ሻሎ – እጀ ብረቷ ገበሬ

አርሲ ምድር ፤ ‹‹አድአ ሻቄ›› ቀበሌ። የለም መሬት፣ ማሳያ የአረንጓዴ ምርት መገለጫ ነው። አካባቢው ሁሌም የሰጡትን አይነሳም። ከዓመት ዓመት ምርት ያሳፍሳል። ኩንታል እህል ያስከምራል። በዚህ መንደር ሕይወታቸው ግብርና የሆነ ብርቱዎች ከእርሻ አርፍደው ይውላሉ።

የአድአ ሻቂ ሰዎች ሕይወታቸው በግብርና ተመስርቷል። ማልደው ሲወጡ መገኛቸው ከማሳው ፣ ከመስኩ ነው። እንዲያም ሆኖ ልጆቻቸው ቢማሩ፣ ቀለም ቢቆጥሩ ይወዳሉ። ልጆቹ መሬት አርሰው፣ ምርት አፍሰው ብቻ እንዲኖሩ አይሹም። እነሱም እንደሌሎች ዕውቀት ቀስመው ወግ ማዕረግ ቢያዩ፣ ካሰቡት ቢደርሱ ደስታቸው ነው።

ሻሎ የሻቂ ፍሬ…

ልጅቷ ገና ስትወለድ እንደብርሃን መድመቋን፣ እንደ ጸሀይ መፍካቷን ያዩ ወላጆቿ ‹‹ሻሎ›› ሊሏት አልዘገዩም። ሻሎ የፈካ፣ የደመቀ ብርሃን እንደ ማለት ነው። የሻቂዋ ፍሬ ሻሎ ዓለሙ በዚህ መንደር ልጅነቷ ሲያብብ ግብሯም እንደ መልኳ የፈካ፣ የደመቀ ሆነ። በምግባሯ የሚወዷት፣ የሚያደንቋት በረከቱ። ስለ ሻሎ ወላጆቿ ይሳሳሉ። በሩቅ የሚያውቋት ደግሞ ውበቷን አይተው ያደንቃሉ።

የገጠሯ ጉብል ሻሎ መልካም ቆንጆ ናት። ከግብርናው ስትውል ክንደ ብርቱ፣ ከቀለም ስትገኝ አዕምሮ ብሩህ ወጣት። ሻሎ ስንፍና ይሉት አያውቃትም። ድካም አይጎበኛትም። ከጠዋት እስከ ማታ በእርሻና ትምህርት ተጠምዳ ትውላለች። ቤት ስትደርስ ደግሞ ጉልበቷ አይደክምም። እንደሴትነቷ ከእናቷን ማጀት ገብታ ጎንበስ ቀና ትላለች።

ልጅ ብትሆንም ውጥኗ የበዛ ፣ ሃሳቧ የሰፋ ነው። ባላት ትርፍ ጊዜ ከውሃ ልማት ተቀጥራ የቦኖ ውሃ ታስቀዳለች። የዛኔ የሚከፈላት ደሞዝ አንድ መቶ አምስት ብር ነበር። ሻሎ ብሩ ‹‹አነሰኝ›› ሳትል በቆጠበችው ገንዘብ ሁለት ጥማድ መሬት ገዝታ ታሳርሳለች። የሚገኘው ምርት የገቢ ምንጯ፣ የቤቷ መደጎሚያ ነው።

ሻሎ ስምንተኛ ክፍል እንደገባች የአንድ ሰው ዓይን አረፈባት። ወዶ የቀረባትን፣ ቀርቦ ያዋያትን ሰው አልገፋችውም፣ አልጠላችውም። የእሷም ልብ እንደሱ፣ ቢወድ ቢፈቅደው በይሁንታ ቀረበችው። ውሎ አድሮ ስሜት ዓላማቸው አንድ ሆነ። ለቁም ነገር ያሰባት እጮኛዋ ሽማግሌ ልኮ ጋብቻ ጠየቀ። ቤቶቿ ለብርቱው ገበሬ ልጃቸውን ‹‹እምቢኝ ›› አላሉም። ወደውና ፈቅደው መርቀው ሰጡት።

