
አዲስ አበባ፡- “ለነገዋ” የሴቶች ተሐድሶና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል እንደሀገር ያለውን የስክነትና አርቆ የመመልከት ስብራት ለመጠገን ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የተገነባውን “ለነገዋ” የሴቶች የተሐድሶና የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸውና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተገኙበት ትናንትና ተመርቋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማበልጸጊያ ማዕከሉ የምረቃ መርሐ ግብር ባደረጉት ንግግር እንዳስታወቁት፤ በአዲስ አበባ ከተገነቡ ፕሮጀክቶች ሁሉ ድንቅ ሥራ የሆነው የማበልጸጊያ ማዕከሉ የኢትዮጵን ስብራት ለመጠገን ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል፡፡
ልጆች ተንከባክበን በማስተማር ለወግ ለማዕረግ ማብቃት ሲገባን ባሉብን ዘርፈ ብዙ ድካሞች ለጎዳናና ላልተገባ የሕይወት መስመር ይዳረጋሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ የነዚህን ዜጎች የሕይወት መስመር ማቅናት እንደሀገር ያለውን ስብራት ለመጠገን ይረዳል ሲሉ ተናግረዋል።
በማዕከሉ አማካኝነት በዓመት 10 ሺህ ሴቶችን ካሉበት የኑሮ ሁኔታ አውጥቶ የተሻለ ሥራ ማስያዝ የምንችል ከሆነ 10 ማዕከል ከገነባን ደግሞ በዓመት 100 ሺህ ሴቶችን ወደተሻለ ሕይወት መመለስ እንችላለን ብለዋል፡፡
የማዕከሉ መገንባት በተለያዩ ምክንያቶች ለማኅበራዊ ችግሮች የተጋለጡ ሴቶችን ተሐድሶ በመስጠት መልሶ ለማቋቋም የሚረዳ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም በዓመት 10 ሺህ የሚደርሱ ሴቶችን ከጎዳና ሕይወት አውጥቶ የተሻለ ሥራ ማስያዝ የሚያስችል በመሆኑ ስብራታችንን ለመጠገን እድል ይፈጥራል ሲሉ አስረድተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት፤ አሻግሮ የመመልከትና ትውልድን ማዕከል አድርጎ ያለመሥራት እንደሀገር ካሉብን ስብራቶች መካከል የሚጠቀስ ነው። ትልቁም ትንሹም፣ ሀብታሙም ድሃውም፣ ወጣቱ፣ የተማረውም ሆነ ያልተማረው ዛሬ ላይ ስለሚያገኛት ነገር እንጂ ነገን እያሰበ አለመሥራቱ ጉዳት ነው ሲሉ ጠቁመዋል።
ማዕከሉ የኢትዮጵን ስብራት ለመጠገን ከሚያበረክተው አስተዋፅዖ ባለፈም ነገ ከነገወዲያም መሰል ፕሮጀክቶችን በኅብረት ለመሥራት ስንቅ የሚሆን ነው ብለዋል፡፡
ሴቶች በኢትዮጵያ ግማሽ ቁጥር ያላቸው ብቻ ሳይሆኑ በሁሉም ሥራዎች ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን አስታውሰው፤ እነሱንም ማሰብ፣ ማነጽ፣ ማስተማርና ዕድል መስጠት ካልቻልን እንደሀገር ለመለወጥ ያለን ሕልም ሙሉ አይሆንም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ባልተገባ መንገድ ሕይወታቸውን የሚመሩ ሴቶችን ወደተሻለ ሕይወት ስንመልስ እነርሱን ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር ያለብንን የስክነት፣ የማሰብ፣ የማስተዋል፣ አርቆ የመመልከት ስብራት ለመጠገን ማዕከሉ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደሚያበረክት አብራርተዋል፡፡
በአዲስ አበባ የታሪክ ስብራታችንን ለመጠገን የዓድዋ ሙዚየምን ጨምሮ፣ ወዳጅነት፣ እንጦጦና አንድነት ፓርክን፣ አብርኆት ቤተ መጽሐፍትን፣ መስቀል አደባባይ እና ሌሎች በርካታ ፕሮጀክቶች መገንባት እንደተቻለ አንስተዋል።
በአዲስ አበባ የተገነቡት ሁሉም ፕሮጀክቶች ቢደመሩ “ለነገዋ” የሴቶች ተሐድሶና ክህሎት ማበለጸጊያ ማዕከልን ያክል ግዝፈት እንደሌላቸው አመላክተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አበቤ በበኩላቸው፤ ማዕከሉ በተለያዩ ምክንያቶች ለማኅበራዊ ችግሮችና ለወሲብ ንግድ ለተጋለጡ ሴቶች ተሐድሶ በመስጠት መልሶ ለማቋቋም የሚረዳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ማዕከሉ በየዓመቱ ለ10 ሺህ ሴቶች ሥልጠና በመስጠት በዘላቂነት እንዲቋቋሙና ገቢ እያገኙ ራሳቸውን እንዲችሉ እገዛ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡
ወጣት ሴቶቹ በማዕከሉ ቆይታቸው ከሚያገኙት የሥነ-ልቦና ድጋፍ በተጨማሪ የሥነ-ውበት፣ የከተማ ግብርና፣ የምግብ ዝግጅት፣ የፀጉር ሥራ፣ የእንጨት ሥራዎች፣ የልብስ ስፌት፣ የከተማ ውበት አጠባበቅና የኮምፒዩተር ሙያ ሥልጠና ወስደው ወደ ሥራ እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል፡፡
ማዕከሉ በውስጡ የተሐድሶ ሥልጠና የሚሰጥባቸው የክህሎት ማበልፀጊያ፣ የማሠልጠኛ ማዕከላት፣ የሥነ-ልቦናና የምክር አገልግሎት፣ የሕክምና ማዕከል፣ ማደሪያ ክፍሎች፣ መመገቢያ አዳራሾች እንዲሁም የስፖርት ማዘውተሪያና የመዝናኛ ስፍራዎችን ማካተቱን ገልጸዋል፡፡
ሄለን ወንድምነው
አዲስ ዘመን መጋቢት 6 ቀን 2016 ዓ.ም