የዛሬ የመጽሐፍ አጭር ዳሰሳችን ትኩረት የሚያደርገው ባለፈው ዓመት በጥር ወር 2010 ዓ.ም ለህትመት በቅቶ ገበያ ላይ የዋለውን ‹‹ምሁሩ›› የተባለውን መጽሐፍ ነው። የዚህ መጽሐፍ ፀሐፊ ዶክተር አለማየሁ አረዳ ሲባሉ መጽሐፉ በዋናነት የምሁር ምንነት፣ ማንነት፣ የምሁርነት መገለጫዎቹ እንዲሁም የኢትዮጵያ ምሁራን በሐገራችን የነበራቸው የታሪክ አረዳድና በአጠቃላይ በ21ኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ ላይ ያላቸው ሚና ምን እንደሚመስል ይተነትናል። በዋናነት ምሁርነት በሐገራችንና በዓለም አቀፉ ደረጃ ምን እንደሚመስል በሰባት ምዕራፎች ተከፋፍሎ የቀረበበት ነው።
ፀሐፊው በመጽሐፉ መጀመሪያ ባዶ ገፅ ላይ ‹‹ለአዲሱ ትውልድ የተበረከተ መጽሐፍ›› በማለት ስጦታቸው ለአዲሱ ትውልዱ እንደሆነ አስምረውበታል። የመጽሐፍ ሀያሲ እና ተንታኝ እሸቱ ብሩ እንዲህ ይላል “አዎ ልክ ነው! ለአዲሱ ትውልድ ብዙ ሃሳቦች ያስፈልጉታል። ዶክተር አረዳም በዚህ ተግባራቸው ሊመሰገኑ ይገባል። አዲሱ ትውልድም ወደ ምሁርነት መሄጃው መንገዱና ምሁርነት ምን እንደሚመስል በጥልቅ ይረዳ ዘንድ ይሄን መጽሐፍ ቢያነብ ተጠቃሚ ይሆናል።
ምሁራን ወገናቸውን በዕውቀት ከማብቃት አንፃር ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው። በዛው ልክ ደግሞ ሕዝቡ ራሱን በማስተማር፣ ችግሮች ሲከሰቱ ችግሮቹን የሚፈታበት መላን ያገኝ ዘንድ ለዕውቀት ቆርጦ መነሳት አለበት። ማሰብ፣ ማሰላሰል፣ መመራመር፣ ዕውቀትን መቃረም ይጠበቅበታል።”
ፀሐፊው የምሁራንን ግዴታዎችን በዘረዘሩበት ርዕስ ስር እንዲህ ይላሉ‹‹ራሱን በእውቀት ማዕከልነት አደራጅቶ የኑሮ ትልሙን የተገነዘበ ሕዝብ በድህነት አይኖርም። መብትና ነፃነቱን የሚጋፋ ሥርዓት ውስጥ አሜን ብሎ ማደር አይሆንለትም›› በማለት ይገልጻሉ።
አዎ! ለጨቋኞች አንገት የሚደፋ፣ ለአምባገነኖች እሺ ብሎ የሚኖር ሕዝብ ነፃነቱን አሳልፎ የሠጠ ነው። ዕውቀት ያለው ሕዝብ ጨቋኞች ምንም ያሕል የጦር መሣሪያ ቢኖራቸው በበሰለ ሃሳቡ፣ በአሸናፊ ዕውቀቱ ብቻ ድል ይነሳቸዋል።
ፀሐፊው የምሁርን ማንነትና ምንነትን በተነተኑበት ሃሳብ ላይ የተለያዩ ተመራማሪዎችን ብያኔ አስቀምጠዋል። ከዚህ ውስጥ በገጽ 17 ላይ የቶማስ ሶዌልን ‹‹ምሁር›› የሚለውን ቃል ትርጉም ሲዘረዝሩ‹‹ምሁር ሥራው ሀሳብ በማመንጨት ጀምሮ ያመነጨው ሃሳብ ላይ የሚያበቃ ነው›› ይላል ይሉናል። አዎ! ምሁርነት ሃሳብ ማመንጨት ላይ ብቻ ተወስኖ እንዲቀር የሚያደርግ ብያኔ ነው። ፀሐፊው እንደሚሉት ይህ ብያኔ የምሁሩን የአዕምሮ ብቃቱን፣ የሃሳብ ከፍታውን አያሳይም።