ሙሽሪት ልመጂ …

የሻሎ ባለቤት ከቀለም የተዋደደ፣ ከዕውቀት የቀረበ ነው። ቀድሞ ወታደር ነበርና በብዙ ፈተናዎች ተመላልሷል። ይህ እውነት ከማንነቱ ተዳምሮ ፣ መልካም አባወራ ሊሆን አስችሎታል። ለግማሽ አካሉ ደግ ባለቤት ነው። የሚያውቁትን ሁሉ ያከብራል። የቀረቡትን ይወዳል። ሚስቱ ሻሎ የዋህነቱን፣ አርቆ አሳቢነቱን ትወድለታለች። ለእሷ ሁሌም አክባሪ ባሏ ነው። በፍቅር በአክብሮ ት ማ ደርን አስተምሯታል።

በእነሱ ጎጆ ፍቅርና ሰላም ሰፍኗል። ባሏ እንደ ወንድም መካር፣ እንደ አባት ተቆጪ፣ እንደ ባል አባወራ ነው። ከእሱ ለምዳ ሕይወት ለመጋራት፣ ኑሮ ለመምራት አልከበዳትም። አስተዋዩ ባሏ ትዳሩን በክብር ፣ ቤቱን በፍቅር ይይዛል። በእነሱ ጎጆ የሴት፣ የወንድ ይሉት ሥራ የለም።

እሷ እንጀራ ብትጋግር ወጡ የእሱ ድርሻ ነው። ልብስ ብታጥብ ቡና ማፍላት ግዴታው ይሆናል። ጥንዶቹ ሁሌም በፍቅር ያድራሉ። በመስማማት ይኖራሉ። ሁለቱም ስለነገው የወጠኑት ህልም አንድ አይነት ነው። በላብ በወዛቸው ድካም ነገን ትጉህ ገበሬ መሆን ዓላማቸው ሆኗል።

ትምህርት ፣ ልጆች፣ ሥራ

ሻሌ ተማሪ ሳለች የያዘችው ጥማድ ከአባወራዋ መሬት ተዳምሮ ሥራ ከጀመረ ሰንብቷል። ብርቱዎቹ ባልና ሚስት ዛሬም ቋንቋቸው ፍቅር ነው። ‹‹አንተ ትብስ አንቺ›› መባባሉ ብርቃቸው አይደለም። በቤታቸው ሶስት ልጆች ከተወለዱ በኋላ አባወራው ሚስቱ ትምህርት እንድትቀጥል ፈልጓል። ይህ ደግነት ብርታት የሆናት ሻሌ ከዓመታት በኋላ ደብተር ይዛ ትምህርት ቤት መዋል ጀም ራለች።

ሻሌ አሁንም የቦኖ ማስቀዳት ሥራዋን ላይ ነች። የምታገኘው ጥቂት ገቢ ለጎጆዋ ይደጉማል። መማሯን ያስተዋሉ አሰሪዎቿ ግን ዓላማዋን አልወደዱም። ትምህርቷን እንድታቆም ማስገደድ ይዘዋል። ጥሩ አሳቢው ባሏ ዛሬም ከጎኗ ነው። ጅምሯን እንድትለቅ፣ ሥራዋን እንድትተው አይሻም።

ይህ እውነት አማራጮች አሰፋ። በግል ተመዝግባ ለፈተናው እንድትዘጋጅ ሆነ። ሻሌ በወጉ አጥንታ ያሰበችውን ፈጸመች። ሚኒስትሪን በጥሩ ውጤት አልፋ ለዘጠነኛ ክፍል በቃች። ይህ ውጤት የእሷ ብቻ አይደለም። የበጎ አሳቢው ባለቤቷ ድርሻ ጭምር እንጂ።

ሻሎ ዘጠነኛን ክፍል ከመጀመሯ አራተኛውን ልጅ ነብሰጡር መሆኗን አወቀች። ትምህርቱ ሲገፋ ፈተናው ሲዳረስ ድካሙን አልቻለችም። የቤት ኃላፊነት ልጆች ከማሳደግ ጋር ይከብዳት ያዘ። ይህኔ ባልና ሚስት ተቀምጠው መከሩ። ሁሉን ትታ ወደፊት በሚያስቡት እቅዳቸው ላይ ብቻ እንድታተኩር ተስማሙ። የታሰበው ሁሉ በጊዜው ተከወነ። እጅን በአፍ የሚያስጭን፣ የላብ የድካም ፍሬ ዕውን መሆን ያዘ።

