ወይዘሮ ዝምታወርቅ ነጋሽ ይባላሉ። በሥራዎቻቸው ታዋቂ፤ በብዙዎች ደግሞ የሚመሰገኑ የተቸገረን ረጂ፣ አስተዋይና ታታሪ እናት ናቸው። እኔም ይህንን ይዤ ነበር ከእርሳቸው ዘንድ ብዙ የህይወት ተሞክሮ እንዳለ በማሰብ ያሉበት ድረስ ያመራሁት። እውነትም ካሰብኩት በላይ ብዙ ተሞክሮ እንዳላቸው የተረ ዳሁት ከቃለመጠይቁ ቆይታ በኋላ ነው።
የፊት ገጽታቸው ደርባባነታቸውን ይናገ ራል፤ ሰው አክባሪም መሆናቸውን ይመሰክራል። ለዚህም ትንሽም ሆነ ትልቁን አንቺ ማለት አለመውደዳቸው ማሳያ ነበር። ባደጉበት የቤተሰብ ሁኔታ ይሆናል ይህንን የሰጣቸው። በዚያ ላይ ደግሞ በስነምግባር ተኮትኩተው ማደጋቸው የትናንቱን ማንነታቸውን አለመልቀቃቸው ዛሬ ላይ ያላቸውን ባህሪ አጎናጽፏቸው ይሆናል።
የሕይወት እንዲህ ናት ዓምዳችን እንግዳ ወይዘሮ ዝምታወርቅ ቃለመጠይቁን ስንጀምር “ምንም የሚያስተምር ነገር የለኝም” የሚል አስተያየት ሰንዝረው ነበር። በኋላ ግን የመግባ ቢያ ጭውውት ስናደርግ ‹‹ያስተምራል ካልሽ …›› ብለው ከልባቸው የተቀመጠውን የሕይወት ተሞክሮ አጋሩኝ። እኔም ከነገሩኝ ያስተምራሉ ያልኩትን ቀንጨብ በማድረግ እንዲህ አቀረብኩት።
ስም ከግብር ጋር ሲዋሃድ
እትብታቸው የተቀበረው በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ወሊሶ ከተማ ነው። ይሁን እንጂ በቦታው ብዙም መቆየት አልቻሉም። ስድስት ዓመት ሲሞላቸው እናታቸውን ተከትለው ሸገር ላይ ነው እድገታቸውን ያደረጉት። ለዚህ ደግሞ መንስኤው የአባታቸው መሞት ነበር። እናታቸው በቦታው ብዙ ዘመድ አዝማድ ቢኖራቸውም ዋናው ቤተሰብ የሚገኘው አዲስ አበባ በመሆኑ ጓዛቸውን ጠቅልለው አዲስ አበባ እንዲገቡ ተገደዱ።
ለቤተሰቡ ሦስተኛ ልጅ የሆኑት ወይዘሮ ዝምታወርቅ በእነርሱ ጊዜ ስም ያለምክንያት እንደማይወጣ ይናገራሉ። በዚህም የእርሳቸው ስምም በትርጓሜ የወጣ እንደሆነ ይገልጻሉ። በዋናነት ሁለት ለስማቸው መውጣት ምክንያት የሆኑትን ያነሳሉ።
የመጀመሪያው አባታቸው ሲሞቱ የተላበሱት ጸባይ ሲሆን፤ ነገሩም እንዲህ ነው። በፊት ፍልቅልቅ ሕፃን ነበሩ፣ ማንም ሰው ይይዛቸዋል ግን አያለቅሱም፤ ማንም ሰው ይዟቸው ሊያድርም ይችላል። ይህ ጸባይ ግን ከአባታቸው ሞት በኋላ ተቀየረ። ማልቀስም ሆነ መሳቅ አቆሙ። ዝምታው ነገሰ።