ከዚህ ሃሳብና ከሌሎች የምሁር ምንነት ትርጓሜዎችን መሠረት አድርገው ጠቅለል አድርገው ያስቀመጡት ድምዳሜ ይሄን ይመስላል‹‹ምሁር ማለት በመማርም ሆነ በሕይወት ልምድ የጨበጠውን ዕውቀትና የአዕምሮ ብቃት ተጠቅሞ በራሱም ሆነ ባለበት ሕብረተሰብ አስተሳሰብና አመለካከት ላይ ባንድ ወይ በሌላ መልኩ በሚያቀርባቸው ሐሳቦች ተፅዕኖ ማሳረፍ የሚችለውን ወይም የቻለውን ግለሰብ ወይም የማኅበረሰብ ክፍል ነው።›› ይላሉ።
በምዕራፍ ሁለት ላይ ስለምሁርነት፣ ምሁር ማንነት፣ ምንነትና መገለጫዎቹ በሚለው ርዕስ ስር የአያን ራንድን ‹‹ለአዲሱ ምሁር›› (For the new intellectual) የሚለውን መጽሐፍ በመጥቀስ ሲገልፁ፡-‹‹የሰው ንቃተ ሕሊና (Consciousness) ዕድገት ከሚያልፍባቸው ሦስት ደረጃዎች መካከል ሁለቱን ከእንስሳት ጋር ይጋራቸዋል። ሰውም ሆነ ሌላ እንስሳ በስሜት ሕዋሶቻቸው አማካይነት መልዕክቶችን ይቀበላሉ (Sensation):: ሁለቱም የተቀበሉትን መልዕክት ምንነት ይመዘግባሉ ወይም ምንነቱን ይለያሉ (Perception)::
ሰውና እንስሳት እነዚህን ሁለት የንቃተ ሕሊና ዕድገት ደረጃዎች ይጋራሉ (Sensation & Perception):: ሰው ግን በሕዋሶቹ ተቀብሎ የመዘገበውን መልዕክት አዕምሮውን ቋጥሮ ከያዛቸው ሌሎች መረጃዎች ጋር አዋህዶና አቀናጅቶ በማንጠር ፅንሠ ሃሳቦችን (Conception) መፍጠር ይችላል። ሦስተኛው የንቃተ ሕሊና ዕድገት ደረጃም ይኸው ነው። ይሄም የማሰብ ሂደት ነው። ከዚህ ሂደት ውስጥ አመክንዮ ትልቅ ሚና ይጫወታል።›› ይላሉ።
ይህ የአያን ራንድ ሃሳብ ከታላቁ ፈላስፋ ከአርስጣጢሊስ ጋር ይመሳሰላል። አርስጣጢሊስ ስለሠው ተፈጥሮ ሲናገር እንዲህ ይላል፡- ‹‹ሠው ሶስት ዓይነት ተፈጥሮ አለው። የመጀመሪያው ተፈጥሮው አካላዊ ነው። ይሄም ከእፅዋት ጋር ያመሳስለዋል። ሁለተኛው ስሜታዊው ተፈጥሮው ነው። ይሄ ተፈጥሮው ደግሞ በደመነፍስ ከሚመሩት እንስሳት ጋር ያመሳስለዋል። የሠው ልጅ ሶስተኛው ተፈጥሮ የምክንያታዊነት ተፈጥሮው ሲሆን፤ ይህ ተፈጥሮው ከሠው በስተቀር ለሌላ ለማንኛውም አይነት ፍጡር የተቸረ አይደለም››… በማለት ያብራራል።
አስገራሚ ሀሳብ ነው! ሰው ከሚያየው ነገር ሃሳብ መፍጠር ይችል ዘንድ እፁብ ድንቅ ውድ ስጦታ የሆነውን የማሰብ ፀጋውን ተጎናጽፏል። ከሠማው ነገር ምርጥ ጥበብን ሊቀምር ይችላል። ወደ ውጭ አይቶ ወደ ውስጥ ማሰብ ይችላል። ወደ ውስጥ ተመልክቶም ወደ ውጭ ሃሳቡን ማንፀባረቅና ተፅዕኖ መፍጠር ይሆንለታል። የውስጡን ሃሳብ በውጪው ሃሳብ እያቃረነና እያዋሃደ አዲስ ሃሳብ ይሠራል። የሰው ልጅ በስሜት ሕዋሳቱ ከሚረዳቸውና ከሚገነዘባቸው ነገር ተነስቶ ሌሎችን ሊያስረዳ የሚችል አዲስ ሃሳብ ይፈጥር ዘንድ ችሎታ ታድሎታል።