ከዓመታት በኋላ…

እነሆ ! ሂጦሳ ወረዳ ‹‹ሻቂ ሸረራ›› ቀበሌ ላይ ነኝ። ከወይዘሮ ሻሌ ወብ ጊቢ ተገኝቻለሁ። ሥፍራው ገጠር ነውና ነፋሻው አየር ይማርካል። ፊት ለፊት የቆመው ግዙፍ ቪላ ዘመናዊ የሚባል ነውና ለጊቢው ግርማ ሞገስ ሆኖታል። የማየው እውነት ለአፍታ በእንግድነት የሚያስቀምጠኝ አልሆነም። ሰፊውን አጸድ ተዘዋውሬ ከማየቴ በአድናቆት መደመም ፣ መገረም ጀምሪያለሁ።

ሻሌ ጠንካራዋ ወይዘሮ፣ ክንደ ብርቱዋ ገበሬ። ዛሬም በሥራ ላይ ነች። ለአፍታ እረፍት ይሉት የላትም። መባተል ከጀመረች ቀን ሌቱ አይበቃትም። ከጊቢው ተዘዋውሬ ሁሉን ባየሁ ጊዜ ድካም ልፋቷ ፍሬ መያዙ ገባኝ። ከሰፊው ቦታ ላይ አንዳች ቁራሽ መሬት አልባከነም። እያንዳንዱ ሥፍራ የተሰጠው የሥራ ድርሻ በግልጽ ይስተዋላል።

ማንም አጋጣሚ አግኝቶ ወደዚህ ሥፍራ ቢገባ ለአፍንጫው የሚደርሰውን መልካም መአዛ እንደዋዛ ችላ ማለት አይቻለውም። ውሰጡ ፍጹም በሆነ የአዕምሮ እርካታ ይሞላል። እግሮቼ ከአረንጓዴው የአትክልክት ቦታ ላይ ቆመዋል።

በአቦአካዶ ፣ ሙዝና ማንጎ፣ በቡና አፕልና የንብ ቀፎ የተሞላው ጊቢ ለዓይን ይማርካል። ዙሪያውን የታጀበው የጤናአዳም፣ የበሶብላ፣ አዝመሪኖና ቃሪያ ሽታ አሁንም እየተከተለኝ ነው። በቀላሉ የማይገለጽ እርካታ ተሰማኝ። በየአፍታው ደስታና አድናቆት ይፈራረቁብኝ ያዙ። የማየው በረከት ሁሉ አስደመመኝ። በውስጤ ይህን ላደረጉ ጠንካራ እጆች አድናቆትና ምስጋና አቀረብኩ። ‹‹ሻሎ አንቺ! ድንቅ ሴት ጉልበትሽ አይድከም፣ እጆችሽ አይዛሉ››።

የሻሎ በረከቶች…

ሻሎ ክንደ ብርቱዋ ገበሬ ከሌላት ጊዜ፣ ከምትሳሳለት ቀን ደቂቃዎችን ተበድራ የልፋት ድካሟን ፍሬ እያስጎበኘችኝ ነው። በእርግጥ ብቻዬን አይደለሁም። እንደኔው የእሷን በረከት የሚጎበኙና ስለማንነቷ ጠንቅቀው የሚያውቁ የግብርና ባለሙያዎች አብረውኝ አሉ። አሁን በኮባና ፍራፍሬ የተሞላውን ሰፊ ጊቢ እያለፍን ነው። ብዙ የተለፋበትን መሬት ለመርገጥ ጥንቃቄ ያሻል። እንዲያም ሆኖ እግራችን ከአንድ የባዮ ጋዝ ማብላያ አድርሶናል።

በሻሎ እጆች በጥልቀት የተዘጋጀው ጉድጓድ በከብቶች አዛባ ተሞልቶ መዋሀድ፣ መብላላት ጀምሯል። ሽታው ለአፍንጫ አይረብሽም። ሻሎ አዛባውን በረጅም እንጨት እየበጠበጠች በቀጭኑ በተዘረጋው የቧንቧ መስመር ትለቀዋለች። የተለቀቀው ፍሳሽ መድረሻውን አይስትም። በአፍታ ራሱን ቀይሮ ጋዝ በመሆን ለማጀቷ ይደርሳል።

