የጎጃሙ ወጣት
ይርጋ ባዘዘው፣ የተወለደው በጎጃም ዱርቤቴ በሚባል አካባቢ አቸፈር ወረዳ ነው። ከፊደል ጋር ትውውቅ የጀመረው አያሌው መኮንን በሚባል ትምህርት ቤት ሲሆን፤ ሲወለድ ጀምሮ ቆሞ መሄድ አይችልም። አካል ጉዳተኛ ስለነበር ትምህርት ቤት ሲሄድ በ‹‹ሽኩኔታ›› እየተመረኮዘ ነበር። ወደ ባህርዳር የመጣው 1977 ዓ.ም ገና በልጅነቱ ነበር።
ይርጋ ገና በልጅነቱ ነበር የክራር ድምፅ ሲሠማ ፍላጎቱ ይንር፤ ልቡ ስውር ይል ነበር። እናም ክራር የመማር ፍላጎት አደረበት። ለእናቱ ፍላጎቱን ሲነግራቸው ብዙም ደስተኛ አልሆኑም። ደግሞ የአዝማሪ ሥራ ምን ይሠራልሀል እያሉ ይነቅፉት ነበር። እርሱ ግን የክራር ድምፅ በልቡ ላይ ቤት ሠራ። በኋላም በአካባቢው ከሚገኙ ቁሳቁስ የራሱን ክራር ሠርቶ ይጫወት ጀመር።
በአካባቢ ደግሞ አስማረ አዲስ የሚባሉ ሰው ክራር ይጫወቱ ነበር። ይርጋም ግን ሥራቸው ሆኖ የጣታቸውን እንቅስቃሴ ይመለከታል። እግራቸው ሥር ቁጢጥ ብሎ በሚገባ ይከታተላል። በልጅነቱ አካል ጉዳተኛ ቢሆንም የሚፈልገውን ከማድረግ አላገደውም።
ይርጋ በሂደት ክራር አሳምሮ መጫወት ጀመረ። ለምን ብለው ሲቃወሙ የነበሩ ቤተሰቦቹ ደስተኛ እየሆኑ መጡ። በተለይም ደግሞ አባቱ በሥራው ይመሰጡ ጀመር። እናቱም በሂደት የይርጋን ሥራ ከማናናቅ ወደ ማድነቅ ተሸጋገሩ፤ በችሎታውም ተደመሙ።
ይህን ችሎታውን ተገን በማድረግም በሂደት በዱርቤቴ የወረዳ ኪነት ተቀላቀለ። ከዚያም የባህርዳር ዙሪያ ወረዳ 1978 ዓ.ም ኪነት አባል ሆነ። ያኔ በግምት10 ዓመት ይሆነኛል ይላል። በልጅነቱ ቀጫጫ ነበር። ግን በዚያ ሰውነቱ ጭንቅላቱን ግራ ቀኝ እየነቀነቀ ክራሩን ሲጫወት የብዙዎችን ቀልብ በትዝታ ስቅዝ አድርጎ ይይዝ ነበር። በትምህርቱ ከስምንተኛ ክፍል አልዘለለም።
በወቅቱ የወረዳዎች ኪነት ከወረዳዎች ጋር ይወዳደሩ ነበር። እናም ይልማና ዴንሳ፣ ሜጫ ወረዳ፣ አቸፈር እና ባህርዳር ዙሪያ ወረዳ ውድድር አደረጉ። በዚህም ላይ ይርጋ ከባልደረቦቹ ጋር አቸፈር ወረዳን ወክሎ ተወዳደረ። ከዚያም እርሱ የተካተተበት ወረዳ አሸናፊ ሆነ። በዚህም ጊዜ ሞራሉ የበለጠ ተጠናከረ፤ ፍላጎቱም ናረ።
በቤት ውስጥም ልምምዱን ገፋበት። በተለይም አዲስ ዘፈን በወጣ ቁጥር በራሱ ቅኝት አስተካክሎ ለመጫወት ጉጉቱ ጨመረ። በወቅቱ የኤፍሬምን ‹‹በጣና አቋርጠሽ ጣና ላይ›› የሚለውን ዘፈን አሳምሮ ይጫወት ስለነበር የብዙዎችን ትኩረት አግኝቶ ነበር።
ወደ ኪነት አለም
ይርጋ የበለጠ በሙዚቃው እየተሳበ መጣ። በወቅቱ ባህርዳር ላይ ቴክስታይል ኪነት እና ግሽ አባይ ኪነት የሚባሉ ሁለት የኪነት ቡድኖች ባህርዳር ነበሩ። በዚህ ላይ ደግሞ ወንድሙ ባህርዳር ይኖር ስለነበር ጓዙን ጠቅሎ ወደ ባህርዳር ከተመ።
‹‹በባህርዳር ግሽ አባይ ኪነት ቡድን በድምጽ እና ክራር ተወዳድሬ አንደኛ ወጣሁ›› ይላል። ግን በወቅቱ ዊልቸር ስላልነበረው ከቡድን አጋሮቹ ጋር እንደልብ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ አልቻለም። መሬት ለመሬት በሽኩኔታ ነበር የሚንፏቀቀው።
