ አስተዳደሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ለስድስት ወራት የሚቆየውን የአየር ብክለት የመከላከል ንቅናቄ ይፋ ያደረገ ሲሆን ይህንን ንቅናቄ ወጤታማ ለማድረግ ከሚሠሩት ቀዳሚ ተግባራት መካከል በአሮጌ ተሽከርካሪዎች አማካኝነት የሚመጣውን የአየር ብክለት መከላከል አንዱ ነው። ለዚህም በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች፤ ሞተር ሳይክልና ብስክሌቶችን በስፋት መጠቀም ይጠበቃል።

ይህንንም ከግምት በማስገባት በከተማ አስተዳደሩ ስር ላሉ መሥሪያ ቤቶች በዋናነትም ለወረዳዎች 150 በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን ገዝተን አስረክበናል ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ በዚህ ቁጥር ደረጃ በአንድ ግዜ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ ሥራ ሲገቡ እንደ አዲስ አበባ ከተማ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገርም የመጀመሪያ ነው ብለዋል።

እነዚህ ተሽከርካሪዎች የአካባቢ ብክለትን ከመከላከል ባለፈም ወጪን በመቀነስ ረገድም የሚኖራቸው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፤ ከተማ አስተዳደሩ በሚያካሄደው የኮሪደር ልማት የኤሌክትሪክ ሞተር ሳይክልና ብስክሌቶችን በስፋት ለመጠቀም እንዲቻል ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል።

ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ መሥሪያ ቤቶች በተለይም በወረዳ ደረጃ ላሉት ተቋማት ትኩረት በተገቢው ሁኔታ ባለመሰጠቱ ምክንያት የተለያዩ ግብዓቶችን እጥረት እንዳለባቸው የጠቆሙት ከንቲባዋ፣ በዚህም የተነሳ የሕዝብ አገልግሎት ሲበደልና ሲጓተት ነበር ብለዋል።

እነዚህ ሚኒ ባሶች ለአገልግሎት መቅረባቸው ወረዳዎችን ብቁ በማድረግ ቀልጣፋና ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ለሕዝቡ ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ አቅም እንደሚሆናቸው የጠቆሙት ከንቲባ አዳነች፣ የወረዳ ሠራተኞች ይህንን በመገንዘብ ተገቢውን ቀልጣፋ አገልግሎት ለሕዝቡ ተደራሽ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ሲሉም ተናግረዋል።

ከንቲባ አዳነች እንደገለጹት፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማዋን የትራንስፖርት አገልግሎት ለማሳለጥና አቅርቦቱን ተደራሽ ለማድረግ በርካታ ተግባራትን አያከናወነ ይገኛል። ለዚህም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ያለው በአንድ በኩል አገልግሎቱን ማዘመን ሲሆን በሌላ በኩል አቅርቦቱን መጨመር ነው። በዚህ ረገድ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከ377 በላይ ደረጃቸውን የጠበቁ እና ዘመኑ የሚጠይቀው ቴክኖሎጂ የተገጠመላቸው አውቶብሶችን በመግዛት ለማኅበረሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ተችሏል።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12/2016 ዓ.ም

Recommended For You