ማጀቷን ለማየት ተከትለናት ገባን። ጨለም ያለውን የማብሰያ ክፍል በትልቁ አምፖል ወገግ አድርጋ አበራችው። በዚህ ብቻ አልቆመችም። እንደ ከተሜው ኤሌክትሪክ ያለውን ምድጃ በአንዴ ለኩሳ ብረት ድስቷን ጣደች። እሳቱ እንዳሻው እየጨመረ ፣ እየቀነሰ ሃይሉን አሳየን። ምግብ ሲበስልበት፣ ሻይ ቡና ሲፈላበት ተመልክተን አደነቅን፣ ተደነቅን።

ከባዮ ጋዝ ማብለያው ጥግ በወጉ የተዘጋጀ የአፈር ማዳበሪያ ለዓይን ይስባል። አፈሩን የሚያዳብሩት ትሎች ሆን ተብለው የተፈጠሩ ናቸው። ሻሎ ትሎቹን ለአፈሩ ማዳበሪያነት ትጠቀማቸዋለች። እነሱ ለእሷ የገቢ ምንጭ ሆነዋል። ማዳበሪያውን በኩንታል መግዛት የሚሹ ደንበኞች በርካቶች መሆናቸውን ነግራናለች። የሻሎ ጠንካራ እጆች በየጊዜው የእንጨት ቆጣቢ ምድጃዎችን እያመረቱ ያወጣሉ። በእጆቿ ጥበብ የምታዘጋጃቸው የቁም ምድጃዎች በበርካቶች ዘንድ የሚፈለጉ፣ የሚመረጡ ሆነው ዓመታትን ዘልቀዋል።

ሻሎ ለአካባቢው ዘመናዊነትን የተረዳች ይመስላል። ለከብቶች የሚያስፈልጋትን መኖ የምታዘጋጀው በጊቢዋ ባቆመችው የመፍጫ ማሽን ታግዛ ነው። ይህ ማሽን የእርሻ በሬዎቿን ጨምሮ ዛሬም በበረት ለሚገኙ ከብቶች መድህን ነው። በሆዱ ምግቡን አላምጦ፣ አድቅቆ ያጎርሳቸዋል። እንዲህ መሆኑ ለባተሌዋ ወይዘሮ እፎይታን ፈጥሯል። ከዚህ ቀደም በርከት ያሉ የፈረንጅ ላሞች ነበሯት። ወተታቸውን፣ እርጎና ዓይባቸውን እየሸጠች ተጠቅማለች።

ወይዘሮዋ መሬት ተከራይታ እያረሰች ሽንኩርት ተክላ ትሸጣለች። የጊቢዋ አቦካዶ በደረሰ ጊዜም በሳጥን እየሞላች ለገበያ ታቀርባለች። ከአካባቢዋ ወጣ ከሚል ገጠር ባላት የእርሻ መሬት ስንዴ እየዘራች ታበቅላለች። ምርቱ ለገበያ ውሎ ጎኗን፣ ቤቷን ይደጉማል።

ሻሎ በጤና አጠባበቅና ቤት አያያዝ ላይ ያላት ልምድ ለየት ይለያል። ጥንካሬዋም ለሌሎች ተምሳሌት እስከመሆን ደርሷል። በትልቁ ቤት ግርጌ ማለፍ እንደያዝን ገርበብ ያለውን ክፍል ዓይኖቼ ቃኙት። ከአፍ እስከ ገደፉ እህል በተሞሉ ማዳበሪያዎች ተጨናንቋል። አዕምሮዬ እርፍ ነቅንቆ ጠንክሮ ስላረሰው ገበሬ አስታወሰኝ። ሻሎ ማለት እንደእሱ ናት። ከዓመት ዓመት ጎተራዋ የሞላ ፣ ጓሮዋ የለመለመ ጠንካራ አራሽ።

የሻሎን አፀድ ዙሪያ ገባ እየቃኘን ነው። የእሷ ጠንካራ ክንዶች ያረፉባቸው በረከቶች ታይተው አይታለፉም። አካባቢው የገጠር ቀበሌ ቢሆንም በከተማ ካሉት እውነታዎች እምብዛም አይለይም። የቪላዋን በረንዳ አልፈን ወደሳሎን በገባን ጊዜ አረፍ ያልንበት መቀመጫ ምቾት ሰጠን። መልካም ይሉት ሶፋ ነው። ብፌዋን የሞሉት ዘመናዊ ዕቃዎች ድንቅ ናቸው።