ሁለተኛው ምክንያት ብለው የጠቀሱት ደግሞ ከቤተሰቡ ውስጥ ብዙ የማይናገሩና በውስጣቸው ብዙ ነገሮችን የሚያብሰለስሉ መሆናቸው ነበር። በዝምታ ውስጥ ስራቸውን አያስተጓጉሉም፤ ዝም ብለው የደማ ሥራ ይሰራሉ። በእነዚህ ምክንያቶች መጠሪያ ስማቸው ዝምታወርቅ መባል መቻሉን አውግተውኛል።
‹‹በእኛ ቤት›› ይላሉ ‹‹በእኛ ቤት ትልቅ ትንሽ ብሎ ነገር የለም፤ ሁሉም ይደማመጣል። ሁሉም የሚገባውን ሥራ ይሰራል። ታዛዥ አዛዥ ብሎ ነገር የለም። መደማመጥ አብዝቶ የሰፈነበት ቤተሰብ ውስጥ ነው ያደኩት። በዚህም ዛሬም ድረስ ለመከባበርና ለመደማመጥ ትልቅ ቦታ እንድሰጥ ሆኛለሁ» ይላሉ ልጅነታቸውን ሲያስታውሱ።
ወይዘሮ ዝምታወርቅ በልጅነታቸው በጣም ከሚወዱት ነገር አንዱ ለሰው በጎ ማድረግን ነው። በቤት ውስጥ ሁሉ ነገር ቢሞላላቸውም የተቸገረ ሰው ካዩ ሳይበሉ ይውሏታል እንጂ ያላቸውን ከማካፈል አይቦዝኑም።
በእነርሱ ቤት የቦታ፣የምግብ እና የሠራተኛ ችግር የለም። በእነርሱ ቤት የደብተርና እስኪርብ ቶም ማጣት አይታሰብም። ስለዚህም ወይዘሮ ዝምታወርቅ በእነርሱ ቤት የሞላው ሁሉ በሌሎችም ቤት እንዲሞላ ይፈልጋሉ። በዚህም የቻሉትን ሁሉ ለተቸገረ ያደርጋሉ። በተለይ በልጅነታቸው ከሚያደርጓቸው ነገሮች የሚያስደስታቸው አቅመ ደካሞችን ማገዝና መታዘዝ ነበር። ችግረኛ ጓደኞቻቸውንም ባላቸው ሁሉ መደገፍ ይበልጥ እንደሚያስደስታቸው ይናገራሉ።
የትምህርት ሀሁ…
ወይዘሮ ዝምታወርቅ ባደጉበት እንደዛሬው ቅድመ መደበኛ የሚባል ትምህርት ቤት ባይኖርም በግቢያቸው የቄስ ትምህርት የሚያስተምር መምህር ዘንድ ፊደል የሚቆጥሩበትን እድል አግኝተዋል። ከዚያም ቢሆን ዘመንኛውን ትምህርት ለመማር በወቅቱ አንቱ የተባለ ትምህርት ቤት ለመግባት ችለዋል። ይኸውም በየነ መርድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ነበር። በዚህ ያለው ቆይታቸው ሲጠናቀቅ ደግሞ ኮሜርሻል እስኩል ማለትም በዛሬው የንግድ ሥራ ኮሌጅ ትምህርት ቤት ገብተው እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን አጠናቀዋል።
ወይዘሮ ዝምታ ወርቅ በትምህርታቸው በጣም ጎበዝ ወይም በጣም ሰነፍ አልነበሩም። መካከለኞቹ ላይ የሚቀመጡ ናቸው። ይህ ደግሞ የከፍተኛ ትምህርትን የመማር እድል አይነፍጋቸውም። በዚህም ዲፕሎማቸውን ለመማር ከአዲስ አበባ ይልቅ እንግሊዝ ይሻላል የሚለው የቤተሰቡ ምልከታ እንግሊዝ አገር እንዲያቀኑ አደረጋቸው። ለሦስት ዓመትም በፒትማንስ ኮሌጅ በአስተዳደር የትምህርት ዘርፍ ተማሩ። ከዚያ በኋላ ትምህር ታቸውን አልቀጠሉም። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ በዘርፉ ብዙ መስራት መፈለጋቸው ነው። ሆኖም ለሥራቸው የሚያግዛቸውን የተለያዩ ስልጠናዎችን ወስደዋል።
