
አዲስ አበባ፡- የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ እየሰራቸው ባሉ የማህበረሰብ አቀፍ የምርምር ሥራዎች 71 የእንሰት ዝርያዎች ከመጥፋት መታደግ መቻሉን አስታወቀ፡፡
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የምርምር፣ የማኀበረሰብ አገልግሎትና የቴክኖሎጂ ትራንስፈር ምክትል ፕሬዚዳንት ዮሐንስ ገብሩ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳስታወቁት፤ ዩኒቨርሲቲው እየሰራቸው ባሉ የማህበረሰብ አቀፍ የምርምር ሥራዎች 71 የእንሰት ዝርያዎች ከመጥፋት መታደግ ችሏል፡፡
በአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች ከተካተቱ 15 ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ነው ያሉት ዶክተር ዮሐንስ፤ ዩኒቨርሲቲው የምርምር የማኅበረሰብ አገልግሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ስራዎችን እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው የፈርዝዬ የእንሰት ምርምር ማዕከል አቋቁሞ በእንሰት ዙሪያ እየሰራ መሆኑን ዶክተር ዮሐንስ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ምቄ የሚባል የቡና እና የፍራፍሬ ምርምር የሚካሔድበት ጣቢያ እንዳለው አስረድተዋል፡፡
ሁሉም ዝርያዎች የየራሳቸው ጠቀሜታ እንዳላቸው የጠቆሙት ኃላፊው፤ ዝርያዎች እንዳይጠፉ ማድረግ፣ በሽታን የመከላከል ሒደት ማሻሻል፣ የአሰራር ሂደትን ማዘመን እንዲሁም የተለያዩ ማሽነሪዎችን ማፍለቅ በምርምር ማዕከሉ ከሚሰሩ ሥራዎች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
እንደ ዶክተር ዮሐንስ ገለጻ፤ በተሰሩ የምርምር ሥራዎች የእናቶችን ድካምና ጊዜ መቀነስ እንዲሁም በእንሰት ላይ የሚከሰቱ የተለያዩ በሽታዎችን መከላከል ተችሏል፡፡ በተለይ በማሽነሪ ለማምረት በተደረገ ጥረት ሁለት ማሽኖች በመስራት በቅርቡ ሰርቶ ማሳያ ላይ ሙከራ መደረጉን አመልክተዋል፡፡
ማሽኖች ተሻሽለውና ያሉባቸው ችግሮች ተፈትተው ለእያንዳንዱ አርሶ አደር ለማዳረስ ባይቻል እንኳን በጋራ የተደራጁ ወጣቶችን በማዋቀር የእንሰት ወፍጮ ቤት በወረዳው ላይ ለማቋቋም እቅድ እንደተያዘም ነው ዶክተር ዮሐንስ የገለጹት፡፡
አንዳንዶቹ የእንሰት ዝርያዎች ለመድኃኒትነት የሚያገለግሉ ናቸው ያሉት ዶክተር ዮሐንስ፤ የእንሰት ተረፈ ምርት ከአሸዋና ከጠጠር ጋር ተደባልቆ ለአስፋልት ጥንካሬ ይሰጣል የሚል እሳቤ በመኖሩ በሲቪል ኢንጂነሪንግ ጥናት እንዲሰራ የሚደረግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
እንሰት የምግብ ዋስትናን እና የአየር ንብረት ተፅዕኖ ላይ ያለው ሚና ለማረጋገጥ በአግሪካልቸራል ኢኮኖሚክስ የሚሰሩ ፕሮጀክቶች አሉ ያሉት ዶክተር ዮሐንስ፤ እንሰት ከምግብነት በተጨማሪም ከተረፈ ምርቱ ለመኝታ አገልግሎት እንዲሁም ጥራት ያለው ወረቀት ለማምረት እንደሚያስችል አስታውሰዋል፡፡
ልጅዓለም ፍቅሬ
አዲስ ዘመን መጋቢት 12 ቀን 2016 ዓ.ም