የቤት አያያዟ ይማርካል። ከማጀቷ የሚጋገረው ትኩስ እንጀራ የኤሌክትሪክ ምጣድ መሆኑን አይቻለሁ። የቤተሰቡ ልብስ የሚታጠበው በዘመናዊ የልብስ ማጠቢያ ማሽን ነው። ምግብ በስሎ ከፍሪጅ ይቀመጣል። የእሷና የልጆቿ መኝታ ቤቶች በወጉ የተዘጋጁ፣ በንጽህና የተያዙ ናቸው።

በሻሎ ጊቢ ሌላው አቅጣጫ የተሠሩ ቤቶች መኖሪያዎች ብቻ አይደሉም። መዝናናትን ለሚሹ ሻይ ቡና የሚባልባቸው ማረፊያዎች ጭምር እንጂ። በዚህ ስፍራ ያለው የፑል ማጫወቻ ለአካባቢው ወጣቶች ጊዜ ማሳለፊያ ሆኗል። በርካቶች ሰብሰብ ብለው ይዝናኑበታል።

በሻሎ ሳሎን የጀመርነው ውይይት ቀጥሏል። በጨዋታ መሀል በየሰበቡ ስለምታነሳው ባለቤቷ እያወጋችኝ ነው። እሷ ስለእሱ ያላት አክብሮት በእጅጉ ይለያል። ዛሬ ለደረሰችበት ታላቅነት ሰፊውን ድርሻ የሚወስደው የትዳር አጋሯ መሆኑን አትሸሽግም።

የስድስቶች እናት ሻሎ …

አቶ በየነ የልጅነት ባሏ ነው። ትምህርቷን ትታ ከእሱ ወዳ፣ ፈቅዳ የተጣመረችው ግማሽ አካሏ። ስለ ባለቤቷ ስታወጋ ዓይኖቿ ውሃ ይሞላሉ። ደግነቱን፣ የዋህነቱን፣ ለትዳር ታማኝነቱን የተለየ ቦታ ትሰጣዋለች። ሻሌ 22 ዓመታትን በትዳር ስታሳልፍ ስድስት ልጆችን አፍርታለች።

እሷ ለልጆቿ ልዩ ክብርና ፍቅር አላት። ቤት ጎጆዋን ስታስብ ፣ ስኬቷን ስታይ ደግሞ ለአፍታ የግማሽ አካሏን ውለታ አትዘነጋም። ጥቂት ዓመታትን ወደ ኋላ መለስ ስትል በሕይወቷ የተፈተነችበት ፣አንገቷን ደፍታ ያዘነችበት ክፉ ጊዜ ትዝ ይላታል። ዛሬም ቢሆን ይህ ስሜት በአዕምሮዋ ውል እያለ ያስተክዛታል። ‹‹ልርሳው፣ ልተወው›› ብትል የማይቻላት ነውና።

ስብራትን በትዝታ…

ሻሌ አራተኛ ልጇን ነፍሰጡር ሳለች ባለቤቷ በየነ በድንገት ታመመ። ሌቱን ሲያስጨንቀው ባደረው ጉዳይ መላው ቤተሰብ ጭንቅ ገባ። ሲነጋ ሆስፒታል ሄዶ ሀኪም አገኘው። ድንገት ያጣደፈው ህመም ውጤቱ ሲጠበቅ የደም ግፊት መሆኑ ታወቀ። በአስቸኳይ መድሃኒቱን ጀመረ። ጊዜያት አለፉ። አባወራው ያዝ ለቀቅ ከሚያደርገው ህመም እየታገለ 12 ዓመታትን አስቆጠረ።

አባወራው በእነዚህ ዓመታት ለሻሌ የማይዝል ብርቱ ክንድ ከመሆን አልታቀበም። ሁለቱም ውጥናቸውን ከዳር ለማድረሰ መታገላቸውን ቀጠሉ። በግብርናው፣ በአትክልቱ ምርት ፍሬያማ ለመሆን ታገሉ። ጥንዶቹ ሁሌም ልጆቻቸውን አስተምረው ወግ ማዕረግ ለማድረሰ ያቅዳሉ። ይህ ይሆን ዘንድ አባወራው የቤቱ ራስ ነው። ሚስቱ ሻሌ ደግሞ ምሰሶና ማገር።

