መንግስት፤ አሰሪ ወገንም ሆነ ሰራተኛው የማይነጣጠሉ መሆናቸውን ያምናል ኢንቨስትመንቱ ለአገር ዕድገትና ልማት አስፈላጊ ነው። ገበያው ውስጥ መቀጠልና ተወዳዳሪ መሆን ይኖርበታል የሚል አቋም አለው ወዲህ ደግሞ ሰራተኛው መሰረታዊ የስራ ላይ መብቶቹ እየተከበሩለት መቀጠል ይገባዋል በሁለቱ መካከል የሚኖረው ሰላማዊ ግንኙነት ለምርትና ምርታማነት፤ እንዲሁም ለኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝነት አለው ሆኖም፤ የሁለቱ አካላት አለመግባባት ላለፉት ዓመታት ቅሬታ ሲነሳበትና ሲያወዛግብ ቆይቷል
በተለይም በኢንዱስትሪው ዘርፍ ከፍተኛ ቅሬታ እየተነሳበት ያለውን ዝቅተኛ የክፍያ መጠን ሮሮ ይቀርፋል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ህግ ተፈትሾ ማሻሻያ እየተደረገበት ይገኛል ማሻሻያው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተቀባይነት አግኝቷል ወደህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ተመርቷል ማሻሻያው የደረሰው ምክር ቤትም ጉዳዩ የሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ በዝርዝር እንዲመለከተው መርቶታል በቅርቡ የመጨረሻ ውሳኔ ያገኛል ተብሎ እየተጠበቀም ይገኛል አዋጁ ሲጸድቅ የሚነሱ ችግሮችን እንደሚቀርፍም ይጠበቃል በአሰሪውና በሰራተኛው መካከል የሚኖረውን ግንኙነት ሰላማዊ በማድረግም ምርትና ምርታማነትን ያሳድጋል የሚል እሳቤ አስጨብጧል
የመንግስት ተጠሪ አምባሳደር መስፍን ቸርነት የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ 377/1996 አዋጅን ማሻሻል ያስፈለገበትን ምክንያቶች ለምክር ቤቱ አባላት ሲያብራሩ፤ አሰሪና ሰራተኛ የስራ ግንኙነታቸው መሰረታዊ በሆነና በህግ አግባብ በተደነገጉ መብቶችና ግዴታዎች ላይ በመመስረት አስተማማኝ የኢንዱስትሪ ሰላም ጠብቀው እንዲሰሩ ማድረግ ጠቃሚ መሆኑን መንግስት ግንዛቤ የወሰደበት ጉዳይ ለአዋጁ ማሻሻል አንዱ ምክንያት ነው ይላሉ
ሰራተኞች እና አሰሪዎች የየራሳቸው ማህበራት ኖሯቸው በሙሉ ፈቃደኝነት እና ነጻነት ላይ የተመሰረቱ ማህበራትን በማቋቋም በመረጧቸው ወኪሎቻቸው እንዲወከሉ ማድረግ ሌላው ነው በወኪሎቻቸው አማካኝነት መብትና ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ ግዴታቸውንም በአግባቡ ለመወጣት የሚያስችላቸውን ስርዓት መዘርጋት እና ማጠናከር አስፈላጊነቱ ስለታመነበት ማሻሻል አስፈላጊ ከሆኑ ነጥቦች ውስጥ ይካተታል ባይ ናቸው አምባሳደር መስፍን
እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ ለኢንቨስትመንትና አገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት ግቦች መሳካት ምቹ ሁኔታ መፍጠር አስፈልጓል የሁለትዮሽ እና የሶስትዮሽ ማህበራዊ ምክክር አሰራር ለማጠናከር በህግ መሰረት የማማከርንና የመቆጣጠርን ተግባር እያመጣጠነ ስራውን የሚያከናውን አካል ስልጣንና ተግባር መዘርዘር እና መወሰን አስፈላጊ መሆኑ ተቀባይነት በማግኘቱም ለማሻሻያው ሌላው ምክንያት የሆነ ጉዳይ ነው