ጥሩ ዕድል ቢገጥመውም ከኪነት ቡድኑ አባላት ጋር ለመሥራት እንቅፋት ሆነበት። በመጨረሻም በግሉ መንቀሳቀስ ጀመረ። እያለ እያለ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሮ ህይወቱን በዚያው ይመራ ጀመር።
በእርግጥ በወቅቱ ሃሳቡ ትልቅ ነበር። አንቱ የተባለ ሙዚቀኛ መሆን ይፈልግ ነበር። ግን ያሰበውን ሁሉ ለማሳካት አልቻለም። አካል ጉዳተኛ ከመሆኑ በተጨማሪም ሃሳቡን ተረድቶ የሚያግዘው አካል በማጣቱ ሥራው ከባህርዳር ሳይወጣ፤ እርሱም ከባህርዳር ሳይርቅ እዚያው በዚያው እየንቀሳቀሰ ኑሮውን ሊገፋ ተገደደ።
ዓመት በዓል ሲሆን ወደ እናቱ ቤት እየሄደ ይጠይቃቸው ነበር። እናቱ ግን ከአጠገባቸው እንዲርቅ አይሹም ነበር። ‹‹ተው ልጄ ከእኔ ዘንድ ሁን ብለው›› ይማፀኑታል። እርሱ ግን እኔ እራሴን ማውጣት አለብኝ ሲል እናቱን በሃሳብ ያሸንፋል። እንዲህ እያለ እርሱ ከክራር፤ ክራርም ከእርሱ ጋር በባህርዳር ከተሙ።
ሦስት ወር በአዲስ አበባ
1999 ዓ.ም ካሴት ላውጣ ብሎ ወደ አዲስ አበባ አመራ። እናም ሙልጌታ ከሚባል ሙዚቃ አቀናባሪ ጋር ተገናኙ። ግን ብዙም ያሰበው ሊሳካለት አልቻለም፤ ነገሮች ባሰበው መንገድ ሊጓዙ አልቻሉም። በወቅቱም ስለአዲስ አበባ እና አዲስ አበቤዎች ኑሮ ብዙም ግንዛቤ አልነበረውም፤ ከሰዎችም አይተዋወቅም ነበር።
በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በሚተላለፈው ‹‹አለቤ ሾው›› ቀርቦ ነበር። ችሎታው የተመለከተ አንድ ሰው ግን በወቅቱ ሁለት ሺህ ብር አግዞት ነበር። ግን የዕለት ችግሩ ብሶበት ብሩን ከምንም ሳያደርሰው እንደጨረሰው ያስታውሳል።
በዚህም ተስፋ አልቆረጠም። አዲስ አበባ ጎጃም በረንዳ ለሦስት ወራት ቆይቷል። የህዝብ ሙዚቃም ይጫወት ነበር። በዚህ ጊዜ ‹‹ብዙዬ ሙዚቃ ቤት›› ከሚባል ድርጅት ጋር ዘፈኑን ሠራ። በወቅቱ ካሴቱም በሚገባ መቸብቸቡን ይናገራል። ይሁንና አሳታሚው ከአምስት ሺህ ብር ውጭ ምንም አልሰጠውም። ይህን ሲያደርግ የነበረው በህዝቡ ዘንድ ለመታወቅ ካለው ጉጉት አንጻር እንጂ ገንዘብ መሰረት አድርጎ እንዳልነበር ይናገራል።
ለሶስት ወራት በጎጃም በረንዳ ተከራይቶ ይኖር ስለነበር በእጁ ላይ የነበረውን ብር ጨረሰ፤ ከዚያም ወደ ባህርዳር በመመለስ፤ በግሉ የባህርዳር ከተማን 360 ዲግሪ እያካለለ ሕይወቱን ይገፋ ጀመር።
ወደ ትዳር
ሰው ብቻውን ይኖር ዘንድ አልተፈቀደም የሚለውን የመፅሐፍ ቅዱስ ቃል አከብራለሁ ይላል። በሥራ አጋጣሚ ዛሬ የልጆቹ እናት የሆነችውን የግራ ጎኑን አግኝቷል። አንድ ወንድ እና አንድ ሴት ልጅ አለው።
የመጀመሪያ ልጁ ሰባት፤ሁለተኛው ደግሞ ሦስት ዓመት ሞልቷቸዋል። ይርጋ ብዙ ነገሮችን ያስባል። አንድ ወንድ እና አንድ ሴት ልጅ አለው። አሁን የሚኖረው በቀበሌ ቤት ውስጥ ነው። መፀዳጃ ቤቱ የጋራ በመሆኑ እንደ ልቡ መጠቀም አይችልም። የጫማ ሶል እየሰፋ እያዞረ ያከፋፍላል።
ክራር ከመጫወት ባለፈ ሌላ የእጅ ሙያ አለው። እርሱ እንዲህ እየኖረ፤ ሌሎች የቤተሰቡን አካላት ለማኖር ይፈልጋል።