ባልና ሚስቱ ብዙ አቅደዋል። ሥራቸው ባለበት እንዲቆም አይሹም። ስለነገ ዛሬን ይሮጣሉ። ሩጫቸው ድካም አልባ እረፍት የለሽ ነው። ውሎ አድሮ ግን ይህን ፍጥነት የሚገታ እንቅፋት ተከሰተ። ብርቱው አባወራ አቅም ከጤና ያጣ ጀመር።

አሁንም ከሀኪም ፊት ቀረበ። የህክምናው ውጤት ሁለቱም ኩላሊቶቹ ሥራ ማቆማቸውን አመላከተ። መላው ቤተሰብ ከማይወጣው ጭንቅ ገባ። ስድስተኛ ልጇን ነፍሰጡር የሆነችው ሻሌ ከልብ ከፋት፣ ሆድ ባሳት። ትይዘው ትጨብጠው አጣች። ህመሙን ዋጥ አድርጎ ቤተሰቡን የሚያጸናው አባት አልቻለም። ለተሻለ ህክምና በአዲስ አበባ ሆስፒታሎች ውሎ አደረ።

ተስፋ ያልቆረጠው ቤተሰብ ታማሚውን ከቤቱ መልሶ በዙሪያው ከበበ። አባወራው አሁንም ይስቃል፣ይጫወታል። ሻሌ ገጽታውን ስታይ ደስ ይላታል፣ ትጽናናለች። ከቀናት በአንዱ ግን ታሪክ ተቀየረ። የቤቱ ምሰሶ ደጉ አባወራ በድንገት ክንዱ ዛለ። በቤቱ ድንጋጤ ሆነ። በየነ ብዙ አልቆየም። ህመም ያደከመው አካሉ ለሞት እጁን ሰጠ።

ይህ ጊዜ ወሯ ለገባው ነፍሰጡሯ ሻሌ በእጅጉ የከፋ ሆነ። የልጅነት ባሏን ሞት በነጠቃት ማግስት ቤቷ ቀዘቀዘ። ይህኔ አብሯት የኖረው ብርታት ጥንካሬዋ ሲክዳት ተሰማት። ትዝታው፣ ደግነቱ አይዞሽ ባይነቱ በፊቷ ተመላለሰ። ውስጧ እንደ አገዳ ተሰበረ። በዕንባ የማትወጣው፣ በጭንቀት የማትዘልቀው ኀዘን ዋጣት።

ከቀናት በኋላ ሻሌ በሰላም ሴት ልጅ ወለደች። ይህ ጊዜ በዕንባና ሳቅ፣ በብርሃንና ጨለማ ስሜት የተደበተችበት ነበር። የአራስ ቤቷን ቆይታ በሯን ዘግታ ባሳለፈች ጊዜ የእስከዛሬውን አስታወሳ በትኩስ ዕንባ ታጠበች። አሁን ስትወልድ የሚያርሳት፣ የሚያጎርሳት ባሏ ጎኗ የለም። እሷን የሚጽናኑ ቃላት የጠፉ እስኪመስሉ በብቸኝነት አነባች … አነባች… አነባች..።

ሕይወት እንደገና…

እነሆ ! እነዛ ፈታኝ ጊዜያት በአይረሴ ትዝታዎች ተጠቅልለው በሌሎች አዲስ ቀናት ተተኩ። ሻሌ አሁን ልጇን በጀርባዋ ፣ የባሏን ትዝታ በልቧ አኑራ ርምጃ ጀምራለች። ትንሸዬዋ ስጦታ ለእሷ የመጨረሻ መታሰቢያዋ ናት። በእርሷ ጥንካሬን ታያለች፣ ቃልኪዳኗን ታጠብቃለች፣ ርምጃዋን ታፈጥናለች። ሻሌ ህፃኗን ‹‹ሴና›› ስትል ሰይማታለች። ‹‹ሴና›› ያለፈ ታሪክ እንደማለት ነው።