የፖለቲካ ኢኮኖሚ ከማህበራዊ ፖሊሲ ጋር የተገናዘበ፤ ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነት ጋር የተገናኘ፤ ሌሎች ህጋዊ ሰነዶች ጋር የተጣጣመ ህግ ለማውጣት እና በስራ ላይ ያለውን የአሰሪና ሰራተኛን አዋጅ በአዲስ መተካት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ መሆኑንም አምባሳደር መስፍን ይጠቅሳሉ
ረቂቅ አዋጁ እንዳስቀመጠውም፤ በይዘት ውስጥ ሲታይ በህጉ ውስጥ “የስራ መሪ” በሚለው ትርጉም ውስጥ “የስነ ስርዓት እርምጃ የሚወስድ” ተግባሮችን የሚያከናውን የሚለውን ሀረግ ከስራ መሪነት ትርጉም እንዲወጣ ተደርጓል አንዳንድ ሰራተኞች የህጉን ክፍተት በመጠቀም እስከ አራት ቀናት በመደዳው በመቅረት በአምስተኛው ቀናቸው ወደ ስራ የሚገቡ በመኖራቸው እና በእዚህም የስራ ስነ ምግባር እየተጎዳ በመሆኑ ይህንን መከላከል የሚያስችል ድንጋጌ በረቂቅ ህጉ ተካትቷል
ሌላው ማሻሻያ የተደረገበት ጉዳይ ቢኖር ለግሉ ዘርፍ ዝቅተኛ ደመወዝ በህግ ሊቀመጥ ይገባል ወይስ አይገባም በሚለው ጉዳይ እልባት የማስቀመጥ ነው በተለያዩ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የተለያዩ ሃሳቦች የሚንሸራሸሩ ቢሆንም፤ እስካሁን የፖሊሲ ውሳኔ ሳይተላለፍበት ቆይቷል ሲል ማሻሻያ አዋጁ ያትታል ጉዳዩ በባለሙያዎችና በህግ አውጭው ታይቷል፣ ውይይትም ተደርጎበታል በውይይቱም ሊወሰን እንደሚገባ ታምኖበታል በረቂቁ እንዲካተት ተደርጓል በማለት ደንግጓል
በሚሻሻለው አዋጅ አንቀጽ 55 ንዑስ አንቀጽ (2) የደመወዝ ቦርድ እንደሚቋቋም የተቀመጠው ሃረግ እንደሚያመለክተውም፤ የሃገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት፤ የስራ ገበያ ሁኔታ እና የመሳሰሉትን እያስጠና ዝቅተኛ ደመወዝ የሚወስን የመንግስት፤ የአሰሪና ሰራተኛ ተወካዮች፤ እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት የደመወዝ ቦርድ ስለሚቋቋምበትና ተግባርና ሃላፊነቱ ስለሚወሰንበት ሁኔታ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ እንደሚደነገግ አስቀምጧል በስራ ደንብ ወይንም በህብረት ስምምነት ያልተወሰኑ የደመወዝና ሌሎች ጥቅማ ጥቅም አወሳሰን በግል እንዲሻሻል የሚያደርግ አንቀጽም እንዲካተት ተደርጓል
በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሰላማዊ ኢንዱስትሪ ግንኙነት ዳይሬክተሩ አቶ ፍቃዱ ገብሩ እንደሚሉት፤ በማሻሻያ አዋጁ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ተካሂዷል ቀጥታ ኢንቨስትመንት ወደ አገር ውስጥ ያስገቡ ተቋማት፤ ባለሃብቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በምክክሩ ተካትተውበት ውይይት ተደርጓል መንግስት ሁለቱም ወገኖች የማይነጣጠሉ መሆናቸውን ያምናል ኢንቨስትመንቱ አስፈላጊ ነው ገበያው ውስጥ መቀጠልና ተወዳዳሪ መሆን አለበት በሌላ በኩል ደግሞ፤ የሰራተኛው መሰረታዊ የስራ ላይ መብቶች እንዲከበሩ ማድረግ ይገባል በሁለቱ መካከል የሚኖረው ሰላማዊ ግንኙነት የግድ ያስፈልጋል ይህ እንዲሆንም መደራጀት ጠቃሚ ነው ይላሉ። አቶ ፍቃዱ፤
