ድርጅቱ ከሆስፒታሉ ውጪ ለሚገኙ ሴቶች የድጋፍ አቅርቦቱን እንደሚያሰፋ አስታወቀ

አዲስ አበባ፡- የሴቶች ጤና ድጋፍ በጎ አድራጎት ድርጅት በቀጣይ ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ውጪ ለሚገኙ ሴቶች የድጋፍ አቅርቦቱን እንደሚያሰፋ አስታወቀ፡፡

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ በማህጸንና ጽንስ ትምህርት ክፍል ሐኪሞች የተቋቋመው የሴቶች ጤና ድጋፍ በጎ አድራጎት ድርጅት ትናንት ሕጋዊ ዕውቅና ማግኘቱን አስመልክቶ መርሐ ግብር  አዘጋጅቷል።

በወቅቱ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅና በሆስፒታሉ የማህፀንና ፅንስ ክፍል ኃላፊ ወንድሙ ጉዱ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ማኅበሩ በቀጣይ የበጎ አድራጎት ተግባሩን ከሆስፒታሉ ውጪ ለሚገኙ ሴቶችም ተደራሽ ለማድረግ ይሠራል፡፡

የበጎ አድራጎት ድርጅቱ የማህጸንና ጽንስ ሕክምና አገልግሎት ለማግኘት ወደሆስፒታሉ መጥተው የገንዘብ ችግር ያለባቸውን እናቶች እየረዳ መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይ ከሆስፒታሉ ውጪ በተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስረድተዋል፡፡

አገልግሎቱን በማስፋፋት በተለያዩ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ለሚገኙ ሴቶች የማህጸን በር ጫፍ ካንሰርና በሌሎች ሴቶች ተጋላጭ በሆኑባቸው በሽታዎች ላይ የሕክምና አገልግሎት እና ሥልጠና እንደሚሰጥ አብራርተዋል።

የማህጸን በር ጫፍ ካንሰርን ጨምሮ ለሌሎች ህክምናዎች አንዳንድ እናቶች ወደ ሆስፒታሉ ሲመጡ በገንዘብ እጥረት ምክንያት ሕክምና ለማግኘት እንደሚቸሩ አንስተው፤ ድርጅቱ በአንድ ዓመት ከስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ለ70 እናቶች 150 ሺህ ብር የሚያወጣ የሕክምና አገልግሎት ሰጥቷል ብለዋል።

በመሆኑም በጎ አድራጎት ድርጅቱ የተቋቋመው በማህፀንና ፅንስ ክፍል የሚሠሩ ሐኪሞች በጋራ በመሆን ከእራሳቸው ወርሀዊ ገቢ እየተቆረጠ አቅም ላነሳቸው  ሴቶች ድጋፍ ለመስጠት ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልጸው፤ ማኅበሩ አድጎ የበጎ አድራጎት ድርጅት ሆኖ ከመንግሥት ዕውቅና ማግኘቱን አስታውቀዋል።

አሁን ላይ ድርጅቱ የሕክምና ተማሪዎች፤ ከሆስፒታሉ ውጪም መድኃኒት ቤት ያላቸውና የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት መጥተው ስለበጎ አድራጎት ማህበሩ ሰምተው የተቀላቀሉ በጎ ፈቃደኞችን ጨምሮ ከአንድ ሺህ በላይ አባላትን መያዙን አስረድተዋል።

በቀጣይም ከሆስፒታሉ ውጪ የሚገኙ ሴቶችን ጨምሮ በጤና ዘርፉ የቅድመ መከላከል ሥልጠና፣ የሙያና የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ እንደሚሠራ ተናግረዋል።

በጎፈቃደኞች የድርጅቱ አባል በመሆን ለሴቶች ጤናማነት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን  የካቲት 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You