አዎ! አሁን ፈታኙ የታሪክ ጉዞ በፈተናዎች አልፏል። ከዚህ በኋላ ሻሌ በአዲስ መንፈስ በልዩ ጥንካሬ ሕይወትን ልትጀምር ተነስታለች። ዛሬን እንደትናንቱ ‹‹ልሙት፣ ግደለኝ›› ስትል ወደ ፈጣሪዋ አትጮህም። ይህ እንዳይሆን የሟች ባሏ ጅምር ሥራዎች ቃልኪዳኗ ናቸው። ከዚህ በኋላ ከፍጥነቷ፣ የሚመልስ ከሃሳቧ የሚገታት የለም። በየአፍታው እሱን እያስታወሰች ውስጧን ‹‹አይዞኝ›› ትላለች። መለስ ብላም ባሏን በምናብ እያወጋች ‹‹አይዞህ ብቻዬን አይደለሁም›› ትለዋለች። ክንደ ብረቷ ሻሌ ሁሌም ጥንከሬዋ ከእሷ ነው። ውጥኖቿን ልትቋጭ ቆርጣ ተነስታለች። በዚህ ስሜት በአጭር ጊዜ ቪላ ቤቷን ገንብታ ጨርሳለች።

ቀድሞ ሰፊ ጊቢዋ በተከረከሙ የጽድ ዛፎች የተሞላ ነበር። በውበቱ ይማረኩ የነበሩ ብዙዎች ሰርጋቸውን ደግሰውበታል፣ ፎቶግራፍ ተነስተውበታል። ዛሬ ግን ይህ ታሪክ ተቀይሮ ሥፍራው የአትክልትና ፍራፍሬ እርሻ ሆኗል።

ሻሌ የዕለት ትጋቷ እናትነቷን አላስጣለም። ሁለት ህጻናት ልጆቿን አቅፋ እያዘለች ከሥራዋ ትገኛለች። የሰብል፣ የእርሻ ውጤቷ ፣ የአትክልት ፍራፍሬ ምርቷ፣ የእጅ ጥበቧ ፍሬማ መሆን ይዟል። እነዚህ ተግባራት ዓይነ ግቡ መሆናቸው በርካቶችን እየሳበ ነው። የወይዘሮዋ ብርታት በጠንካራ ሴት አርሶደሮች ተርታ አሰልፎ ለአድናቆት አድርሷታል፣ ለሽልማት አብቅቷታል።

የሻካራ እጆች ፍሬ ሽልማት …

በሻሌ ሳሎን ከባለቤቷ ፎቶ አጠገብ በክብር የተቀመጡ ዋንጫና ሜዳሊያዎች ዓይን ይስባሉ። እነዚህ ሽልማቶች የሻካራ እጆች ውጤት ናቸው። ከሽልማቶቹ ጀርባ የላብና ድካም ወዝ ታትሞባቸዋል። የብርታት፣ ጥንካሬ ዐሻራ ደምቆባቸዋል። ከሜዳሊያዎቹ አንዱ ባለቤቷ በሕይወት እያለ በጤና ኤክስቴንሽን በ2002 ዓ.ም ከኦሮሚያ ክልል የተሸለመችው ነው።

ይህ መነሻ ብርታት ሆኗት ሌሎችን ሜዳሊያዎችና የዋንጫ ሽልማቶችን አክላለች። አንደኛው ዋንጫ ከፌዴራል መንግሥት በ2008 ዓ.ም የተበረከተላት ነው። ‹‹የአፍሪካ ባዮጋዝና ኮንፍረንስ፣ የኦሮሚያ ክልል የባዮ ጋዝ ማብላያ አርአያ›› የሚል ጽሁፍ ታትሞበታል።

ሻሌ ለበርካቶች ብርታት ሆናለች። ማንም ከእርሷ ደርሶ ጥንካሬዋን ቢሻ ፣ልምዷን ቢቀስም ተሞክሮዋን ለማጋራት አትሰስትም። በተለይ ሴቶች እንደእሷ ክንደ ብርቱ ቢሆኑላት ምኞቷ ነው። ትናንትን በትጋትና በፈተናዎች መሀል ያለፈችው ሻሎ ስለ ልጆቿ ነገ በብዙ ታስባለች። እሷ አባታቸው በሕይወት ሳለ ያስብ የነበረውን ዕቅድ ከግብ ለማድረስ እየተጋች ነው።

በጨዋነት ተኮትኩተው ያደጉት ልጆች ታዛዦቿ ናቸው። ከቃሏ ዝንፍ አይሉም። የምትላቸውን ይሰማሉ። በእሷ መንገድ ይጓዛሉ። አሁን ልፋቷ ፍሬ ይዞላታል። ልጆቿ ለቁምነገር ደርሰዋል። የመጀመሪያ ልጇ ከዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን አጠናቆ ሥራ ጀምሯል።

