
አዲስ አበባ፡– የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እጩ የሴቶችና ሕፃናት ምክትል ኮሚሽነር ለመምረጥ ማህበረሰቡ ነጻና ገለልተኛ የሆኑ እጩዎችን እንዲጠቁም ጥሪ አቀረበ፡፡
ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እጩ የሴቶችና ሕፃናት ምክትል ኮሚሽነር ለመምረጥ የሕዝብ ጥቆማ ከትናንትናው እለት ጀምሮ ለአስራ አምስት ቀናት እንደሚካሄድ ኮሚሽኑ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ለሴቶችና ሕፃናት ኮሚሽነር እጩ አቅራቢ ኮሚቴ ፀሐፊ ወይዘሮ ባንቺይርጋ መለሰ በትናንትናው እለት በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 210/1992 እና በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 1224/2012 መሠረት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንን አቋቁሟል፡፡
በመሆኑም በአዋጅ ቁጥር 210/1992 እና በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 1224/2012 መሠረት አንቀፅ 80(2) መሠረት ኮሚሽኑን የሚመሩ አንድ ዋና ኮሚሽነር፣ ምክትል ዋና ኮሚሽነር፤ አንድ የሴቶችና ሕፃናት ኮሚሽርና ሌሎች የዘርፍ ኮሚሽነሮች ተሹመው ሲሠሩ የቆዩ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ሥራ በለቀቁት የሴቶችና ሕፃናት ምክትል ኮሚሽነር ምትክ ማሟላት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
ለዚህም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የእጩ አቅራቢ ኮሚቴ በማቋቋም ሥራውን በይፋ የጀመረ ሲሆን፤ የእጩ አቅራቢ ኮሚቴው የእጩ አቅራቢ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት በማቋቋም ሥራው የሚመራበት የምልመላ መስፈርት፣የድርጊት መርሀ ግብርና የትግበራ መመሪያ አዘጋጅቶ ወደ ሥራ ገብቷል ብለዋል፡፡
የእጩ አቅራቢ ኮሚቴው አወቃቀርም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ሰብሳቢ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ምክትል ሰብሳቢን ጨምሮ ስምንት አባላትን የያዘ መሆኑንም ወይዘሮ ባንቺይርጋ ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም በመላ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ሕዝቦች ከሚያዚያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሚያዝያ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ባሉት 15 ቀናት ዕጩዎችን በአካል፣ በጽሑፍ፣ ለዚሁ አላማ በተዘጋጁ ሳጥኖች እንዲሁም በኦንላይን መጠቆም የሚችል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
እጩ አቅራቢ ኮሚቴውም በተከታታይ ተደማጭነትና ተነባቢነት ባላቸው የመገናኛ ዘዴዎች መስፈርቶች እንደሚገለጹ ወይዘሮ ባንቺይርጋ አስታውቀው፤ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥም እጩውን የመለየት ሥራውን በማጠናቀቅ ለምክር ቤት እንዲጸድቅ እንደሚቀርብ ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሴቶችና ሕፃናት ኮሚሽነር ለመሆን የሚጠቆመው ጾታ ሴት እጩዎች ሲሆኑ፤ ዜግነት ኢትዮጵያዊት እና ለኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት ተገዥ የሆኑ፣ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ተቆርቋሪ የሆኑ፤ በሕግ ወይም አግባብነት ባለው ሌላ ሙያ የሠለጠኑ ወይም በልምድ ሰፊ እውቀት ያካበቱ፣ ሥራውን ለመሥራት የሚያስችል ጤንነት ያላቸው፣ ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ገለልተኛ የሆኑ፤ከደንበ መተላለፍ ውጪ በሌላ የወንጀል ጥፋት ተከሰው ያልተፈረደባቸው እና ዕድሜአቸው ከ35 ዓመት በላይ የሆኑ መሆን እንደሚኖርበት አስታውቀዋል፡፡
በመሆኑም ተቋም የሚገነባው በጠንካራ አመራር በመሆኑ ከላይ የተገለጹትን መስፈርቶች የሚያሟሉ ነፃና ገለልተኛ የሆኑ እጩዎችን ከመላው የሀገሪቱ ሕዝቦች እንዲጠቁሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ማህሌት ብዙነህ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 8 ቀን 2016 ዓ.ም