በዞኑ ጥናት በተካሄደበት ስፍራ 950 ሚሊዮን ቶን የብረት ማዕድን መኖሩ ተረጋገጠ

አዲስ አበባ፡- በጎፋ ዞን መሎ ኮዛ ወረዳ ጥናት ባካሄደበት በ146 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ውስጥ ብቻ 950 ሚሊዮን ቶን የብረት ማዕድን ክምችት መኖሩን በጥናት ማረጋገጡን የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የኢንዱስትሪ ትስስርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር ቶሌራ ሴዳ(ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ አርባ ምነጭ ዩኒቨርሲቲ ከቀድሞው ደቡብ ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ጋር በመተባበር ላለፉት ስድስት ዓመታት በቡርጂ፣  በጋሞ፣ ጎፋ፣ ኮንሶና ደቡብ ኦሞ ዞኖች በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ስምንት የማዕድን ጥናት ፕሮጀክቶችን አከናውኗል፡፡ በዚህም የተለያዩ ከፍተኛ ጥራትና መጠን ያላቸው ማዕድናት መገኘታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ በዘንድሮ ዓመት ምን አለ? በሚል በተካሄደ ጥናት መሠረት በጎፋ ዞን መሎ ኮዛ ወረዳ ላይ በ146 ስኩየር ኪሎ ሜትር ውስጥ 950 ሚሊዮን ቶን የብረት ማዕድን ክምችት መኖሩን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ጥናቶችን በስፋት ማካሄድ ከተቻለ ከዚህም በላይ ክምችት ይኖራል፡፡

በተመሳሳይ በኮይሻ በተደረገው ጥናት ከፍተኛ ጥራት ያለው የከሰል ድንጋይ ክምችት መኖሩን የጥናት ውጤቱ ማመላከቱን የጠቀሱት ዶክተር ቶሌራ፤ ይህን ሀብት በመጠቀም ለኢኮኖሚ አጋዥ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ጥናቱ ስድስት ተመራማሪዎች የተሳተፉበት ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ጥናቱን ለማካሄድ የጂኦ-ኬሚስትሪና ጂኦ ፊዚክስ መረጃዎች ጥቅም ላይ ውለዋል ሲሉም አስረድተዋል፡፡

እንዲሁም በመሎ ኮዛ ወረዳ ባንካ ቀበሌ 429 ሚሊዮን ቶን የድንጋይ ከሰል ማዕድን ክምችት መኖሩ መረጋገጡንና፤ ጥናቱ የተደረገው በውስን ቦታ በመሆኑ መሰል ጥናቶችን ማካሄድ ቢቻል በባስኬቶ፣ ደቡብ ኦሞና ኮይሻ አካባቢዎች ከፍተኛ የማዕድን ክምችቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ምልክቶች መኖራቸውን ከጥናት ውጤቱ መገንዘብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ ገረሴ ላይ በተደረገው ጥናት ጂምስቶን በብዛት መኖሩ ተረጋግጧል ያሉት ዶክተር ቶሌራ፤ አኳማሪንና ጌጣጌጥ ማዕድናት በብዛት አሉ። እንዲሁም ለሴራሚክ ፋብሪካ ግብዓት የሚሆን ፊልድስፐር በብዛት እንዳለ ጥናቱ ያሳያል። በ38 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ላይ በተካሄደ ጥናት 101 ሚሊዮን ቶን ፊልድስቶር መኖሩ ተረጋግጧል፡፡ ተጨማሪ ጥናት ቢጠና እስከ ኮንሶ ድረስ እንደሚኖር መረጃዎች ያሳያሉ ብለዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለኢንዱስትሪና ቴክኖሎጂ ትስስር ከተሰጣቸው ተልዕኮዎች አንዱ ችግር ፈች ምርምር ከአጋር አካላት ጋር መስራት ነው፡፡ በ2010 ዓ.ም በቡርጅ አካባቢ ምን አለ? በሚል በተካሄደ ጥናት መሰረት ጀምስቶን፣ ሩቢ፣ ሳፋየር፣ በ2010 ዓ.ም መጨረሻ በኮንሶ ዞን ላይ ጥናቶች ተካሂደዋል፤ በዚህም የኮንስትራክሽን ማዕድናት የተገኙ ሲሆን፤ በተለይ ግራናይት፣ ቱርሚሊን፣ ባዛልትና ኤመራልድ እንዳሉ ማወቅ ተችሏል ብለዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ በጥናቱ የተገኘው ውጤት የሀገር ሀብት በመሆኑ ለኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ መዋል አለባቸው፡፡ እንደ ሀገር ያለንን ሀብት አናውቅም፤ ወደፊት በስፋት ጥናቶችን በማካሄድ ያለንን ሀብት ማወቅ አስፈላጊ ነው። በደቡብ ኢትዮጵያ የማዕድን ሀብት በስፋት ይኖራል ተብሎ አይገመትም ነበር፤ ነገር ግን ጥናቶች የሚያመላክቱት በተቃራኒው ነው፡፡ በመንግሥት በኩል አቅጣጫዎች ከተቀመጡ ብዙ ማዕድናትን በጥናት ማወቅ ይቻላል። የተቀሩት ቦታዎች እንዲጠኑ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

ሞገስ ጸጋዬ

አዲስ ዘመን  የካቲት 2 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You