ሙያን በተግባር
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ በጸሐፊነትና አስተዳደር ሥራ ነበር ተቀጥረው ለ17 ዓመት ያገለገሉት። ይህ ልምዳቸው ደግሞ የራሳቸውን ሥራ እንዲጀምሩ እንዳገዛቸው ይናገራሉ። አዋጪ ሥራ የትኛው እንደሆነም ሲያጠኑ የቆዩት በዚህ መስሪያ ቤት ሳሉ ነበር። እናም ባለቤታቸው በመርከብ ሥራዎች ድርጅት ውስጥ በመስራቱና የተሻለ ሥራ በትራንስፖርት አገልግሎት ላይ መስራት እንደሆነ በማመኑ መጀመሪያ የትራንስፖርት አገልግሎት በግል ደረጃ መስጠት እንዲጀምሩ በሩ ተከፈተ።
‹‹ፍርተርስ ኢንተርናሽናል ፖቦሚ ኃ.የ.የግ.ማ›› በማለትም ስራቸውን ማጧጧፍ ቀጠሉበት። ይህ ሥራ ደግሞ የገንዘብ ምጣኔያቸ ውን ከፋ ሲያደርገው እይታቸውን አሰፉ። ሪዞርት ላይ ቢሰሩ የበለጠ ውጤታማ እንደሚሆኑ ተግባቡበት። ከዚያም በወሊሶ ከተማ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሆቴል ሽያጭ ጨረታ መውጣቱን ተከትሎ የትራንስፖርት አገልግሎቱን በሪዞርት በመደገፍ ወሊሶ ላይ ነጋሽ ሪዞልትን ከፈቱ።
ይህ የሪዞርት ስራቸው በአንድ ቦታ ብቻ ተወስኖ እንዳይቀርም ሌሎች አማራጮችን ማስፋት ላይ የተሰማሩት ወይዘሮ ዝምታወርቅ፤ በቅርብ ርቀት ያለንና ለሪዞልት ምቹ የሆኑ ከተሞችን መመልከታቸውን ተያያዙት። እናም ቀጣይ ምርጫቸው ወንጪ ሊያደርጉ አስበው ቦታ ተረክበው ሥራ ለመጀመር ዝግጅት ላይ ናቸው። በተመሳሳይ ደንዲ ላይም እንዲሁ ብዙ ምቹ ሁኔታዎችን በማየታቸው ወደዚያ በመሄድ ጥያቄ አቅርበው በአካባቢው ማህበረሰብ ግፊት የግጦሽ ቦታ ተለቆላቸው አጥር የማጠር ተግባራቸውን እንዳከናወኑ አጫውተውኛል።
«የዚህ ሁሉ ተግባር መቋጫው የኢንቨስት መንት ኮሚሽን በጎ ምላሽ ነው» የሚሉት ባለታሪኳ፤ አጥር አጥሮ መቀመጥ ውጤት ሊያመጣ አይችልም። የመስሪያ ፈቃዱ ቶሎ ተሰጥቶ ሪዞርቱ መሰራት አለበት። ለዚህ ደግሞ መንግሥት በጎ ምላሹን ቶሎ ሊያሳውቃቸው እንደሚገባ ይናገራሉ።
