
– በሁለተኛው ዙር 20 ሚሊዮን መማሪያ መጻሕፍት ከሁለት ወራት በኋላ ይደርሳሉ
– ከ11 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ሙሉ እድሳት ተደርጓል
አዲስ አበባ:- የ12ኛ ክፍል ትምህርት ምዘና እና ፈተና ሥርዓቱ የትምህርት ስብራቱ ያለበትን ደረጃ ለማወቅ
ማስቻሉንና በቀጣይም ግብረገብነትን ለመፍጠር ታሳቢ ያደረገ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በአዲሱ የትምህርት ካሪኩለም መሠረት የተዘጋጁ በሁለተኛው ዙር ከ20 ሚሊዮን በላይ መጽሐፍት
ከሁለት ወራት በኋላ ለትምህርት ቤቶች እንደሚደርሱና ከ11 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ሙሉ እድሳት መደረጉንም አስታውቋል፡፡
ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ከትናንት በስቲያ በሀገሪቷ የትምህርት ጥራት ማሻሻያና አጠቃላይ የትምህርት ዘርፉ
አፈጻጸም ዙሪያ ከሀገር ውስጥ ሚዲያዎች ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ እንደገለጹት፤ የአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ደረጃ በደረጃ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡
የ12ኛ ክፍል ምዘና እና ፈተና ሥርዓቱ የተቀየረው ችግሩን ለማወቅ፣ ለመለየትና በትምህርት ሥርዓቱ ግብረገብነትን ለመፍጠር ነው ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ ምዘና እና ፈተና ሥርዓት በ12ኛ ክፍል ፈተና ተግባራዊ የተደረገው የትምህርት ስብራቱ ያለበትን ደረጃ ለማወቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከማጭበርበርና ከኩረጃ የጸዳ ፈተና ቢሰጥ ወደ ከፍተኛ ትምህርት መሄድ የሚችልና የማይችለውን መለየት ሁለተኛ የትግበራው ዓላማ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ከመፍትሔውም ጋር የተያያዘው ግብረገብነት በትምህርት ማህበረሰቡ ውስጥ መፍጠር መሠረታዊ እና በሶስተኛ ደረጃ የሚጠቀሰው ነው ብለዋል፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የመማሪያ መጽሐፍት ስርጭት ሁለተኛው ዙር 20 ሚሊዮን ቅጂ ከሁለት ወራት በኋላ ህትመቱ ተጠናቅቆ እንደሚደርስ የጠቆሙት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ ዘንድሮ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ጥምርታ ቢያንስ አንድ መጽሐፍ ለሁለት ይሆናል የሚል መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡
በስምምነቱ መሠረት አታሚው ድርጅት አራት ሚሊዮን ተጠባባቂ መጽሐፍት እንደሚጨምርም ነው የገለጹት፡፡
“መጽሐፎቹን ለማሳተም አቅም የለም፣ የታተመው ከተለያዩ ፕሮጀክቶች እየተለመነ ነው”ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት አንድ መጽሐፍ ለሁለት ተማሪ በሚል ስሌት ለማሳተም ያስፈለገው 40 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
የመጽሐፍ ህትመት ጨረታውን ያሸነፈው ድርጅት ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር በመነጋገር በህትመት ዘርፍ ለመሰማራት መስማማቱን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ጠቁመዋል፡፡
በዚህም መሠረት በቀጣይ ዓመት በኢትዮጵያ ማሽን ተከላ እንደሚጀምርና ከዚያ በኋላ መጽሐፍ የማተም ችግር ይጠፋል ብለው እንደሚገምቱ የጠቆሙት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ ከትምህርት መጽሐፎች በተጨማሪ ሌሎች መጽሐፎች በቅናሽ ዋጋ የሚታተሙበት ዕድልን እንደሚፈጥርም ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡
ተማሪዎች በንድፈሃሳብ ደረጃ ከሚማሩት ትምህርት ባሻገር እንደተሰጥኦአቸው የተወሰነ ክህሎት ይዘው እንዲወጡ ተደርጓል፡፡ ኢኮኖሚክስ፣ግብርና ያሉ ትምህርቶች ተጀምረዋል፡፡
የትምህርት ቤቶች ደረጃን ለማሻሻል በ‹‹ትምህርት ለትውልድ›› ንቅናቄ ባለፉት ሰባት ወራት በተሰራው ሥራ 11 ሺህ 611 ትምህርት ቤቶች ሙሉ ዕድሳት ተደርጎላቸዋል ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ አራት ሺህ 871 ትምህርት ቤቶች እንደተሠሩም ነው የጠቆሙት፡፡
እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ ሶስት ሺ 180 ቅድመ አንደኛ፣ አንድ ሺህ 390 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ 295 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሕዝብ መዋጮና ትብብር ተሠርቷል፡፡ በተጀመረው ስሜት ከቀጠለ በአምስት ዓመታት ውስጥ የትምህርት ቤቶችን ገጽታ ለመቀየር የተጀመረው ሥራ ይሳካል፡፡
በትምህርት ገበታ ይገኛሉ ተብለው ከተገመቱት መካከል አምስት ሚሊዮን የሚደርሱ ተማሪዎች በግጭት፣ በጦርነት፣ በመፈናቀል፣ በድርቅ ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው እንደቀነሱም ፕሮፌሰር ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡
ከነዚህ መካከል በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ሦስት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን፣ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ተማሪዎች እንዲሁም በቅድመ መደበኛ ትምህርት ያልተገኙት 470 ሺ ተማሪዎች መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
በተቻለ መጠን ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ መደረግ እንዳለበት፣ ለትግበራውም የፖለቲካ ሁኔታው ሊሻሻል እንደሚገባውም መክረዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲዎች ራስገዝ እንዲሆኑ የተፈለገው የዩኒቨርሲቲ ተፈጥሮ ስለሆነ፣ ከምንም አይነት ተጽእኖ ነጻ ለማድረግ፣ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ፣ እውቀትና ትምህርት እንዲሁም አዳዲስ ሃሳቦች የሚፈልቁበት እንደመሆኑ መምህራንና ተማሪዎች በነጻነት እንዲያስቡ ጥናትና ምርምር እንዲሰራ ለማስቻል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን የካቲት 2 ቀን 2016 ዓ.ም