አሁን ላይ ለልጇ የተሻለ ዕውቀት ብታስብ ከመቀነቷ አቅም ከፍላ እያስተማረችው ነው። ሌሎች ልጆቿም በዩኒቨርሲቲ እንዲማሩ የአቅሟን እያደረገች ነው። ትንንሾቹም ከትምህርታቸው እንዳይታጎሉ ሁሌም ከጎናቸው ናት።

ሻሎ በባለሙያዎች ዓይን …

ጅብሪል መኮንን በሂጦሳ ወረዳ የግብርና ባለሙያ ነው። በሻቂ ወረዳ ያለፉትን ዓመታት ከሻሌ ጋር የመሥራት አጋጣሚ ነበረው። ባለሙያ ነውና እሷን መሰል አርሶ አደሮች ሊያገኝ ግድ ይለዋል። እሱ ስለ ሻሌ ያለው አመለካከት ግን ከሌሎች ተጠቃሚዎች ሁሉ ይለያል። እሷን የሚገልጻት ጥንካሬና ብርታቷን አስቀድሞ ፣ሥራና ውጤቷን አክብሮ ነው።

ይህች ብርቱ ገበሬ ሁሌም የግብርና ባለሙያዎች የሚነግሯትን ለመተግበር የፈጠነች፣ ሠርታ ለማሳየትም የተጋች ናት። ጅብሪል እንደሚለው ሻሎ በአትክልትና ፍራፍሬ በተለይ በአቦካዶ ምርት የራሷን ጥረት አክላ መሥራቷ ለሌሎች ጭምር አርአያ ያደርጋታል። ወደፊት ይህን ምርት በሰፊው ከያዘች የሚገኘውን ገቢ ወደባንክ በመቀየር ቀጣይ ፕሮጀክችን ማስፋት ይቻላታል።

ሻሎ የወረዳው ሞዴል አርሶ አደር ነች፣ ነገን ከፍ ብላ እንድትወጣ የመንግሥትና የሌሎችም አጋርነትን ትሻለች። ለዚህ ተግባራዊነት እሱን ጨምሮ ሌሎች የግብርና ባለሙያዎች ወደ ኢንቨስትመንቱ እንድትገባ ተጨማሪ ክንዶች ሊሆኗት ዝግጁ ናቸው።

ስለ ነገ…

ሻሌ ከባለቤቷ የተለየችባቸው ያለፉት ሰባት ዓመታት እንደ ስለት ሞርደዋታል። ከነበረችበት ፈተና በተሻገረች ጊዜ ራሷን ከጥንካሬ ፣ ከብርታት መንገድ አግኝታዋለች። ክንደ ብርቱዋ ሻሌ ዛሬም ዕቅዷ የሰፋ ፣ ሃሳቧ የበዛ ነው። ስለ ሥራ ካሏት እጇን አታጥፍም፣ ፊቷን አታዞርም። የትናንቱን በተሻለ መስመር ተክታ ፍሬያማ መሆንን ትሻለች።

የሻሎ ነገ በምኞት ብቻ አልተከለለም። ሃሳቧ ዕውን እንዲሆን ውጥኖቿን አስፍታለች። ያለችበት ቦታ ለዋናው መንገድ ቅርብ በመሆኑ ሆቴል ብትከፍት ለብዙዎች እንደሚበጅ ታውቃለች። መዝናኛና ሌሎች ተመሳሳይ ፕሮጀክቶችም የወደፊት ዕቅዶቿ ናቸው። ይህ ይሆን ዘንድ የእሷ ጥረት ብቻውን በቂ አይደለም። በሙያ፣ በሃሳብና በገንዘብ ድጋፍ የሚሰጧትን ትሻለች።

እንዲህ ከሆነ እሷ ብቻ ሳትሆን አካባቢ ፣ አገርና ሕዝብ ይጠቀማል። ክንደ ብርቱዋ ሻሎ ዛሬም እንደ ስሟ ስያሜ ሃሳቧ ደማቅ ብርሃን ነው። በዚህ ብርሃን ስንፍናን የማጥፋት፣ ሥራን የማስፋት ዓላማን ሰንቃለች። ሻሎ ፈተና ያልሰበራት፣ ችግር ያልበገራት ልበ ሙሉዋ ፣ እጀ ብረቷ ገበሬ።

አዲስ ዘመን የካቲት 29 /2016 ዓ.ም

Recommended For You