ወይዘሮ ዝምታወርቅ «ኢንቨስተርነት ሁሉንም መያዝ ሳይሆን አዋጭውን መርጦ ውጤት ላይ ማድረስ ነው። ለዚህም ደግሞ በአቅምና በትምህርት የተገነባ አሰራር መዘርጋት ይገባል። ስለሆነም አሁን እየሰራን ባለው ሥራ ውጤታማ እየሆንን የመጣንበት መንስኤ ሁላችንም በሙያ የታገዘ ሥራ በመስራታችን ነው›› ይላሉ። ለዚህም የሚያግዛቸውን አዲስ አበባ ከተማ ላይ ሁሉንም ስራ የሚቆጣጠሩበት ማዕከል ከፍተው ነጋሽ ሪዞርት በማለት እየሰሩ ይገኛሉ።
‹‹ኢንቨስትመንት ለአንድ አገር እድገት ወሳኝ መሆኑን መናገር ለቀባሪው አረዱት ነው›› የሚሉት ባለታሪኳ፤ በምሰራቸው ሥራዎች ለበር ካታ ሰራተኞች የሥራ እድል መፍጠር ችያለሁ። ከዚህ የበለጠ ለመስራት ደግሞ የያዝኳቸው ሥራዎች በአፋጣኝ እንዲጓዙ ከመንግስት የሚሰጡ ምላሾች ፈጣን ሊሆኑልኝ ይገባል። እኔ ደግሞ የምሰራው በቱሪዝም ላይ በመሆኑ ብዙ የውጪ ምንዛሬ ማስገኘት የምችልበት አጋጣሚ ሰፊ ነው። እናም ለሰሪ ሥራ መስጠት ሳይሆን ሥራው ውጤት አምጥቶ አገር እንዲገነባ ማድረግ ያስፈልጋልና መንግሥት እንዲያግዘኝ ጥሪ ይቅረብልኝ ብለዋል።
አገር ወዳድነትን ለልጅ
ወይዘሮ ዝምታወርቅ በእንግሊዝ አገር ሲማሩ ብዙ የሥራ እድሎች እንደቀረቡላቸው ያስታውሳሉ። ይሁንና ከአገሬ የሚበልጥ ማንም የለም የሚል አቋም አላቸው። በዚህም ብዙ እድሎቻቸውን ትተው አገራቸው ገብተ ዋል። «አገሬ እኔን አስተምራኛለች፤ ግን አልተጠቀ መችብኝም። ምክንያቱም ለእርሷ ምን እንደ ምሰጥ የማውቀው እኔ ነኝ። ስለዚህም ብዙ እንደወጣብኝ ብዙ ማድረግን እሻለሁና ቅድ ሚያ ለአገሬ ብዬ ነው የተመለስኩት» ይላሉ እንግሊዝ አገርን እንዴት ትተው ወደ አገራቸው እንደተመለሱ ሲያወሱ።
«የሌላ አገር ማገልገል ለእኛ ኢትዮጵያውያን ዋጋው ዝቅ ያለ ነው። ምክንያቱም ነጻና የምንሰራ፤ ብዙዎችንም የሚያስቀና የፈጠራ አቅም ያለን ነን። ሆኖም መገዛት ልምድ እያደረግነው በሌላ አገር ለመስራት እንሯሯጣለን። በዚያ ሄደንም የማይገባንን ነገር እንሰራለን። ምክንያቱም ሌሎች አገሮች የሚገባንን አይሰጡንም፤ ይገባችኋል የሚሉትን ነው የሚሰጡን። አገራችን ግን እኛ ከበረታን የሚገባንን ብቻ ሳይሆን ከሚገባን በላይ ታጎናጽፈናለች። ስለሆነም መጀመሪያ አገር ወዳድነትን በውስጣችን አንግበን ለራሳችን ስንሰራ አገሪቱ ካላት ሁሉ ትቸረናለች» ይላሉ ።
ወይዘሮ ዝምታወርቅ ከራሳቸው አልፈው ልጆቻቸውንም በዚህ ምዕራፍ ውስጥ እንዲያልፉ ያደረጉ አገር ወዳድ እንስት ናቸው። ይህ ሲባል ደግሞ በወሬ ብቻ አይደለም። በተግባር ከእንግሊዝ አገር ልጆቻቸውን በማምጣት አርአያነታቸውን ተከትለው ከሥራቸው እንዲሰሩ አድርገዋቸዋል።
