
አዲስ አበባ፡- የጥቁሮች ታሪክ መታሰቢያ ወር ሲከበር የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት አስተሳሰብን በሚያስቀርና አንድነትን በሚያጎለብት መልኩ መሆን እንዳለበት ምሁራን ገለጹ፡፡
በዓመቱ የካቲት ላይ የሚከበረው የጥቁሮች ታሪክ መታሰቢያ ወርን አስመልክቶ በተዘጋጀው የፓናል ውይይት የተሳተፉት የታሪክ ምሁርና ተመራማሪው አየለ በከሬ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የጥቁሮች ታሪክ ሲታሰብ አንድነትን በሚያጎለብትና የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት አስተሳሰብን በሚያስቀር መልኩ ሊሆን ይገባል፡፡
አፍሪካዊያን በባህል በቋንቋ እንዲሁም በአኗኗር ዘዬ ጠንካራ ግንኙነት አላቸው ያሉት ዶክተር አየለ፤ ይህንን በማጎልበትና ለጥቁር ሕዝቦች ዋጋ የከፈሉትን በማሰብ ፈለጋቸውን መከተል ይገባል ሲሉ ተናግረዋል። መታሰቢያ ወሩ በውይይት መድረኮች መከበሩ ለወደፊት አላስፈላጊ የቅኝ ግዛት አስተሳሰቦችን ለማስወገድ ያግዛል ያሉት የታሪክ ተመራማሪው፤ አፍሪካዊያን ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ግንኙነታቸውን በማሳደግ ነጻነታቸውን ማወጅ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
እንደ ዶክተር አየለ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ ለመላው የጥቁር ሕዝቦች ነፃ መውጣት ከፍተኛ ድርሻ ነበራት፤ ይህን ድርሻዋን በተለያዩ መስኮችም እያሳደጉ መሄድ ይገባል። የፖሊሲ አማካሪና የኢኮኖሚ ሙሁሩ ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የጥቁሮች ታሪክ ሲታሰብ አንድነት በማጎልበትና የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት አካሄዶችን በተለያዩ ትብብሮች የሚሻሩበትንም መንገድ ማየት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ፓን አፍሪካኒዝም ለአፍሪካውያን ነፃነት ያሳደረው አዎንታዊ አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም ያሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ በአህጉሪቱ ጠንካራ ኢኮኖሚ ተባብሮ መገንባት ካልተቻለ ደግሞ የአፍሪካን ነፃነትን ሙሉ በሙሉ ለማወጅ አስቸጋሪ እንደማይሆን ተናግረዋል፡፡ እንደ ዶክተር ገለጻ፤ አፍሪካ ለኢንቨስትመንት መዳረሻ ምቹና ቀዳሚ ናት፤ የተፈጥሮ ሀብቶቿንና ዕውቀትን በማስተሳሰር የተሻለ መስራት የሚቻልበትን አማራጭ ማስፋት ይገባል።
በኢትዮጵያ የዛምቢያ ኤምባሲን ወክለው የተገኙት ሚስተር ናዋ ሲቦንጎ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ለአፍሪካና ለመላው የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ትግል አርዓያ መሆኗን ጠቁመው፤ የጥቁሮች ወር በየጊዜው መታሰቡ ለአፍሪካውያን አንድነትና ነፃነት ጉዳዮች ላይ የበለጠ ትብብር ለማድረግ ያግዛል ብለዋል፡፡
መላው አፍሪካዊያን የኢኮኖሚና የንግድ እንዲሁም ፖለቲካዊ ግንኙነታቸው ወደ ላቀ ደረጃ በማድረስ ከዘመናዊ የቅኝ ግዛት አካሄዶች መውጣት እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል። ለጥቁሮች ታሪክ መታሰቢያ የሆነው ወርሀ የካቲት፤ ለጥቁሮች ነጻነት የታገሉ አርበኞች፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች፣ ተራማጆችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን ትግል ለመዘከር በየዓመቱ ይከበራል፡፡
ልጅዓለም ፍቅሬ
አዲስ ዘመን ጥር 26/2016