አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም በየመን በሁቲ አማጽያን ላይ የአየር ጥቃት ከፈቱ

የአሜሪካ እና የዩናይትድ ኪንግደም ጥምር ኃይል በየመን የሁቲ አማጽያንን ዒላማ በማድረግ የአየር ጥቃት ከፈቱ። ሁለቱ ሀገራት በጥምረት ጥቃት ከጀመሩ በኋላ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ ጥቃቱ በኢራን የሚደገፉት የሁቲ አማጽያን በቀይ ባሕር ላይ በመርከቦች ላይ ላደረሱት ጥቃት ምላሽ እንደሆነ ተናግረዋል።

የሁቲ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም “ከፍተኛ ዋጋ” እንደሚከፍሉ አስጠንቅቋል። የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ እንዳሉት፣ የሮያል አየር ኃይል ጥቃቱን የከፈተ ሲሆን፣ ይህ ጥቃት “ውስን፣ አስፈላጊና ራስን ለመከላከል የተፈጸመ ተመጣጣኝ እርምጃ ነው” ብለዋል።

ኔዘርላንድስ፣ አውስትራሊያ፣ ካናዳ እና ባሕሬን ለዚህ ጥቃት ድጋፍ መስጠታቸው ተገልጿል።ጥቃቶች ተፈጽመዋል የተባሉት በየመን መዲና ሰንአ፣ በሁቲ በተያዘ የቀይ ባሕር አካባቢ ሁዳያህ፣ ዳህማር እና በሰሜን ምዕራብ ከፍተኛ የሁቲ አማጽያን ይዞታ ባለበት ሳዳ ነው።የሁቲ አማጽያን አብዛኛውን የመን ይቆጣጠራሉ።

ለሐማስ ድጋፍ ለመስጠት ወደ እስራኤል እየተጓዙ የነበሩ መርከቦች ላይ ጥቃት ሲሰነዝሩ ቆይተዋል።የሁቲ መሪ ሞሐመድ አል-ቡካቲ፣ አሜሪካ እና ዩኬ “በቅርቡ በታሪካቸው ትልቅ ስህተት መሥራታቸውን ይገነዘባሉ” ብሏል።“የመን ላይ ጦርነት መክፈታቸው ስህተት ነው። ከቀደመው አልተማሩም” ብሏል።

በቀይ ባሕር ላይ የሁቲ አማጽያን መርከቦች ላይ ባለፉት ሳምንታት በፈጸሟቸው ጥቃቶች ሳቢያ ግዙፍ የባሕር መጓጓዣ ድርጅቶች ሥራ ለማቋረጥ ተገደው እንደነበር ይታወሳል።የኤሌክትሪክ መኪና አምራቹ ተስላ በግብዓት መስተጓጎል ሳቢያ የጀርመን፣ በርሊን ምርቱን ማቆሙን ገልጿል።

በአማጽያኑ ላይ የደረሰው የአየር ጥቃት በቀጣይ ሁቲዎች ጥቃት እንዳይሰነዝሩ መልዕክት ሊያስተላልፍ እንደሚችል ምዕራባውያን መሪዎች ያምናሉ።በአሜሪካ፣ ዋይት ሀውስ ፊት ለፊት ‘ከየመን እጃችሁን አንሱ’ የሚል መፈክር ያለው የተቃውሞ ሰልፍ ተካሂዷል።‘የመን ትኑርበት’ የሚሉና ሌሎችም መፈክሮች ተሰምተዋል።

የአውስትራሊያ፣ ባሕሬን፣ ካናዳ፣ ዴንማርክ፣ ጀርመን፣ ኔዘርላንድስ፣ ኒው ዚላንድ እና ኮርያ፣ አሜሪካ እና ዩኬ መንግሥታት በጋራ መግለጫ አውጥተዋል።ሁቲዎችን በተመለከተ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ “ስምምነት” ላይ መድረሱን መግለጫው ይጠቁማል።“የግልና የጋራ መከላከል መብትን በተከተለ ሁኔታ” የአየር ጥቃቱ መፈጸሙን አገራቱ ባወጡት መግለጫ አካተዋላል።

