የኅብረት ሥራ ማህበራት ሪፎርምን ወደ ሙሉ ትግበራ ለማስገባት እየተሠራ ነው

አዳማ፦ የኅብረት ሥራ ማህበራት ሪፎርምን ወደ ሙሉ ትግበራ ለማስገባት እየተሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የኅብረት ሥራ ማህበራት ሪፎርም የተሳለጠ እንዲሆን የፌዴራልና የክልል የብልጽግና ፓርቲ አመራሮችን ግንዛቤ ማስጨበጫ መርሀ ግብር ትናንት ተካሂዷል።

በመርሀ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌታቸው መለሰ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ማህበራቱ በሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ ለማስቻል ሀገር አቀፍ የኅብረት ሥራ ማህበራት ሪፎርም መርሀ ግብር ተዘጋጅቶ ወደ ሙሉ ትግበራ መግባት የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ።

ማህበራቱ አባሎቻቸውን በዘላቂነት ተጠቃሚ እንዲያደርጉና በሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ ያስፈልጋል ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ይህ እንዲሆን ለማስቻል ሀገር አቀፍ የኅብረት ሥራ ማህበራት ሪፎርም መርሀ ግብር ተዘጋጅቶ ወደ ሙሉ ትግበራ መግባት የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል።

ለሀገሪቱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወሳኝነት ላለው ለኅብረት ሥራ ማህበራት ሪፎርም ውጤታማነት ከፌዴራል እስከ ወረዳ በየደረጃው ያሉ የብልጽግና ከፍተኛ አመራሮች የሚያደርጉት የድጋፍና ክትትል ሥራ አይተኬ ነውም ብለዋል፡፡

በአጭር ጊዜም ቢሆን እስካሁን ባለው ተሞክሮ ለሀገሪቱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወሳኝነት ላለው ለኅብረት ሥራ ማህበራት ሪፎርም ስኬታማነት ከፌዴራል እስከ ወረዳ በየደረጃው ያሉ የብልጽግና ከፍተኛ አመራሮች የሚያከናውኑት የድጋፍና ክትትል ሥራ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ኮሚሽነሩ ጠቁመው፤ አመራሩ የሚያደርገው ድጋፍና ክትትል ለሪፎርሙ ውጤታማነት አይተኬ በመሆኑ በትኩረት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ኮሚሽነሩ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጀምሮ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በሚባል ደረጃ በዘርፉ ሪፎርም ማምጣት በትኩረት ሊሠራበት የሚገባ ወቅታዊ አጀንዳ መሆኑን ግንዛቤ እንዲፈጠር መደረጉን ጠቅሰው፤ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከከፍተኛ አመራር እስከ ቀበሌ አመራር እንዲሁም ለባለድርሻ አካላት ጭምር የግንዛቤ ማስጨበጫ ተሰጥቷል።

በዚህም በከተማ አስተዳደሩ የኅብረት ሥራ ማህበራት መረጃ የመሰብሰብና የመተንተን ሥራ፣ የአደረጃጀት አዲስ ፍኖተ ካርታ የማዘጋጀትና በገጠር ደረጃ በክላስተር ኅብረት ሥራ ማህበራትን መልሶ የማጠናከር ተግባር ተከናውኗል ብለዋል።

በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል በየደረጃው ላሉ የብልጽግና ፓርቲ አመራሮችና ለተመረጡ ኅብረት ሥራ ማህበራት አመራር አካላት በሪፎርም ትግበራው ዙሪያ የግንዛቤ ፈጠራ ንቅናቄ መደረጉን አውስተው፤ በተፈጠረው ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ በክልሉ ኅብረት ሥራ ማህበራትን በደረጃ የመለየት ሥራና በሥራ ላይ የሌሉትን የመሰረዝ ሥራ ከመከናወኑ ባለፈ በፌዴሬሽንና ዩኒየኖች የቦርድ አመራር ውስጥ አማካሪ ባለሙያዎች እንዲካተቱ በማድረግ ለሌሎች ክልሎች አስተማሪ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርና የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ለሪፎርም ሥራው ልዩ ትኩረት በመስጠት ባከናወኑት የድጋፍና ክትትል ሥራ የተመዘገቡ ውጤቶች እንደመልካም ተሞክሮ የሚወሰድ ናቸው የሚሉት ኮሚሽነሩ፤ ይህንን መልካም ተሞክሮ ሌሎች ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ትምህርት የቀሰሙበትና የሪፎርም ትግበራ ሰነዶችን ወደ አካባቢያቸው ነባራዊ ሁኔታ በመቀየር ወደ ሥራ ለመግባት በሂደት ላይ መሆናቸውን አመላክተዋል።

የሀገር አቀፍ የኅብረት ሥራ ማህበራት ልማትና እድገት ሪፎርም ንቅናቄ ታህሳስ 28 ቀን 2016 ዓ.ም “ኅብረት ሥራ ማህበራት፣ ከገበያም በላይ!” በሚል መሪ ሃሳብ ይፋ መደረጉ ይታወሳል።

ሶሎሞን በየነ

አዲስ ዘመን  የካቲት 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You