
አዲስ አበባ፡– ኢንዱስትሪዎች አብሮ በጋራ መሥራትን እና ምርት መቀባበልን እንዲላመዱ የሚያስችል ስትራቴጂካዊ አጋርነት ከክልሎችና ተቋማት ጋር መፍጠር መጀመሩ ተገለጸ፡፡
ኦ ፕሮድዩስ ኢንቨስትመንት ግሩፕ እና ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ትናንት ተፈራርመዋል፡፡
የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ሥራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱለይማን ደደፎ፤ ስምምነቱ አብሮ በጋራ መሥራትን፣ ምርት መቀባበልንና ምርምሮችን በጋራ መሥራት የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው፤ ከሁሉም የክልል ተቋማት ጋር ስትራቴጂካዊ አጋርነትን መፍጠር ተገቢ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የመግባቢያ ስምምነት ፊርማውም ኢንዱትሪዎች በጋራ እንዲሠሩ ለማስቻል ስትራቴጂካዊ አጋርነትን መፍጠር ለመጀመሩ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ በሀገሪቱ የኢንዱስትሪ ዘርፉን መምራት፣ ማገዝና ማስፋፋት ላይ እየተሠራ ነው ያሉት አምባሳደሩ፤ አምራችነትን በማስፋፋት፣ ከውጭ የሚገባን ምርት በመቀነስ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡትን መደገፍ ይገባል ብለዋል፡፡
ኦ ፕሮድዩስ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ማርታ በላይ በበኩላቸው፤ ስምምነቱ በማሽን መለዋወጫ፣ ዕቃ አቅርቦትን ጨምሮ በቴክኖሎጂ ውጤቶች ትግበራና በቴክኒካል እገዛ ዘርፍ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
ግሩፑ ለክልሉ ብሎም ለሀገሪቱ የኢንዱስትሪ ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛል ያሉት ኢንጂነር ማርታ፤ የመንግሥት ሀብት የሆኑ የልማት ድርጅቶችን በገበያ ሥርዓት ውስጥ ተወዳዳሪና ውጤታማ ለማድረግ እየተሠራ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛሬን ለማዳን በመስራት ላይ እንደሚገኝም ነው የጠቆሙት፡፡
የተለያዩ የማሽን መለዋወጫዎችን እቃዎችንና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እየተሰራ መሆኑን በመግለጽ፤ በማሽን መዋወጫ እጥረት ምክንያት የሚፈጠሩ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ እንደሚያስችል አመልክተዋል፡፡
ኦ ፕሮዲዩስ ግሩፕ በገበያ ሰንሰለቱ ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት፣ ዋጋን ለማረጋጋትና የክልሉን ኅብረተሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሠራም አያይዘው ተናግረዋል፡፡
አቅምን አሟጦ በመጠቀም ሀገሪቱ ወደ ኢንዱስትራላይዜሽን ለምታደርገው ጉዞ የበኩሉን ለመወጣት የተቋቋመ ግሩፕ ነው ያሉት ኢንጂነር ማርታ፤ በስሩ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች የልህቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ሆነው እንዲያገለግሉ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡
ኦ ፕሮድዩስ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የኦሮሚያ ኢንቨስትመንት ግሩፕ አካልና የመንግሥት የልማት ድርጅት ሲሆን፤ ስድስት ኢንዱስትሪዎችን እያስተዳደረ የሚገኝ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን መጋቢት 12 ቀን 2016 ዓ.ም