
አዲስ አበባ፦ “የግብርና ምርት አምራችና አስመራች ግንኙነት” መመሪያ በገበያ ትስስርና በምርታማነት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን እንደሚቀርፍ ተገለጸ።
መመሪያውን እውን ለማድረግ ግብአት ማሰባሰብን ዓላማ ያደረገና በግብርና ምርት ማቀነባበር ዘርፍ የተሰማሩ 40 የሚደርሱ ድርጅቶች የተሳተፉበት የውይይት መድረክ ትናንት ተካሂዷል፡፡ የውይይት መድረኩን የግብርና ሚኒስቴርና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በጋራ አዘጋጅተውታል።
በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ኢንቨስትመንትና ምርት ግብይት መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ደረጄ አበራ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ መመሪያው የግብርና ምርትን ጥራት፣ የአመራረት ቅልጥፍናንና ተወዳዳሪነት እንዲሁም የግብርና እና አግሮ- ኢንዱስትሪ ተመጋጋቢነት በማሳደግ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርን እውን ለማድረግ ወሳኝ ነው።
መመሪያው የግብርና ምርት አምራቾች ለገበያ የሚሆን የግብርና ምርቶችን ወደ ማምረት እንዲሸጋገሩ ያደርጋል ያሉት አቶ ደረጄ፤ ይህም የግብርና ምርቶችን ከሚያዘጋጁ፣ ከሚያቀነባብሩ፣ እሴት ከሚጨምሩ አግሮ ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም ከትላልቅ ገዥዎች ጋር ቀጣይነት ያለው የገበያ ትስስር ይፈጥራል ብለዋል።
በሥራ ላይ ያሉት ሕጎች የግብርና ምርት ውልን ልዩ ባሕሪያት በተሟላ መልኩ የማያስተናግዱ በመሆናቸው የግብርና ምርት አምራችና አስመራች ግንኙነትን ለመወሰን የወጣ አዋጅ ጸድቋል ያሉት አቶ ደረጄ፤ መመሪያው የግብርና ምርት ውልን በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን እንደሚያሳድግ ገልጸዋል።
መመሪያው የግብርና ምርት አምራችና አስመራች ግንኙነትን ለመወሰን የወጣውን አዋጅ የሚያስፈጽም ነው ያሉት አቶ ደረጄ፤ መመሪያው ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ሲሆን የእውቀትና ክህሎት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የገበያ ትስስር የሚፈጠርበት እድልን ያመቻቻል ብለዋል።

ከደብሊው ኤ የዘይት ፋብሪካ የመጡት አቶ አንተነህ አሰጌ በበኩላቸው፤ ከዚህ በፊት የግብርና ምርት አምራችና አስመራች ግንኙነትን ለመወሰን የወጣ አዋጅ ባለመኖሩ በአስመራችና በአምራች መካከል ሰላማዊ ግንኙነት አልነበረም ብለዋል።
ይህ ደግሞ በርካታ ደላላዎች በግብይት ሰንሰለቱ ላይ እንዲሳተፉ ከማድረጉም ባለፈ የግብርና ምርት አምራቾችና አስመራቾች መካከል ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳይኖር እና የምርት ብክነት እንዲፈጠር በማድረግ የኑሮ ውድነትም ያባብሳል ያሉት አቶ አንተነህ፤ የአምራች እና የአስመራች ግንኙነት በተሟላ የሕግ ማዕቀፍ የሚመራበት ሥርዓት በመዘርጋቱ የተሸለ ሥራ እንዲሠራ ያግዛል ብለዋል፡፡

የጎልደን ፉል ዘይት ፋብሪካ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ትግስት አለማየሁ በበኩሏ፤ መመሪያ በአምራቹና በአስመራቹ መካከል እምነትን ይፈጥራል። ምርትና ምርታማነትን ያሳድጋል። ከዚህም ባለፈ ዘላቂ ኢንቨስትመንት እንዲኖር እና ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በሀገር ውስጥ እንዲተኩ በማድረግ የውጭ ምንዛሪን ይቀንሳል ብላለች።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን የካቲት 2 ቀን 2016 ዓ.ም