“እነዚህ ዒላማ ያላቸው ጥቃቶች የሁቲን አቅምና መዋቅር ለማዳካም ነው ያለሙት። የሁቲ እንቅስቃሴ በዓለም ቀዳሚው የውሃ አካል ላይ ዓለም አቀፍ ንግድን አውኳል” ብለዋል።ግባቸው “ቀውሱን ማብረድና አካባቢውን ማረጋጋት” እንደሆነም አክለዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ባለፈው ወር ባወጣው መግለጫ የሁቲ አማጽያን በቀይ ባሕር ላይ በሚጓዙ መርከቦች ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት እንዲያቆሙ ጠይቋል።ሳዑዲ አረቢያ በበኩሏ አሜሪካ እና አጋሮቿ ከጥቃትና ነገሩን ከማባባስ “እንዲቆጠቡ” አሳስባለች።የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ “ከፍተኛ ስጋት አለን” ማለታቸውም ተዘግቧል።

የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ዋና ሐጸፊ ሎይድ ኦስተን፣ የአየር ጥቃቱ የተፈጸመው በሁቲ ተሽከርካሪዎች፣ መርከቦች፣ የአየር መቆጣጠሪያዎችና ሌሎችም መገልገያዎች መሆኑን ተናግረዋል።እስካሁን ወደ 12 ገደማ ዒላማዎች መመታታቸው ተገልጿል።ባይደን ተጨማሪ ርምጃዎች ሊወሰዱ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።

አሜሪካ እና አጋሮቿ “ጥቃትን ዝም ብለን አንቀበልም። በዓለም ዋነኛ የንግድ ቀጣና እርምጃ ሲወሰድም ዝም አንልም” ብለዋል። በቀይ ባሕር ላይ እየደረሱ ያሉ ጥቃቶች የማያቆሙ ከሆነ በሁቲ አማጽያን ላይ ርምጃ እንደሚወሰድ ምዕራባውያን አገራት ባለፉት ሳምንታት ማስጠንቀቂያ ሲሰጡ ቆይተዋል።

የየመን ሁቲ አማጺያን በቀይ ባሕር ላይ የሚያልፉ ዕቃ ጫኝ መርከቦችን በሚሳኤል እና በድሮን ዒላማ ማድረጋቸው የነዳጅ እና የሌሎች ምርቶችን ዋጋ ከፍ ያደርጋል መባሉን ይታወሳል።ሰፊ የየመን ግዛትን ተቆጣጥረው የሚገኙት ሁቲ አማጺያን ከእስራኤል እና ከሐማስ ጦርነት መቀስቀስ ወዲህ በቀይ ባሕር በኩል በሚያልፉ ግዙፍ የጭነት መርከቦች ላይ ጥቃት ሲሰነዝሩ ቆይተዋል።

አማጺያኑ ከእስራኤል ጋር ጦርነት ውስጥ ለገባው ሐማስ ያላቸውን ድጋፍ በይፋ ከገለጹ በኋላ፣ በቀይ ባሕር በኩል አድርገው ወደ እስራኤል የሚያቀኑ መርከቦችን ዒላማ እንደሚያደርጉ በይፋ አሳውቀዋል። የሁቲ አማጺያን ባለፉት ሳምንታት ወደ ተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ነዳጅ እና የተለያዩ ምርቶችን ጭነው የሚንቀሳቀሱ ግዙፍ መርከቦችን በሚሳኤል እና በድሮን ሲያጠቁ እና እገታ ሲፈጽሙ ነበር።

ታዲያ ይህ ስጋት ውስጥ የከተታቸው የዓለማችን ዋነኛ የመርከብ ጭነት ማጓጓዣ ድርጅቶች ቀይ ባሕርን ከመጠቀም ይልቅ ረዥም ጊዜ እና ብዙ ነዳጅ አባክነው በደቡብ አፍሪካ በኩል አድርገው ወደ መዳረሻቸው እያቀኑ መሆኑ ይታወሳል።

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You