
አዲስ አበባ:- የአንጋፋው ጋዜጠኛ አስፋው መሸሻ ሥርዓተ-ቀብር በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ትናንት ተፈፅሟል።
ከ25 ዓመታት በላይ በሬድዮና ቴሌቪዝን ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢነት ያሳለፈው ጋዜጠኛው፤ የአንድ ወንድ ልጅ አባት እንደ ነበር ተገልጿል። አስፋው መሸሻ በኢ.ቢ.ሲ. ኤፍ.ኤም አዲስ 97 ነጥብ 1 “አይሬ” በተሰኘው የመዝናኛ ፕሮግራም አዘጋጅ እና በኢቢኤስ ቴሌቪዥን የመዝናኛ ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢ በመሆን አገልግሏል።
ጋዜጠኛ አስፋው ባደረበት ህመም ምክንያት ወደ አሜሪካ ሄዶ ህክምናውን ሲከታተል በቆየበት የጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ቅዳሜ ጥር አራት ቀን 2016 ዓ.ም ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ ይታወሳል።
ከቀብር ሥነሥርዓቱ አስቀድሞ የጋዜጠኛ አስፋው መሸሻ አስክሬን ዘመድ ወዳጆቹ በተገኙበት በሚሊንየም አዳራሽ ሽኝት ተደርጎለታል። በመርሐ ግብሩ ላይ የጋዜጠኛው ልጅ ሳምሶን አስፋው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ለአባቱ ላደረጉት የክብር ሽኝት ከልብ አመሰግናለሁ ብሏል።
“አባቴ ጥሩ ሰው ነበር ፍቅርና ደግነቱን ለኔ አካፍሎኝ አልፏል” ያለው ሳምሶን፤ ኢቢኤስ ቴሌቪዥንም አባቱን ከማስታመም ጀምሮ ላበረከተው መልካም አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርቧል። በሥርዓተ ቀብሩ ላይ አድናቂዎቹ፣ የሙያ አጋሮቹ፣ ወዳጅ ዘመዶቹ እንዲሁም የተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትም ለቤተሰቦቹና ለሚያውቁት ሁሉ መፅናናትን ይመኛል።
ዳግማዊት ግርማ
አዲስ ዘመን ጥር 14/2016