በመዲናዋየሚሰጡ 11 አገልግሎቶችን ለሶስተኛ ወገን የማስተላለፍ ሂደት ተጀምሯል

አዲስ አበባ፡- በመዲናዋ ለሶስtኛ ወገን ሊተላለፉ ከታቀዱ 24 አገልግሎቶች መካከል 11ዱን ለሶስተኛ ወገን የማስተላለፍ ሂደት መጀመሩን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ገለጸ።

በቢሮው የሰው ሀብት ልማት አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ አቶ መላኩ ታምሩ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጀት እንደገለጹት፤ 11 የአገልግሎት አይነቶችን ለሶስተኛ ወገን የማስተላለፍ (የአውትሶርስ) ሂደት ተጀምሯል።

በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙና ለሶስስተኛ ወገን ተላልፈው የሚተገበሩ የአገልሎት አይነቶች 24 መሆናቸውን የገለጹት አቶ መላኩ፤ ከዚህ ውስጥ 11ዱን አውትሶርስ ለማድረግ የጨረታ ሰነድ የማዘጋጀት ተግባር በመጠናቀቁ ጨረታው በቅርቡ ይጀመራል ብለዋል።

የተለያዩ ድርጅቶች ጨረታውን ካሸነፉ አገልግሎቶቹን የሚያቀርቡበት ዝርዝር ሁኔታ እንደሚመቻች አስረድተዋል።

አቶ መላኩ እንደተናገሩት፤ ለሶስተኛ ወገን የሚተላለፉ አገልግሎቶች ከኢንዱስትሪ ልማት፣ ከስራና ክህሎት፣ ከፕላን ኮሚሽን፣ ከየመሬት ልማት አስተዳደር፣ ከመሬት ምዝገባ መስሪያ ቤቶችና በሌሎች ተቋማት የሚገኙ ናቸው።

ከዚህ በፊት አንዳንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የፅዳትና ጥበቃ ሠራተኞችን በእራሳቸው ከመቅጠር በተለየ አውትሶርስ ማድረጋቸውን በማስታወስ፤ የአገልግሎቶቹ አውትሶርስ መደረግ ነዋሪውን በስፋት ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።

የመዲናዋን አገልግሎቶቹን አውትሶርስ ማድረጉ አገልግሎቶችን በሰፊው ተደራሽ ከማድረግ በተጨማሪ የመንግሥት ተቋማት ጋር ያለውን የሥራ መጨናነቅ የሚያስቀር ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ለእንግልት የተጋለጡ የነበሩ ተገልጋዮችን በተፈለገው ቦታ ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል አሠራር በመሆኑ በሰፊው ተግባራዊ እንደሚደረግ አመላክተዋል።

በአዲሱ አሠራር መሠረት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ይሠራል ያሉት አቶ መላኩ፤ ውጤታማነቱ እየተመዘነ አመርቂ ውጤት ያላመጡትን የሶስተኛ ወገን አገልግሎቶች እንዲቋረጡና በተቋማት እንዲሰጡ ይደረጋል ሲሉ አስረድተዋል።

አቶ መላኩ እንደገለጹት፤ በአሰራሩ መሠረት የበለጠ ውጤት ከተገኘበት ደግሞ የአውትሶርስ ሂደቱ እንዲስፋፋ ይደረጋል።

ስለ አውትሶርስ ሂደቱ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ተሞክሮ ለማግኘት ጥረት እንደተደረገ ገልጸውም፤ በዚህም በምን መልኩ በመሥራት ውጤታማ መሆን ይቻላል፤ አገልግሎቶቹን በምን አይነት መልኩ ነው አውትሶርስ መደረግ ያለባቸው የሚሉ እና ሌሎች ጥያቄዎች በምሁራን ተጠንተዋል ብለዋል።

በመሆኑም በምሁራን የተጠኑትን እውቀቶች ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማስተሳሰር ተግባራዊ እንደሚደረጉ አቶ መላኩ አስታውቀዋል።

አገልግሎቶችን ለሶስተኛ ወገን የማስተላለፍ (አውትሶርስ) አሠራር በመንግሥት የሚሰጡ አገልግሎቶች በኮንትራት ወደ ግለሰቦችና ማህበራት በማዞር ሕዝቡን የሚያገለግልበት አሠራር እንደሆነም ተገልጿል።

አመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You