አዲስ ዘመን ድሮ

አዲስ ዘመን የታሪክ ቋት መሆኑ ይታወቃል። በብዙዎች እንደ ተመሰከረለት ከሆነ ደግሞ የታሪክ ቋት ብቻ ሳይሆን ራሱ ታሪክ ነው። ይህንን ስንል ዝም ብለን ሳይሆን ባስቆጠራቸው ከ80 ምናምን አመታት በላይ ውስጥ ታሪክን ምንም ሳያስቀር 1፣ 2፣ 3 ∙ ∙ ∙ በማለት ሲዘግብ መኖሩ ሲሆን፤ የሚከተሉት ለዛሬ የመረጥናቸው ናቸው።

የሻምፓኝ ግብዣ

ግርማዊ ንጉሠ ነገሥትና ግርማዊት እቴጌ ልዑለ ልዑላትን አስከትለው በክቡራን ሚኒስትሮችና መኳንንት ታጅበው ገነተ ልዑል ቤተመንግሥታቸው ገብተው በመንበረ ዳዊት ዙፋናቸው እንደተገኙ ሱዳንን፣ ሳውዲ አረቢያን፣ ጎብኝተው በደህና ስለመመለሳቸው ልዑላን ንጉሣዊያን ቤተሰብ ለክቡራን ሚኒስትሮችና መኳንንት፣ ለክቡራት ሴት ወይዛዝርት፣ ደስ የሚያሰኝ የሻምፓኝና የቀዝቃዛ መጠጥ ግብዣ ተደረገ::

በዚህም ጊዜ ግርማዊና ግርማዊት በደህና መመለሳቸውን ምክንያት በማድረግ ከደራሲዎች የተሰናዳው የደስታ መግለጫ ጽሑፍ ታድሎ ሲያበቃ በዚያ የነበረው ሁሉ “እንኳን በደህና ገቡልን″ በማለት ልባዊ ምኞቱን እየገለጸ ወደ ቤቱ ተመለሰ::

(አዲስ ዘመን፣ ጥር 16 ቀን 1952 ዓ.ም)

ገነተ ልዑል ቤተመንግሥት

ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መልካም ፈቃዳቸው ሆኖ ታህሳስ 20 ቀን 1952 ዓ∙ም ከጧቱ በ3 ሰአት ከስዊዲን አገር በቅርብ ጊዜ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት መጥተው የነበሩትን ሚስ አን ሜሪ ጃንሰን የተባሉትን የስዊዲን ጋዜጠኛ በክቡር ጸሐፌ ትዕዛዝ ተፈራወርቅ ኪዳነወልድ አቅራቢነት ተቀብለው ሩብ ሰዓት ያህል አነጋግረዋቸዋል::

እንዲሁም ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ከማሮክ የመጡት አልመቅረብ አልዓረቢ የተባለው የማሮክ የወር መጽሄት አዘጋጅ ሚስተር ጠይብ ሲባታ የወንጂን ስኳር ፋብሪካ፣ የቆቃን የሀድሮ አሌክትሪክ ግድብና የአምቦና የጅማን ከፍተኛ የእርሻ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎችንና የትምህርት ቤቶችን በመጎብኘት ሁለት ሳምንት ያህል ቆይተው ስለነበር በ3 ሰዓት ተሩብ ጉዳይ ላይ በገነተ ልዑል ቤተመንግሥት ተቀብለው 15 ደቂቃ ያህል አነጋግረዋቸዋል::

ቀጥሎም በ3 ሰዓት ተኩል በኢትዮጵያ ወንዶች ክርስቲያናዊ ማህበር ዋና ፀሐፊ የሆኑትን ሚስተር መርሰን ኤ ቢ ሾፕን ተቀብለው ሩብ ሰዓት ያህል አነጋግረዋቸዋል::

(አዲስ ዘመን፣ ታህሳስ 21 ቀን 1952 ዓ.ም)

የዓለም ፍሬ

አንዱ ብስል አንዱ ፍሬ

ዓለም ስትወልጂ ሁሉም መንታ መንታ፣

አንደኛው ቅን ሲሆን አንደኛው ወስላታ::

አንደኛው ደግ መንፈስ ሌላው አመጸኛ፣

ወንድሙን ለመግደል ለሊት የማይተኛ፣

ሁለቱም ሲሆኑ የማህጸን ጓደኛ፣

ታዲያ ለምን ሆነ አንደኛው ምቀኛ::

ብዬ ብጠይቃት ዓለምን በመላ፣

እሷም ነገረችኝ መልሱን እንዲህ ብላ::

ወልጄ … ወልጄ … ሲቀር ሳይሟላ፣

ሐኪሙ መርምሮ ኋላ ይቀራላ!!!