« ሁሉም እድሉ ካለው ትምህርትና እውቀት መቅሰም ተገቢ ነው።» የሚል እምነት ያላቸው ባለታሪኳ፤ ልጆቻቸው እንግሊዝ አገር ሄደው የመጀመሪያውና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን እንዲማሩ አድርገዋል። ይህንን ሲያደርጉ ግን የትምህርት መጠናቀቂያ ጊዜን ጠብቀው ወደ አገራቸው እንዲመጡ በማድረግ ነው።
«ለዚህም ምክንያት ነበረኝ» ይላሉ። በዚያ ቢቆዩ አገሩን ይለምዱትና ኢትዮጵያ ምን ትሰራለች ሊሉ ይችላሉ። ስለሆነም ከአገራቸው ውጪ አማራጭ እንደሌለ ለማሳየት አገራቸው ቶሎ ቶሎ እንዲመጡና ታሪካቸውን እንዲያውቁ ለማድረግ ነው። ይህ ደግሞ ልጆቻቸው በእንግሊዝ አገር የመኖር ሰፊ እድል ቢኖራቸውም አገራቸውንና ወገናቸውን እንዲመርጡ አስችሏቸዋል።
ለማህበረሰብ መኖር
ወይዘሮ ዝምታወርቅን ከልጅነት የጀመረው በጎነት ዘወትር እንደተከተላቸው የሚታይበት ዋናው ጉዳይ ይህ ለሰው መኖራቸው ነው። ገና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሳሉ ነበር በግላቸው ከሚከፈላቸው ደመወዝ ላይ መለገስን የለመዱት። ካላቸው የወር ገቢ ላይ እየቀነሱ ለተቸገሩ መድረስንም ሀ ያሉት። ባል ካገቡ በኋላም ቢሆን ይህ ሁኔታ ጠነከረ እንጂ አልተቋረጠም። የባለቤታቸውም እጅ ለለጋሽነት የተዘረጋ በመሆኑ ይበልጥ ጎለበተ እንጂ አልታጠፈም ።
በግላቸው የበጎነታቸውን ሥራ የጀመሩት በትውልድ ስፍራቸው ገጠር ቀበሌ ውስጥ አንድ ትምህርት ቤት በማሰራት እንደነበር ያስታውሳሉ። ለዚህ ያነሳሳቸው ደግሞ ከርቀት መጥተው የትምህርት ጥማታቸውን ለማርካት ደፋ ቀና የሚሉትን ልጆች መመልከታቸው ነው። እንደውም በርቀቱ ምክንያት ብዙዎች ትምህርታቸውን አቋርጠው ሲመለከቱ ልባቸው ይሰበር እንደነበር ይናገራሉ። ነገር ግን ያሰቡትን ከግብ ሳያደርሱ መቆም የማይወዱት እንግዳዬ በወር ከሚሰጣቸው ደመወዝ በማጠራቀም ዝም ብሎ የጨረቃ ቤት አሰሩ።
የተማሪዎቹን መብዛትና የትምህርት ፍላጎታቸውን ሲመለከቱ ደግሞ በስርዓት ሁሉ ነገር የተሟላለት ትምህርት ቤት ሊያደርጉላቸው ቻሉ። ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍልም ከፍ እንዲል አስቻሉት። ይሁንና ይህም ቢሆን ችግሩን በስፋት ሊቀርፈው አልቻለም። እናም ቀጣይ ክፍሎች ማስፈለጋቸውን በማየታቸው እስከ ስምንተኛ የሚቀጥልበትን ሁኔታ አመቻቹ።
