
ቦንጋ፡- ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ እንደሀገር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ከአካባቢው የመልማት ጸጋ ጋር በማቀናጀት እየሠራ መሆኑን አስታወቀ። ዩኒቨርሲቲው በአምስት የቡና ጣቢያዎች ሁለት ሚሊዮን የተለያዩ የቡና ዝርያዎችን እያለማ ነው።
የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክስ ምርምር ቴክኖሎጂ ሽግግርና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ከለላው አዲሱ(ዶ/ር) ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው ከተመሰረተ ስድስት አመቱ ቢሆንም ባጭር ጊዜ ውስጥ ከአካባቢው ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት ያለውን የመልማት ጸጋ ማህበረሰቡ በአግባቡ እንዲጠቀም ለማስቻል የተለያዩ የምርምር ስራዎችን እየሰራ ነው።
እንደ ዶክተር ከለላው ገለጻ፣ ክልሉ በቡና፣ በማር፣ በኮረሪማ፣ በእንሰት፣ በበግ እርባታና ሌሎች ዘርፎች ላይ ያለውን አቅም በጥናት የተመሰረተ ስራ በማከናወን የማህበረስቡን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ሰፊ ስራ እያከናወነ ነው። በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የቦንጋ በግ፣ የበሬ ማድለብ፣ የወተት ላም፣ የቡና ልማት፣ የሙዝ፣ የአናናስና የአፕል ፍራፍሬዎችን ምርት ለማባዛት ተግባራዊ ምርምሮችን እያካሄደ ነው።
ዩኒቨርሲቲው ለምርምር የሚሆኑ ቦታዎች በክልሉ ባሉ ዞኖችና ወረዳዎች የምርምር ቦታዎችን ተረክቦ ለአርሶ አደሩ ችግኞች ለማሰራጨት እየሰራ መሆኑን የገለጹት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ በተለይም ሀገራዊ አቅጣጫ ከሆነው የሌማት ትሩፋት ጋር ቁርጠኝነት ያላቸው እንደ ዶሮ እርባታ፣ የወተት ላሞች እርባታና ማዳቀል ስራ በመስራት ውጤታማ ስራ መስራቱን ገልጸዋል።
ዶክተር ከለላው እንደሚሉት፤ በሚያከናውነው የሌማት ስራ ስራአጥ ሴቶችን በማደራጀት ወተት፣ እንቁላል፣ ሙዝና ሌሎች አትክልትና ፍራፍሬዎችን የሚሸጡበት ሱቅ አመቻችቷል። በተጨማሪም በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ጧሪ ለሌላቸው 54 አረጋውያን የማይቋረጥ ድጋፍ እያደረገ ሲሆን በዘላቂነት የሚኖሩበት ጤና ጣቢያ ያለው የመኖሪያ ቤት ግንባታም አካሂዷል።
ዩኒቨርሲቲው ለመጀመሪያ ጊዜ በመጀመሪያ ዲግሪ 37 እንዲሁም በሁለተኛ ዲግሪ 12 ተማሪዎችን በቡና ቴክኖሎጂ እንደሚያስመርቅ የተናገሩበት ዶክተር ከለላው፣ በአምስት ጣቢያዎቹ 74 አንድ 10፣ 74 አንድ 12 እና 74 ፤ 54 የተባሉ የደጋ፣ የቆላና የመካከለኛ ቦታዎች ተስማሚ የሆኑ ሁለት ሚሊዮን የቡና ችግኞች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
ሞገስ ተስፋ
አዲስ ዘመን መጋቢት 12 ቀን 2016 ዓ.ም