ኃይለሚካኤል ዓባይ

(አዲስ ዘመን፣ መጋቢት 7 ቀን 1952 ዓ.ም)

ዕቃ የሚደብቁ ነጋዴዎች ፈቃድ ይወሰዳል

(ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት )

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር 3ተኛው ዙር የዋጋ ቁጥጥር መጀመሩን ገልጦ ዕቃ ደብቀው የሚገኙ ነጋዴዎች ፈቃዳቸው የሚወሰድባቸው መሆኑን አስታውቋል::

ሚኒስቴሩ ሰሞኑን ባደረገው በሁለት ዙር የተከፈለ የቁጥጥር ዘመቻ አጥጋቢ ውጤት መገኘቱን ገልጧል::

በአዲስ አበባና በአካባቢው በሚገኙ የገበያ ሥፍራዎች፣ የንግድ መደብሮችና መናኸሪያዎች፤ እንዲሁም በየኬላውና በአዲስ አበባ አምስቱም በሮች እንስፔክተሮች ተሠማርተው ባልሆነ ቦታ ዕቃ በሚያቆዩና በሚደበቁ ነጋዴዎች ላይ ቁጥጥር ማድረጋቸውን ገልጦ በዚሁ መሠረት የዕቃ እጥረት እንዳይደርስ ዕቃ በሚደብቁ፣ ባልሆነ ቦታ በሚያቆዩና የንግድ መደብራቸው ከሚገኝበት ሥፍራ በቶሎ የማያደርሡ ነጋዴዎች በአስተዳደር ውሳኔ ብቻ የንግድ ፈቃዳቸው ላልተወሰነ ጊዜ እንደሚያዝባቸው አስታውቋል::

(አዲስ ዘመን፣ መጋቢት 1 ቀን 1968 ዓ.ም)

ጠጉሩን ሹሩባ ተሠርቶ የተያዘው ወንድ ልጅ ከክሱ ነፃ ሆነ

አፍሮ ጠጉሩን ሹሩባ ተሠርቶ በመገኘቱ ለባሕል ተቃራኒ የሆነ ድርጊት ፈጽሟል ተብሎ ከተከሰሰ በኋላ በቅርቡ ታስሮ የነበረው አበበ ወልደጻድቅ ከክሱ ነፃ ሆኖ መዝገቡ የተዘጋ መሆኑን የአዲስ አበባ አውራጃ ፍርድ ዓቃብያነ ሕግ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ::

አበበ ክስ ቀርቦበት ሊታሰር የቻለው በቅርቡ አፍሮውን ሹሩባ ከተሠራ በኋላ አዲሰ አበባ ከተማ፣ አፍንጮ በር አካባቢ 50 የሚሆኑ ሕፃናትን ሰብስቦ ያልታወቀ ንግግር ሲያደርግ በመገኘቱና በሹሩባውም መሠራት ምክንያት ለባሕል ተቃራኒ የሆነ ድርጊት ፈጽሟል ተብሎ ነበር:: በዚሁ ምክንያት ተከሳሹ 2ተኛ ወረዳ ፍርድ ቤት በእስር ቤት እንዲቆይ በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ስምንት ቀን ያህል በእስር ቤት ቆይቶ እንደነበር ተገልጧል:: የተከሳሹም ሁኔታ በዚሁ ጋዜጣ ተገልጦ ሹሩባ መሠራት ወንጀል ሊሆን ይችላልን? የሚል ትችት በማስከተል ጋዜጣው በወጣ ሰሞን ብዙዎችን ሲያጠያይቅ ሰንብቶ ነበር::