ዛሬ ላይ ለመንግሥት አስረክበውት ብዙዎ ችን እያፈራ ይገኛል። ይሁንና ከጎናቸው ግን አልተለዩም፤ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ይደር ሱላቸዋል። እንዳውም እስካሁን ከፍተኛ ውጤት ለሚያስመዘግቡ ተማሪዎች በትምህርት ማጠናቀቂያ ወር ላይ በመገኘት ሽልማት ያበረክ ታሉ።
ዩኒቨርሲቲ የገቡ ተማሪዎችን ጭምር ያግዛሉ። እስካሁን 18 ልጆችን በዩኒቨርሲቲ አስተምረው አስመርቀዋል። አሁንም የሚደግፏ ቸው ተማሪዎች አሉ። ነገር ግን አንድ ነገር እንደጎደላቸው ያነሳሉ። በዩኒቨርሲቲ ያስመረ ቋቸውን ተማሪዎች ሰብስበው ለሌሎችም እንዲ ደርሱ ማድረግ አለመቻላቸው ያስቆጫቸዋል። የጋን ውስጥ መብራት እንደሆኑ እንዲሰማቸው እንዳደረጋቸውም ነግረውኛል። ስለዚህም በቅርቡ ሰብስበው ለማነጋገር እንደፈለጉም አጫው ተውኛል።
«መስጠት ሰጪን ያዘጋጃል» የሚል እምነት ያላቸው ወይዘሮ ዝምታወርቅ፤ ሰው ስለተደረገለት ብቻ ምላሽ መስጠት እንደሌለበት ይናገራሉ። ላደረገለት ሰውም ብቻ አይደለም ምስጋናው መቸር ያለበት የሚል አቋም አላቸው። ይልቁንም ለሌላቸው በማድረግ ክፍያውን ማሳየት ይኖርበታል ባይ ናቸው። እርሳቸውም የሚፈልጉት ያስተማሯቸው ልጆች እንደ እርሳቸው ለጋስና ለተቸገረ ደራሽ እንዲሆኑ ነው።
እንግዳዬ ማንኛውም ሰው በችግር ወደ እርሳቸው ከመጣ እንቢ ማለት አያስችላቸውም። ይህንን የሚያውቁ ብዙ ሰዎች ወደእርሳቸው ዘንድ ይነጉዳሉ። በተለይ ለህክምና ጉዳይ እርሳቸውን የሚጠይቁ ብዙ ናቸው። ወሊሶ ላይ የታመመና ችግሩን መቋቋም ያልቻለ በእርሳቸው ድጋፍ ይታከማል። አሁን አሁን ግን በርከት ያለ ሰው ስለሚመጣ ለማስተናገድ እየተቸገሩ እንደሆነ ይናገራሉ። ስለዚህም አንድ አማራጭ ይዘዋል። ችግረኛ የሚያገኙበትን ቀን ወስነዋል። ይሁንና ይህንን አልፎ ችግሩ የገዘፈበት ሰው ከመጣ ከማስተናገድ ወደ ኋላ አይሉም። የማይችሉ ከሆነ ብቻ ነው የተወሰነ ገንዘብ ሰጥተው ጊዜ እንዲጠብቅ አልያም ሌላ አማራጭ እንዲፈልግ የሚያደርጉት።
ወይዘሮ ዝምታወርቅ ለችግረኛ ደራሽነታ ቸው በዚህ አያበቃም። በወር ተቆራጭ የሚያደ ርጉላቸው አዛውንቶችና አቅመ ደካሞችም አሏቸው። ተራራውን ምሰው ሰው ቢያንስ በፈረስ እንኳን እንዲጓዝ ያደረጉም በጎ አድራጊ ናቸው። ለዚህ ደግሞ የደንዲ ነዋሪዎች ምስክር ይሆኑላቸዋል። እንዳውም ‹‹ከአምላክ የተሰጠችን ገጸ በረከት ነች›› ይሏቸዋል። ምክንያታቸው ደግሞ ተራራ እየቧጠጠ የሚጓዘውን ማህበረሰብ መንገድ በመስራት ምርቱን እንዲያቀርብ፣ የፈለገውን ሸምቶ እንዲገባ አስችለዋል።
