
አዲስ አበባ፦ በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ፈረስን ለጋሪ አገልግሎት ማዋል የሚከለክለው መመሪያ ከመጪው መጋቢት 12 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ተገለጸ፡፡
የዞኑ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሜሮን መኮንን ለኢፕድ እንደገለጹት፤ ፈረስ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ትልቅ ክብር የሚሰጠው እንስሳ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኅብረተሰቡ የሚደረግለት እንክብካቤ እየቀነሰ መጥቷል፡፡
በመሆኑም የጠፋውን የፈረስ ክብር ወደ ነበረበት ለመመለስ፣ ፈረስን ለጋሪ መጎተቻነት የሚያውሉ ዜጎች የ60 ሺህ ብር መቀጮ እንዲጣልባቸው የሚያደርግ መመሪያ ወጥቶ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሠራ ነው፡፡
ዞኑ ፈረስ ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር ያለውን መስተጋብርና ለሕዝቡ የዋለውን ውለታ መሠረት በማድረግ ያወጣው መመሪያ፣ ከዞን አልፎ በመላው ኦሮሚያ ክልል በሥራ ላይ እንዲውል ከአባገዳ አመራሮች ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
እንደ ኃላፊዋ ገለጻ፤ መመሪያው የጸደቀው መስከረም 12/2016 ዓ.ም. ሲሆን የፈረስ ጋሪን በመጠቀም በርካታ ዜጎች ሕይወታቸውን የሚመሩ መሆኑን ከግምት በማስገባት የስድስት ወር ጊዜ ተሰጥቶ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ እየተሠራና አማራጭ የሥራ እድሎችን ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
መመሪያውን ሙሉ በሙሉ ከመጋቢት 12 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ ለማድረግ ከዜጎች ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶችን በማድረግ መግባባት ላይ እየተደረሰ ነው፡፡ መመሪያው ተግባራዊ ሲሆን ድንጋጌውን ተላልፎ በሚገኝ ማንኛውም ሰው ላይ የገንዘብ ቅጣቱ እንደሚጣል ወይዘሮ ሜሮን ጠቁመዋል፡፡
ፈረስ በዓድዋ ድልም ሆነ በሌሎች አውደ ውጊያዎች ላይ ትልቅ ድርሻ እንደነበረው ያስታወሱት ኃላፊዋ፤ ሕዝቡ ከፈረስ ጋር ያለው ቁርኝት ትልቅ በመሆኑ በደስታም ሆነ በሀዘንና በጦርነት ወቅቶች ፈረስን እንደሚጠቀም ገልጸዋል፡፡
ባህላዊና ዘመናዊ የፈረስ እንክብካቤ፣ አረባብና ስፖርታዊ ጨዋታዎችን ከአካባቢው ባህል ጋር በማዛመድ ለጎብኚዎች መዝናኛነት በማዋል ገቢ ለማግኘት እየተሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በዚህ መሠረትም ከሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር 2012 ዓ.ም ጀምሮ በሰሜን ሸዋ ዞን በሰንዳፋ በኬ ከተማ በየዓመቱ የፈረስ ጉግስ ፌስቲቫል እየተካሄደ እንደሚገኝ ያወሱት ወይዘሮ ሜሮን፤ ወደፊት ፌስቲቫሉን በዞኑ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች በማስፋፋት ከአጎራባች ዞኖችና ከተሞች ጋር በጋራ በመሆን ለማካሄድ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
“ኦሮሞ ፈረስን እንደ ልጁ በማየት ነው የሚንከባከበው” ያሉት ኃላፊዋ፤ የፈረስ ታሪክና ክብርን በመመለስ ለዞኑ የቱሪዝም ገቢ ምንጭ እንዲሆን ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ቃልኪዳን አሳዬ
አዲስ ዘመን የካቲት 2 ቀን 2016 ዓ.ም