የአዲስ አበባ አውራጃ ፍርድ ዓቃበያነ ሕግ ጽሕፈት ቤትም ከጋዜጣው ባገኘው ዜና መሠረት ሁኔታውን ለመረዳትና ወንጀል ሊሆን ይችላል በሚልም ጥርጣሬ የምርመራውን መዝገብ አስመልክቶ በጥንቃቄ ከተመለከተ በኋላ በተከሳሹ ላይ ክስ ሊቀርብበት እንደማይችል ከምርመራው መዝገብ ሊረዳ ችሏል::

ምክንያቱም ተከሳሽ ጠጉሩን እንደ ሴት ሹሩባ ተሠርቶ መገኘቱ ቢነገርም በዚህ ሁኔታ በተገኘ ጊዜ ሹሩባውን ምክንያት በማድረግና ሴት በመምሰል የፈጸመው የማሳሳት ተግባር ባለመኖሩ፤ እንዲሁም ከ50 በላይ ሰዎችን ሰብስቦ በነበረበትም ጊዜ ምን እንደተናገረ ከሁለት እስከ አራት በተጠቀሱት ምስክሮች ያልተገለጠ በመሆኑ፤ በተከሳሹ ላይ የተጠቀሰውን አንቀጽ የባሕል መቃረንን የሚገልጥ ሲሆን፤ ተከሳሹ ግን የባሕል ተቃራኒ የሆነ አድራጎትን ሲፈጽም ባለመገኘቱና በዚህም የቀረበ ማስረጃ ባለመኖሩ መሆኑን የዓቃበያነ ሕጉ ጽሕፈት ቤት አስረድቷል::

ተከሳሹ ለመልካም ባሕል ተቃራኒ የሆነ ሁኔታ አሳይቷል ከተባለም የወንድ ሹሩባ መሠራት ቀደም ብሎ የነበረ መሆኑን ታሪክ የሚያስረዳ በመሆኑ ከዚህ ውጪ ወንድ እንደ ሴት ሹሩባ ቢሠራ ለባሕል ተቃራኒ ነው የሚያሰኝ ሕጋዊ ምክንያትና ባሕላዊ ልማድ ባለመኖሩ ጭምር ተከሳሹ ጥፋተኛ ሆኖ አልተገኘም::

በዚህም መሠረት በዝርዝር በተገለጡት ምክንያቶች የወንጀል ድርጊት ፈጽሟል ለማለት የሚያስችል አጥጋቢ ማስረጃና ሕጋዊ ምክንያት አለመኖሩ ስለታወቀ የአውራጃው ፍርድ ቤት ዓቃበያነ ሕግ ጽሕፈት ቤት በተጨማሪ አስረድቷል::

በመሠረቱ ወንድ ጠጉሩን ሹሩባ ቢሠራ አድራጎቱ ለባሕል ተቃራኒ ሆኖ እንደማይገኝ ተገልጧል:: ነገር ግን ሹሩባ ተሠርቶና ሴት መስሎ ሌላ ተግባር መፈጸም ወንጀል ሲሆን፤ ነገር ግን የወንጀል ድርጊት የመፈጸም ሙከራ ሳይደረግ፤ ወይም ወንጀል ሳይፈጸምና ሳይኖር ወንድ ልጅ ጠጉሩን ሹሩባ በተሠራ ብቻ ወንጀል ለባሕልም ተቃራኒ አለመሆኑን ከምሁራነ ሕግ ተነግሯል::

ወንድ ጠጉሩን ሹሩባ ቢሠራ ለባሕል ተቃራኒ የሆነ ድርጊት አሳይቷል ከተባለ በዚህ አንፃር የሚያጠያይቅ ሌላ ነገር መኖሩ ተገልጧል:: ለምሳሌ በአሁኑ ጊዜ ሴቶች አጭር ቀሚስ እየለበሱ ግማሽ አካላቸው ራቁቱን ስለሚታይ ይህም ለባሕል ተቃራኒ ሆኗል ማለት ነው የሚል ከአንዳንዶች ጥያቄ ቀርቦ አበበ በተያዘ ሰሞን ሲያከራክር ሰንብቶ ነበር::

(አዲስ ዘመን፣ መጋቢት 2 ቀን 1968 ዓ.ም)

በመልካምሥራ እና እየሩስ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 28 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You