
አዲስ አበባ፡- በከተማ አስተዳደሩ በእደ ጥበባትና ፈጠራ ዘርፉ ያሉ እድሎችን አሟጦ ለመጠቀም እየተሠራ መሆኑን የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡
ቢሮው የእደ ጥበባትና ፈጠራ ዘርፎች ከቱሪዝም፣ ገቢ ከማመንጨት፣ ከሥራ እድል ፈጠራ እንዲሁም ከሀገር ገጽታ ግንባታ አኳያ ያላቸውን አስተዋጽኦ ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ በቅርቡ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የባህል ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ አስፋው ኩማ በዕለቱ እንደገለጹት፤ በእደ ጥበባትና ፈጠራ ዘርፉ ያሉ ሰፊ እድሎችን አሟጦ ለመጠቀም እየተሠራ ነው፡፡
የእደ ጥበባትና የባህላዊ ፈጠራ ልማትን ለቀጣይ ትውልድ ለማስረከብ የተለያዩ የክህሎት ስልጠናዎች ተሰጥተዋል ያሉት አቶ አስፋው፤ በዘርፉ የሚስተዋሉ የተለያዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሠራ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
በዘርፉ የተመረቱ ምርቶች የገበያ ችግር እንዳይገጥማቸው ቢሮው የተለያዩ አውደ ርዕዮችን በመክፈት ሲያስተዋውቅ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡
እንደ አቶ አስፋው ገለጻ፤ የእደ ጥበባትና የባህላዊ ፈጠራ ልማት ዘርፍ ከሥራ እድል ፈጠራ፣ ቱሪዝምን ከማነቃቃት እንዲሁም የማንነት መገለጫ ከመሆን አንጻር ሰፊ ጠቀሜታ አለው፡፡
ዘርፉ ካለው ሰፊ እድሎች አኳያ እንዴት መጠቀም ይቻላል እንዲሁም ያሉ ተግዳሮቶችስ ምን ምንድናቸው በሚሉ ጉዳዮች ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በተደረገው ውይይት ተገቢውን ግብዓት መሰብሰብ እንደተቻለም ነው አቶ አስፋው የተናገሩት፡፡
“የእደ ጥበብና ፈጠራ ዘርፎች ያላቸው ፋይዳና እየገጠሙት ያሉ ተግዳሮቶች” በሚል ርዕስ መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት ኤፍሬም አሰፋ (ረዳት ፕሮፌሰር) በበኩላቸው፤ ዘርፉ ለቱሪዝምና ለሀገር ገጽታ ግንባታ እንዲሁም ለማንነት መገለጫ የሚጫወተው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም ብለዋል፡፡
በዘርፉ ላለው ሰፊ ሀብት የተለየ ትኩረት በመስጠት አሟጥጦ መጠቀም አስፈላጊ ነው ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ኤፍሬም፤ ዘርፉ የገቢ ምንጭ ከመሆን ባሻገር የቱሪስትን የቆይታ ጊዜ ለማራዘምና ተጨባጭ ለማድረግ ያለው ሚና ከፍተኛ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
እንደ ረዳት ፕሮፌሰር ኤፍሬም ገለጻ፤ ማህበረሰቡ ለእደ ጥበብ ዘርፉ የሚሰጠው የተሳሳተ አመለካከት፣ የፋይናንስ አቅርቦት እጥረት፣ በቂ የክህሎት ስልጠና አለመስጠት፣ ገቢን ብቻ ታሳቢ ያደረጉ ምርቶች ማምረት ለዘርፉ አለማደግ ዋና ዋና ማነቆዎች ናቸው።
ዘርፉን በዘመናዊ መልኩ በመምራት ባለሙያዎችን የሚያበቁ የሙያ ማዕከላትን በማስፋፋት እንዲሁም የገበያ ትስስር እንዲፈጠር በማስቻል ተጠቃሚነትን ማሳደግ እንደሚቻል ምክረ ሃሳበባቸውን አቅርበዋል፡፡
“ባህሎቻችንን ማወቅ፤ ስብራቶቻችንን መጠገን” በሚል መሪ ሃሳብ በተዘጋጀው በዚህ የውይይት መድረክ የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የሥራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት፣ አባቶች የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል። ለሀገር በቀል እውቀቶች ተገቢውን እውቅና መስጠት እንደሚገባም በውይይት መድረኩ ተመላክቷል።
ልጅዓለም ፍቅሬ
አዲስ ዘመን የካቲት 2 ቀን 2016 ዓ.ም