ኢትዮጵያ የናይል ተፋሰስ ትብብርን እውን ለማድረግ ግንባር ቀደምነቷን አጠናክራ ትቀጥላለች

ኢትዮጵያ የናይል ተፋሰስ ትብብርን እውን ለማድረግ ግንባር ቀደምነቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል ተገለጸ፡፡

25ተኛው የናይል ቀን በቡሩንዲ ቡጁምቡራ እየተካሄደ ነው፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የናይል ተፋሰስ ትብብርን እውን ለማድረግ ግንባር ቀደምነቷን አጠናክራ ትቀጥላለች፡፡

የናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ ለሩብ ክፍለ ዘመን የዘለቀው ጉዞው ሲገመገም፣ በ25 ዓመታት ጥሩ ውጤቶችን አምጥቷል ብሎ መናገር እንደሚቻል ያነሱት ሚኒስትሩ፤ በተለይ በተወሰኑ የተፋሰሱ አካባቢዎች የልማት ሥራዎችን ማከናወን መቻሉን ተናግረዋል፡፡

 

ምንምን እንኳን ሕጋዊ አካልነት ባያገኝም፤ በአባል ሀገራት መካከል የውውይት ፎረሞችን በመፍጠር፣ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን በማከናወን፤ ስለተፋሰሱ ግንዛቤ በማስጨበጥና የተፋሰሱ የእውቀት ምንጭ በመሆን እያገለገለ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

አክለውም የናይል ጉዳዮችንና የትብብር አስፈላጊነትን ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ የማስተዋወቅ ሥራ በማከናወን አበረታች ሥራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል።

ናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ 25 ዓመታት ቢያስቆጥርም እስከአሁን የሽግግር መሣሪያ ብቻ ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ቋሚ ሕጋዊና ተቋማዊ ማዕቀፍ በፍጹም ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ እንዳልሆነ ያነሱት ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ፤ ቋሚ ሕጋዊ እና ተቋማዊ ማዕቀፍ የናይል ተፋሰስ አባል ሀገራት አስተዋጽኦና ተሳትፎ ቋሚና ወጥ እንዲሆንና በአባል ሀገራት የመንግሥታት መቀያየር ምክንያት ተጽእኖ ውስጥ የማይወድቅ ጠንካራ ተቋም ለመፍጠር ያግዛል ብለዋል።

እየተከበረ የሚገኘው የብር ኢዮቤልዩ በዓል አባል ሀገራት የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን በማጽደቅ ወደፊት ለመራመድ ወሳኝ ሰዓት መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያም የናይል ተፋሰስ ትብብርን እውን ለማድረግ ግንባር ቀደምነቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

የትብብር ልማትን በተመለከተ በአባል ሀገራት መካከልና በናይል ተፋሰስ የሚገኙ ሕዝቦች ከፍተኛ የመልማት ፍላጎት ቢኖርም፤ የናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ የልማት አጀንዳ ሊረጋገጥ አለመቻሉን ጠቅሰዋል።

በዝግጅት ሂደት ላይ የሚገኘው የናይል ተፋሰስ የኢንቨስትመንት ፕሮግራም የናይል ተፋሰስ ሕዝቦችን ፍላጎት ለማሟላት፤ ብሎም ሕይወታቸውን ለመቀየር መልካም አጋጣሚ መሆኑን አንስተዋል።

ካለፉት የናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ መረዳት እንደሚቻለው፤ በናይል ተፋሰስ ተጨባጭ ሁኔታ ከውጭ በሚደረጉ የፋይናንስ ድጋፎች ላይ ብቻ በመመርኮዝ ትልልቅ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን አዋጭ ሆኖ አይታይም ያሉት ሚኒስትሩ፤ የውስጥ አቅምን ተጠቅሞ ሀብት በማሰባሰብ የተዘጋጁ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን መተግበር ይገባል ብለዋል

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን  የካቲት 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You