ዛሬ አዛውንቶች ሳይቀሩ ወደ ከተማ ወጥተው ቤተሰብ እንዲጠይቁ የሆነው በእርሳቸው ነው። ቦታው ምን አይነት ይዞታ እንዳለው ማወቅ የተቻለውም እርሳቸው በከፈቱት በር ነው። አሁን ደግሞ ለዚህ ስፍራ ሌላ ልዩ ማስተዋወቂያ ይዘዋል። ሪዞርት ሰርተው ቦታውን የቱሪስት መናኸሪያ ሊያደርጉት እየሰሩ ይገኛሉ።
በማህበራዊ ጉዳይ ኃላፊነታቸውን በመወ ጣት አንቱታን ያተረፉ እንስት ናቸው። ምክንያ ቱም በሚሰሩበት ዘርፍ አገራቸውን በሚገባ ያስተዋውቃሉ። ለደን ጥበቃም የሚያደርጉት ነገር ልምድ የሚቀሰምበት ነው። በተለይ ሪዞርታቸው ባለባት ወሊሶ ከተማ የሚሰሩት ሥራ ብዙዎችን ያስደመመ ነው። እንደ ጸበል የሚጠቀሙበት ፍልውሃ በእርሳቸው እገዛ የተሻለ ጥበቃ እንዲያገኝ አድርገዋል።
ሪዞርታቸው ውስጥም ሲገባ ቢሆን የብሔር ብሔረሰቦች መናኸሪያ ነው። አንድ ጎብኚ የትም ሳይሄድ የሚይዛቸውን የመኝታ ክፍሎች በመቀያየር ብቻ ኢትዮጵያን ማየት ይችላል። የየብሔረሰቡ መገልገያ ቁሳቁሶች፣ አልባሳትና ሌሎች የማንነት መገለጫዎቹ ከነክዋኔው የሚቀርብበት ነው። ስለዚህ ለአገር ገጽታ ግንባታም የበኩላቸውን እየተወጡ ያሉ መሆናቸው ይበል የሚያሰኝ መለያቸው ነው።
ቤተሰብ
ወይዘሮ ዝምታወርቅ ከባለቤታቸው ጋር በትዳር 35 ዓመታትን አሳልፈዋል። ግንኙነታቸው በጓደኛ የተመሰረተ ቢሆንም በጓደኛ ተሸመጋግለው አያውቁም። ችግራቸውን በራሳቸው ውይይት ነው የሚፈቱት። በቤት ውስጥ አንድም ቀን ጠንከር ያለ ጸብ ስለማይፈጠር ለልጆቻቸው ትልቅ አርኣያ የሚሆኑ ናቸው።
«ባለቤቴ እኔን ይሰማል፤ ያከብረኛልም። እኔም እንደዛው አደርጋለሁ። ይህ ደግሞ ለዚህ ያህል እድሜ አድርሶናል» ይላሉ። በዚህም ዛሬ የሦስት ልጆች እናት ሆነዋል። ልጆቻቸውን በስርዓት ለማሳደጋቸው ማሳያውም ከስራቸው ሳይለዩና በእርሳቸው ምርጫ ተምረው ለወግ ማዕረግ መብቃታቸው ነው። እንዳውም ስለ ትምህርት መስክ ምርጫቸውና ከእርሳቸው ጋር እንዴት አብረው እንዲሰሩ እንዳደረጓቸው ሲናገሩ እንዲህ ነበር ያሉት።
‹‹አብሮ መስራት እንደአብሮ መብላት ደስ ይላል። አብሮ መለወጥም ላይ ያደርሳል። በተለይም ከቤተሰብ ጋር ሲኮን ደግሞ መግባባቱም ስለሚኖር ውጤታማነቱ አያጠያይቅም። ስለዚህም “ሆስፒታሊቲ ኤንድ ቱሪዝም፣ ቢዝነስ እና ሎጂስቲክስ” የተባሉ የትምህርት መስኮችን በሁለተኛ ዲግሪያቸው እንዲያጠኑ አድርጌያቸዋለሁ። ይህ ሲሆን ግን በማወያየት እንጂ በማስገደድ አይደለም።