ሙዘቃን በልመና
ይርጋ ዛሬም ቢሆን ተስፋ አይቆርጥም። በበርካታ መድረኮች ለመጫወት ቢፈልግም በርካቶች ፊት አይሰጡትም። ዕድልም በሯን እንደዘጋችበት ይናገራል። በየጊዜው በባህርዳር ከተማ በርካታ ባዛሮች የሚካሄዱ ቢሆንም፤ ይርጋ ስለመኖሩም ትዝ የሚላቸው የሉም።
እርሱ ግን እንደምንም አፈላልጎ ይደርስበታል። እባካችሁ አጫውቱኝ ብሎም ይለምናል። ጥቂቶች ይሁንታቸውን ይለግሱታል። በርካቶች ግን ይርጋ ከመድረክ ላይ ሆኖ በመርዋ ድምፁና ከልጅነቱ ጀምሮ በሚወዳት ክራሩ አድማጭ ተመልካችን ዘና እንዲያደርግ ፍላጎት የላቸውም።
ይርጋ ሙዚቃን መድረክ ላይ ለማቅረብ ለምኖ ነው። በእርሱ እምነት ግን ብዙዎች ለምነውኝ እንጂ እኔ ለምኜ ወደ መድረክ ባልመጣሁ ሲል በቁጭት ይንገበገባል። የሆነው ሆኖ እርሱን ከሙዚቃ፤ ሙዚቃንም ከይርጋ መነጠል ከባድ ስለመሆኑ ይናገራል። ሙዚቃ ከገንዘብ ባለፈ ትርጉም አለው፤ ለይርጋ።
ነገስ?
ይርጋ በሚኖርበት ቤት ውስጥ ባህላዊ መጠጦች ይሸጣል። ማታ ማታ ክራር ይጫወታል። ሥራ ቀዝቀዝ ሲል በምሽት ግሮሰሪ ለግሮሰሪዎች እየተሽከረከረ ሰዎችን ያዝናናል። አንዳንዶች ደግሞ ደውለው እነርሱ ባሉበት ይጠሩታል። ባሉበት ቦታ ሄዶ ያዝናናቸዋል። የተጋነነ ባይሆንም ይሸልሙታል። ግን ይህ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሮው ፈቅ ማለት አልቻለም።
ይርጋ ለበርካታ አካል ጉዳተኞች አርዕያ መሆን ይፈልጋል። አካል ጉዳተኛ ሆኖ መለመን በእጅጉ ይኮንናል። አካል ጉዳተኛ ማለት ያለመስራት ሳይሆን፤ ለስራ ምቹ ሁኔታን መፈለግ ነው ይላል። በኢትዮጵያን አይዶል ተወዳድሮ ባህርዳርን በአረንጓዴ ካርድ አጥለቅልቆ ነበር።
በወቅቱም ወደ ሙዚቃው በሰፊው እንዲገባ እገዛ እንደሚያደርጉ በርካታ ሰዎች ቃል ገብተው እንደነበር ያስታውሳል። ግን ከመናገር የዘለለ ምንም አልፈየዱትም።
እርሱ ግን አሁንም ቢሆን ረፈደ እንጂ አልመሸም ይላል። በውስጡ የሚንቀለቀለውን የሙዚቃ ፍላጎት ለመላው ኢትዮጵያን ሊያበረክት ይሻል። ችሎታውና ፍቅሩ እያለኝ በሙዚቃው ዓለም ጎላ ብዬ እንዳልወጣ እጅ አነሰኝ ሲል፤ በትካዜና በቁጭት ስሜት ይገልፀዋል።
አሁንም ቢሆን ከ‹‹ዊልቸሩ›› ላይ ተቀምጦ በክራሩ ይመሰጣል፤ ሌሎችንም ያዝናናል።
ይርጋ ብዙ ቢያስብም፤ ብዙ የሚያስበለት ሰው በማጣቱ ከሚፈልገው መንገድ ጥቂቱን ተጉዞ ረጅም መንገድ እንደቀረው ይናገራል። መንገድን ብቻውን ለመጓዝ ከብዶታል። ምንም እንኳን በርካታ ዓመታት በፈለገው መንገድ ባይኖርበትም፤ ቀሪ ዘመኑን ግን ፍሰሃ ይሆንለት ዘንድ ይመኛል። ለዚህም አጋዥ አላጣም የሚል ተስፋ ያደርጋል።
በራሱ ግጥም ይደርሳል፤ የሙዚቃ ኖታ ያነባል። ግን ሙያውን የበለጠ ለማሳደግ አጋዥ አላገኘም። ለመሆኑ ይርጋን ቀረብ ብሎ የልቡን መሻት የሚረዳው፤ ልቦናውን የሚያረጋጋለት፤ የሙዚቃ ጥሙን የሚቆርጥለት የጥበብ ሰው ማን ይሆን?
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 1/2011
ጌትነት ተስፋማርያም