
አዲስ አበባ፡- ጥገና የሚያስፈልጋቸው ዓለም አቀፍ ቅርሶችን የማደስና የመጠበቅ ሥራ እየሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
በባለስልጣኑ የቅርስ ጥበቃና ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሀብታሙ አብርሃ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጡት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት እድሳት እየተደረገላቸው ከሚገኙ ቅርሶች መካከል አንዱ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ሲሆን፤ ይህም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በተገኘ ድጋፍ እየታደሰ ይገኛል፡፡
የእድሳት ፕሮጀክቱን ባለስልጣን መስሪያ ቤት በኃላፊነት ይዞት እየተከታተለው ይገኛል ያሉት አቶ ሀብታሙ፤ በዘለቄታዊነት በቅርሶቹ ላይ ያሉትን ክፍተቶች ለመሙላትና ቅርሱን ተንከባክቦ ለማቆየትም በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።
እንደ አቶ ሀብታሙ ገለፃ፤ የመጀመሪያው አስቸኳይ ጥገና የሚያስፈልጋቸውን 24 ቦታዎች በመለየት በጉዳታቸው ልክ ቅድሚያ በመስጠት ‹‹ላሊበላን በዘላቂነት›› ወይም (sustainable lalibela) በሚል በፈረንሳይ መንግሥት በተገኘ ድጋፍ አማካኝነት እየተሠራ ነው። ፕሮጀክቱ ቅርሱን ከጉዳት ለመታደግና ዘለቄታዊነቱን ጠብቆ ለትውልድ ለማሻገር ታሳቢ ተደርጎ ተጀምሯል።
‹‹ኢትዮጵያ ወደር የሌላቸው በርካታ ቅርሶች መገኛ ነች›› ያሉት አቶ ሀብታሙ፤ ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ቅርሶች በጉዳት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል። ብዙዎቹ ቅርሶች በማይተካ ደረጃ ሰፋፊ ጉዳቶችን እያስተናገዱ መሆኑን በጥናታቸው መለየታቸውን አስታውቀዋል። ቅርሶች ጉዳት እየደረሰባቸው የሚገኙት ከጥገና እጦት እና ከግንዛቤ እጥረት መነሻ መሆኑንም ተናግረዋል።
ጉዳት የደረሰባቸው እና ስጋት ያለባቸውን ቅርሶች የመለየት ሥራ እንደተሠራ የተናገሩት አቶ ሀብታሙ፤ በጎንደር የሚገኙ እንደ ጉዛራ ፣ ፋሲለደስ፣ ሱሲኒዮስና ሌሎች ዓለም አቀፍ ቅርሶች የሚገኙባቸውን ደረጃ፣ የደረሰባቸውን ጉዳት፣ የችግሮቹን መንስኤና የሚያስፈልጋቸውን የጥገና አይነት ለመለየት እንደ ኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ጥናት መደረጉን ገልጸዋል።
በውጤቱም ከእድሜያቸው አንፃር፣ የሚገባቸው ጥበቃና እንክብካቤ በጊዜው ስላልተደረገላቸው፣ ሁሉም ቅርሶች በጉዳት ደረጃ ላይ እንደሚገኙና ስጋት ላይ እንደሆኑ ተናግረዋል። በጥናቱ ጥልቅ የሆነ የጉዳት መጠናቸው ባይለይም በመሠረታዊነት ግን ችግሮቹ እንዳሉ አረጋግጠናል ብለዋል።
‹‹ቅርሶች የነበራቸውን ይዘት፣ እሴትና ታሪካዊ ትርጉም ሳይለቁ ለማደስ የሚያስችል ሰነድ ተዘጋጅቶ የሚያስፈልገው የበጀት መጠን ተለይቷል›› ያሉት አቶ ሀብታሙ፤ እድሳቱን ለማስጀመር ከምሁራን፣ ከመሪዎችና ከማህበረሰቡ ተወካዮች ጋር ሰፊ ውይይት ተደርጓል ብለዋል። የጉዛራ ቤተ-መንግሥት እድሳትም በዚሁ አግባብ መጀመሩን ገልጸዋል።
ከጎንደር ታሪካዊ ቅርሶች ውስጥ ዋንኛ የሆነው የፋሲለደስ ቤተ መንግሥትም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅህፈት ቤት ፕሮጀክቶች ስር በመያዙ ምክንያት እሴቱን እና ታሪካዊ ትርጉሙን ጠብቆ እንዲታደስ በማሰብ የተጠናውን ሙሉ ጥናት ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ማስረከቡን ገልጸዋል።
እንደ መሪ ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ፤ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ያለው በጀት ውስን በመሆኑ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ቅርሶች ለመጠገን እየሠራ ነው። በዘንድሮው ዓመት 20 ቅርሶች ለመጠገን ተለይቶ ወደ ሥራ ተገብቷል። በዚህ ሂደት በሐረሪ ክልል ጥንታዊ መንደር የሆነውን አበርከሌ ወደ ነበረበት ቁመና እንዲመለስ፤ ታሪኩ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲሻገር እንዲሁም የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን እየተሠራ ነው። በኦሮሚያ ክልል በአዲስ ዓለም አካባቢ ፖርቹጋል ድልድይ እና በሌሎች አካባቢዎችም የጥበቃና የጥገና ስራዎች እየተከናወኑ ነው።
‹‹በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በነበረው ጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን ቅርሶች ለመለየትና መልሶ ለመጠገን የዳሰሳ ጥናት አድርገናል›› ያሉት አቶ ሀብታሙ፤ በትግራይ አካባቢ የቅርስ አድን ሥራዎች ለመሥራት ውስን በጀት ተመድቦ መልካም ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን ገልጸዋል። እርምጃው ሙሉ ለሙሉ ችግሩ ባይፈታም ቢያንስ ስጋት ላይ በማይጥላቸው ደረጃ ላይ እንዲገኙ የተወሰደ ቅድመ ጥንቃቄ ሥራ መሆኑንም አንስተዋል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን የካቲት 2 ቀን 2016 ዓ.ም