በሁሉም የትምህርት ዝግጅታቸው ላይ እኔ ከጎናቸው አለሁ፤ አስጠናቸዋለሁ። የእኔ ፍላጎት እነርሱ ላይ ተጋብቶ ሊሆን ይችላል ሁሉም የማህበራዊ ሳይንስ ትምህርትን ይመርጣሉ። ስለዚህም በራሳቸው ምርጫ መጀመሪያ ዲግሪያቸውን ሁሉም ቢዝነስ አደረጉ። ሁለተኛ ላይ ግን በአንድ ላይ እንስራ በሚል ተመካክረን ማን በምን ቢያጠና ውጤታማ ይሆናል የሚለው ተወስኖ እዚህ ላይ ደርሰናል›› ሲሉ እንዴት ሀሳብ እንዳስቀየሩ ይናገራሉ።
ወይዘሮ ዝምታወርቅ በልጆቻቸው ላይ አገራ ቸውን የሰሩም ናቸው። ለዚህም ደግሞ ማሳያው እርሳቸው እንግሊዝ አገር መቅረትና ልጆቻቸውም እንግሊዛዊ እንዲሆኑ ማድረግ ሲችሉ ተመልሰው አገራቸውን ሊያገለግሉ ቆርጠው ተነሱ። ብዙ የስራ አማራጮች ቢቀርብላቸውም አይበጀኝም አሉ። ልክ እንደ እርሳቸው ሁሉ ልጆቻቸውም ማን እንደአገር እንዲሉ አደረጓቸው።
ሽልማት
ወይዘሮ ዝምታወርቅ በሰርተፍኬት ደረጃ ለቁጥር የሚያዳግቱ ሽልማቶች ተበርክተው ላቸዋል። በዋንጫ ደረጃ ብቻ ከ20 የማያንሱ ስጦታዎች እንደተበረከቱላቸው መደርደሪያቸው ይመሰክራል። ሜዳልያና ሌሎች ሽልማቶችም አሏቸው። ይህ የሆነው ደግሞ በርካታ የበጎ አድራጎት ተግባራትን በመፈጸማቸው እንደሆነ ይገልጻሉ። ለአብነት ባንቱ ላይ ባሰሩት የደጃዝማች ባልቻ ሀውልት፣ በወሊሶ ትምህርት ቤት ግንባታ፣ በሪዞርታቸው የተሻለ አገልግሎትና መሰል ጉዳዮች ያገኟቸው ናቸው።
መልዕክት
«ከሚሊዮኔ ለአንድ ሰው 500 ሰጥቼ የማድነው ከሆነ ለእኔ የሚጨምርልኝ ነገር አለ ብሎ ማሰብ ሰዋዊነት ነው። መርዳት ደግሞ ያደግንበትም የኖርንበትም ባህላችን ነው። ስለዚህ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይህንን መሰረት አድርጎ ቢንቀሳቀስ ዛሬ ችግረኛ አናይም ነበር። እናም ከእኔ ይህንን ተምረው ተግባራዊ ያድርጉት እላለሁ» ይላሉ።
«ያለውን ከሰጠ ንፉግ አይባልም የሚለው አባባል ዛሬ ላይ ለምንደርስላቸው ሚሊዮኖች መሆን አለበት። ሁለት ብር ከኛ አያጎልም፤ ለተቸገረ ግን ቢያንስ ዳቦ ገዝቶ ረሀቡን ያስታግሳልና ምን ትሰራለች አንበል» መልዕክታቸው ነው። እኛም የእርሳቸው መልዕክት ሥራችን ይሁን እያልን ዓባይን በጭልፋ የሆነውን ተሞክሯቸውን በዚህ ቋጨን።
አዲስ ዘመን ዛሬግንቦት 25/2011
ጽጌረዳ ጫንያለው