ሰው በውስጡ የተፈጠረለት ሕሊናው እንዲያስብ፣ ምክንያታዊ እንዲሆንና አዲስ ሃሳብ እንዲፈጥር ያስችለዋል። ሰው እንደእንስሳ ያየውን ብቻ አያምንም፣ ያላየውንም አይጠራጠርም። ለመጠርጠሩም ሆነ ለማመኑ በቂ ምክንያትን ማብቀል ይችላል። ምክንያቱ ከሃሳቡ፣ ሃሳቡ ደግሞ ከስሜት ሕዋሳቱ ምልከታና ንዝረት የሚፀነስና በመጨረሻም በምክንያታዊነት ታሽቶ ስራ ላይ የሚውለው ዕውቀቱ ነው።
ምሁራን ክፍትና ነፃ አዕምሮ ይኖራቸው ዘንድ ካልሰሩ ምሁርነታቸው ጥያቄ ውስጥ ይገባል። ምሁርነት ማለት በፅንፈኝነት ወይም በአንድ ጥግ ተሸሻጊነት ባህሪይ የሚገለፅ ሳይሆን በነፃ ሃሳቡና በክፍት አዕምሮው ሁሉንም የሚመረምር ነው። ምሁር የደረሰበትን ዕውቀት የሚያካፍል እንጂ የሚደብቅ አይደለም። አንዳንዶች እነሱ ብቻ አዋቂ እንዲሆኑ ያለቻቸውን ትንሽ ዕውቀት ይሰውራሉ። እውነተኛ ምሁራን ከሌሎች ያገኙትን ዕውቀት ለሌሎች ማጋራት የትክክለኛ ምሁር መገለጫ ነው። ፀሐፊው ከዚህ አንፃር እንዲህ ይሉናል፡-‹‹አዋቂ ሰው ዕውቀት የሚፈስባቸውን መስመሮች ሁሉ ክፍት እንዲሆኑ ይጥራል። ዕውቀትን ራሱ ዘንድ ከትሮ በማስቀረት ምሁርነቱን ማበልፀግ አይቻለውምና ለመወያየት፣ ለመከራከር፣ ለመደራደር በልዩነትም ለመከባበር አዕምሮውን ክፍት ማድረግ አለበት››
ሌላው መጽሐፉ በምሁራን ላይ የተነሱ ወቀሳዎቹን በዳሰሰበት ርዕስ ስር የአፍሪካውያን ምሁር የተወቀሱበትን ከብዙዎቹ አንዱን ኒኮላስ ኪሬሪ የተናገረውን እናያለን‹‹የአፍሪካ ምሁራን ዛሬም ቢሆን የአዕምሮ ተገዥነት ያልተላቀቃቸው በመሆኑ ለአፍሪካ የሚበጅ አፍሪካዊ አጀንዳ መቅረጽ አልቻሉም›› ይለናል።
እርግጥ ነው! አብዛኛው የአፍሪካ ምሁራን ለወገናቸው መሆን አልቻሉም። የምዕራባውያንን መፍትሄ ወደ አገራቸው ተጨባጭ ሁኔታ ሳይለውጡ ቀድተው ባመጡት ርዕዪት በአህጉሪቱ መሬት የነካና በተግባር የሚታይ ለውጥ ለማምጣት አልበቁም። «የሐገሩን ሰርዶ በሀገሩ» እንዲል ብሂሉ የወገናቸውን ችግር አጥንተው፣ ተጨባጭ ሁኔታውን መርምረው ለወገናቸው ለመድረስ አቅም አጥሯቸዋል። ከዛ ይልቅ አድርባይነት ተፀናውቷቸው ለመጣው መንግሥት ተገዝተው ሲኖሩ እናያለን።
ችግር ሲፈጠር፣ በወገን ላይ በደል ሲደርስ፣ ሐገር ለመውደቅ ስትንገዳገድ ዕውቀታቸውን ተጠቅመው አንድ መላ ከማምጣት ይልቅ በዝምታቸውና በግዴለሽነታቸው ወገናቸውን ያቆስላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ሙያዊ አስታያየት ሳይሆን አስተውሎት ነው። በዚህ መጽሐፉ ላይ ውብ የሆነ የቋንቋ አጠቃቀም፣ ጥልቅ የሆኑ የሃሳብ እና የስሜት ትስስሮሽ፣ ከፍ ያለ ስነ ጽሑፍ ይዘት በመኖሩ ያለው ማለት የሚቻለው መጽሐፉን አንብቡት ነው። መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 25/2011
አብርሃም ተወልደ