በትግራይ ከ50 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት በመስኖ ለምቷል

አዲስ አበባ፡- በክልሉ 50 ሺህ 200 ሔክታር መሬት በመስኖ መልማቱን የትግራይ ክልል ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ አሳወቀ፡፡ ስምንት መቶ ሔክታር መሬት ላይ ስንዴ እየለማ ነው።

በቢሮው የሆርቲካልቸር ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በሪሁን አረጋዊ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በትግራይ ክልል መስኖን በመጠቀም 60 ሺህ 749 ሄክታር ለማልማት ታቅዶ እስካሁን ድረስ 50 ሺህ 200 ሄክታሩን ማልማት ተችሏል፡፡

ክልሉ መስኖን በመጠቀም አትክልት፣ ስንዴ፣ ጥራጥሬና ሌሎችም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሰብሎችን እያለማ ይገኛል ብለዋል።

ዳይሬክተሩ እንዳመለከቱት፤ በትግራይ ክልል ማልማት ከተቻለው መሬት ውስጥ አምስት ሺህ ሄክታር በቆሎ ማሳ የለማ ነው፡፡

በመስኖ ለማልማት ከታቀደው ሁለት ሺህ ሄክታር ስንዴ ውስጥም ስምንት መቶ ሄክታር ያህሉ መልማት እንደቻለም አስረድተዋል።

ክልሉ ለመስኖ ልማቱ 100 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ለገበሬዎች ለማከፋፈል አቅዶ ከእቅዱ በላይ 110 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ማከፋፈሉንም አቶ በሪሁን አስታውቀዋል።

የአርሶ አደሩን የመግዛት አቅም መዳከም ተከትሎ የፌዴራል መንግሥትና ከሌሎችም ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ድጋፍ ማድረጋቸውን ተከትሎ ክልሉ ከእቅዱ በላይ ማዳበሪያ ማከፋፈል በመቻሉ በዘንድሮው ዓመት ሻል ያለ ምርት ይጠበቃል ሲሉ አቶ በሪሁን አብራርተዋል።

በተጨማሪም ለክልሉ ሁለት ሺህ የውሃ መሳቢያ ሞተሮችን ለመግዛት አቅዶ እስካሁን ድረስም አንድ ሺህ ያህሉ ተገዝተው ለአርሶ አደሩ መከፋፈላቸውን ጠቁመዋል።

በተጠቃሚዎች ዘንድ እስከ 10 ሺህ የውሃ መሳቢያ ሞተሮችን ለመውሰድ ፍላጎት ቢኖርም በበጀት እጥረት ምክንያት እንዳልተገዛ ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል።

በክልሉ ከጦርነቱ በፊት 27 ሺህ ያህል የውሃ መሳቢያ ሞተሮች መኖራቸውን አስታውሰው፤ አሁን ምን ያህል እንዳሉና ጥቅም ላይ መዋል እንደሚችሉ ለማወቅ ጥናቶች በመደረግ ላይ እንዳሉም አንስተዋል።

አቶ በሪሁን በክልሉ ግብርናው ዘርፍ ላይ ያሉ ተግዳሮቶችንም አንስተዋል፤ በዚህም የውሃ መሳቢያ ችግርና የዘር አቅርቦትን የጠቀሱ ሲሆን፤ 14 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ለመጠቀም የታቀደ ቢሆንም እስካሁን ግን አምስት ሺህ ኩንታል ብቻ ጥቅም ላይ እንደዋለ ተናግረዋል።

460 ኩንታል ዘርም መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ለክልሉ መሰጠቱን ገልጸዋል።

ዳግማዊት ግርማ

 አዲስ ዘመን  የካቲት 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You