
አዲስ አበባ፡- በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የጥምቀት በዓል በድምቀትና በሰላማዊ መልኩ ተከብሯል፡፡ በጎንደር ከተማ የጥምቀት በዓል በፋሲለደስ ጥምቀተ ባሕር በርካታ የእምነቱ ተከታዮችና እንግዶች በተገኙበት በታላቅ ሃይማኖታዊ ሥርዓት በድምቀት ተከብሯል።
ብፁዕነታቸው ለበዓሉ ታዳሚዎች ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክት የቤተክርስቲያኒቱ ዘመን ተሻጋሪ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችና እሴቶች ሰላምን ፍቅርና ወንድማማችነትን የሚያጠናክሩ ናቸው።
ሕዝበ ክርስቲያኖች በዓሉን ስናከብር ስለ ሰላም ስለ ሕዝቦች አንድነትና አብሮነት በጥልቀት በማሰብና በማስተማር ሃይማኖታዊ አስተምህሮቱን በእለት ተእለት ሕይወታችን ልንተገብረው ይገባል ብለዋል።
ሃይማኖታዊ እሴቱን ጠብቆ በየዓመቱ የሚከበረው የጥምቀት በዓል የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፍጹም ትሕትና ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ተጉዞ በአገልጋዩ በቅዱስ ዮሐንስ እጅ የተጠመቀበትን እለት የምናስብበት ዓብይ በዓል ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በዓሉ ባማረና በደመቀ ሥርዓት መከበሩ የእምነቱን ተከታዮች ሃይማኖታዊ የአብሮነት እሴትና አንድነት የሚጠናክር ነው ያሉት ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ፤ የዛሬ ዓመት በሰላም ያድርሰን ሲሉ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
የጥምቀት በዓል በመቐለ ከተማ፣ በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሰቆጣ ከተማ እና በባሕር ዳር ከተማ በደመቀ መልኩ ተከብሯል።
የሲዳማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ በሀዋሳ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን በተከበረው የጥምቀት በዓል ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ጥምቀት የአብሮነትና የመተሳሰብ እንዲሁም የርህራሄ ተምሳሌት መሆኑን ተናግረዋል።
በዓሉ ሲከበር አንድነትና መተሳሰብን በማጠናከር ሊሆን እንደሚገባ ገልጸው፣ የጥምቀት በዓል ዕሴት የሆነውን ሰላምን የማምጣትና የማጠናከር መንገድ ነው ብለዋል።
”እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገው እጅግ ቀላል፣ ዋጋ የማያስከፍል፤ ጠቃሚ ነገር ነው እሱም ፍቅር ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
”እርስ በርስ በመዋደድና እኛ የሚያስፈልገን ለሌላውም እንደሚያስፈልግ በመረዳት ለአብሮነትና መተሳሰብ መጠናከር እንዲሁም ለሰላም መጽናት የሚጠበቅብንን በቁርጠኝነት ልንወጣ ይገባል” ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የጥምቀት በዓል በወንጪ-ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም ፕሮጀክት በወንጪ ሐይቅ በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ተከብሯል።
በበዓሉ ላይ የሃይማኖት አባቶች፣ የእምነቱ ተከታዮችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
የደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና የሸገር ከተማ ሀገረ-ስብከት ሊቀ-ጳጳስና የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም የበላይ ጠባቂ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ፤ በዓሉ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል ብለዋል።
ሐይቁ ለበዓሉ ማክበሪያና ለቱሪስት መዳረሻነት የሚያስፈልገው መሠረተ-ልማት በመሟላቱ በማራኪ ድባብ እንዲከበር ማስቻሉን ገልጸዋል።
በጋምቤላ ከተማና አካባቢው የከተራና የጥምቅት በዓል ሃይማኖታዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ በደመቀ ሥነ-ሥርዓት ተክብሯል። ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል በክብረ በዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ምዕመኑ በዓሉን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት፣ በማገዝና በመደገፍ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል ዲያቆን ይፍረደው ጥሩነህ የኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳን ዝቅ ብሎ በመጠመቅ ትህትናን፣ ፍቅርን፣ አብሮነትን ያስተማረበት በመሆኑ በዓሉን በዚሁ አግባብ እያከበሩት መሆኑን መግለጻቸው ኢዜአ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ጥር 12 ቀን 2016 ዓ.ም