ማህበራዊ ፍትህ እንዲሰፍን፤ በአሰሪውና በሰራተኛው መካከል የሚኖረው ግንኙነት ሰላማዊ እንዲሆን ሁልጊዜም ውይይት ማድረግ ይኖርባቸዋል ለዚህም ረቂቅ ህጉ ሁሉንም በሚያበረታታ መልክ ተቀምጧል የደመወዝ መነሻ እንደሚቋቋም ያስቀመጠው መልካም የሚባል ነው ህጉ ተግባራዊ ሲሆን የድርጅቶችን የመክፈል አቅም ያገናዝባል፣ የሰራተኛውንና የቤተሰቡን ፍላጎትም ከግምት ውስጥ ያስገባል
ቀደም ብሎ ያልነበረ አሁን በረቂቅ አዋጁ ከተካተተው መካከል በስራ ቦታ የጾታዊ ትንኮሳና ከዚህ ጋር የተገናኙ የመብት ጥሰቶች ህገ ወጥ ድርጊት መሆናቸው ተቀምጧል ሰራተኛው እንዲህ አይነት የመብት ጥሰት ከደረሱበት በህግ የሚያስጠይቅ፤ ካሳ የሚያስከፍል የሚደነግግ ህግም ተካትቶበታል የቅጣት ድንጋጌዎቹም ማሻሻያ ተደርጎባቸዋል
መደራጀት መሰረታዊ መብት ነው የመደራጀት ዋና ዓላማ ለመተባበር እና የጋራ ጥቅምን ለማረጋገጥ ነው እንጂ፤ አንዱ ሌላውን ለመክሰስ ወይም ለመጣል አይደለም በተለይም በአሰሪና በሰራተኛ መካከል ማህበራዊ ግንኙነቱ ወሳኝ ነው ማህበራዊ ግንኙነት ደግሞ በመሰረቱ መጠቃቀም ይፈልጋል አሰሪው ከሰራተኛ ጥሩ ምርታማነትን ይጠብቃል ሰራተኛ ደግሞ ከአሰሪው የተሻለ ጥቅም ይጠብቃል ይህንን ለማረጋገጥም ሁል ጊዜ ምክክር ወሳኝ ነው ይህንን አስተሳሰብ ዕውን ለማድረግ መደራጀት ወሳኝ ነው ስለዚህ በስራ ቦታ ህግ ተደራጁ ብሎ ስላስቀመጠ ብቻ ሳይሆን፤ መደራጀት ትርፉ ሁለቱንም ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ይላሉ
እንደ አቶ ፍቃዱ ማብራሪያ፤ በሁለቱ መካከል መልካም ግንኙነት ከተፈጠረ እርስ በእርስ ተግባቦቱ ይኖራል በተግባቦት የተመሰረተ ግንኙነት ደግሞ በጋራ መግባባት ላይ የተመሰረተ ተጠቃሚነትን ያሳድጋል ሰራተኛው ጥያቄዎቹ ምላሽ ያገኛሉ ጥያቄዎቹ ምላሽ ሲያገኙለት የሚያስጨንቁት ገዳዮች አይኖሩም፡ ምክንያቱም ደመወዙ የሚያድግበት ስርዓት አለ። የጤና አገልግሎት ጉዳይ በግንኙነት ህጉ ተካትቷል በመሆኑም ነጻ በሆነ መንገድ ለምርት ዕድገት የሚሰራ ይሆናል
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር አቶ አበበ አበባየሁ፤ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳትና ኢንዱስትሪው በኢትዮጵያ ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ዕድገት እያሳየ መምጣቱን ያነሳሉ በተለይም የኢንዱስትሪ ፓርኮችን መገንባት ተከትሎ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በዘርፉ ለመሰማራት ወደአገር ውስጥ ገብተዋል በዘርፉ ለመሳተፍ አገር ውስጥ ሲገቡ ወጣቱ በሰፊው የስራ ዕድል መፍጠር ነው
የስራ ዕድል ሲባል በቂ የሆነ ደመወዝ ማግኘት አለባቸው የሚለው ጥያቄ አግባብነት አለው ሆኖም በባህሪው የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪው በየትኛውም አገር ከፍተኛ የደመወዝ ዋጋ ካለባቸው አገሮች ዝቅተኛ ደመወዝ ወዳለባቸው አገሮች ሲሄድ የነበረ፤ በታሪኩም ይህንን መልክ የያዘ ኢንዱስትሪ መሆኑን አቶ አበበ ይጠቅሳሉ
በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪ ቀድማ የምትታወቀው ታላቋ ብሪታንያ፣ በመቀጠልም ወደ ደቡብ ምስራቅ ኢስያ አገሮች ቻይና በዘርፉ የሚታወቁ መሆናቸውን ይጠቁሙና፤ ቻይና ከኢኮኖሚ ዕድገታቸው ጋር ተያይዞ የደመወዝ መጠኑ ከፍ እያለ መሄድን ተከትሎ ወደተለያዩ የአፍሪካ አገሮች መሄዱን አቶ አበበ ያነሳሉ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪው ወደ ባንግላዲሽ፤ ቬትናምና የመሳሰሉ አገሮች እየሄደ ይገኛል ሲሉም ይናገራሉ
ኢትዮጵያ ባለሃብቶችን ለመሳብ የምት ጠቀምበት አንዱ ስልት ሰፊ የሆነ የሰራተኛ አቅርቦት አለ የሚለው ነው ይህ ማለት ግን ርካሽ ጉልበት አለ ማለት አይደለም ርካሽ የሰው ጉልበት የሚባል የለም እንደ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንም ኢንቨስትመንትን በምናስተዋውቅበት ጊዜ ሰፊ የሆነ የሰራተኛ አቅርቦት ተወዳዳሪ በሆነ የደመወዝ ዋጋ መኖሩን ከመግለጽ ባለፈ ቃሉ ርካሽ ተብሎ አይተዋወቅም በታሪክም የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪው ሰፊ የሰው ሃይል የሚጠይቅ በመሆኑ የሚሄደውም በተመጣጣኝ ዋጋ የሰራተኛ አቅርቦት ወዳለበት አገር ነው
ለዚህም ወደ ኢትዮጵያ ባለፉት ሶስትና አራት ዓመታት ብዙ ባለሃብቶች አገር ውስጥ ገብተው እየሰሩ ናቸው አሁን ሰራተኞቹ እያገኙት ያለው የደመወዝ መጠን ኑሯቸውን መምራት በሚችሉበት ሁኔታ መሆን እንዳለበት ይታመናል ይህንን ለማድረግ ደግሞ ህጉ ዝቅተኛ የደመወዝ ክፍያ መጠንን አላስቀመጠም መንግስት አሁን ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶት የአሰሪና ሰራተኛን አዋጅ እያሻሻለ ይገኛል ይህ አዋጅ የሰራተኞች መብት ሙሉ በሙሉ ማስከበር የሚችልበት አግባብ ይኖረዋል አዋጁ ሲጸድቅ ዝቅተኛ ደመወዝ ሊሆን የሚችልበትን በአንዳንድ ቦታዎች ላይ በድርድር፤ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ደግሞ በግልጽ ሊቀመጥ በሚችል መልኩ የሚፈታበትን የህግ መሰረት እናገኛለን ነው የሚሉት፤ አቶ አበበ፤
በሰራተኞችና በአሰሪዎች መካከል ያለው ግንኙነት መልካም እንዲሆን፤ የኢንዱስትሪው የስራ ሁኔታም ሰላም የሰፈነበት እንዲሆን ለማስቻል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር አዋጁ ተዘጋጅቷል አዋጁ የሰራተኞችን መብት ባስከበረ፣ አገሪቱም ለኢንቨስትመንት ተወዳዳሪነቷንና ተመራጭነቷን ባስጠበቀ መንገድ ሰላማዊ የስራ ሁኔታን ለማስከበር ያስችላል
የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጌጎ ተስፋዬ፤ ኢትዮጵያ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር የኢኮኖሚ ሽግግር በማድረግ ላይ የምትገኝ መሆኗን ይገልጻሉ ሽግግሩም በማህበራዊም ሆነ በኢኮኖሚው ላይ ተጽዕኖ በማያስከትል መንገድ ሊሆን እንደሚገባውም ያመለክታሉ በኢንዱስትሪ ፓርኮች፤ በተለይም በጨርቃ ጨርቅ ዘርፉ እየተነሱ ካሉ ችግሮች መካከል የመደራጀት መብትና ለስራቸው በቂ ክፍያ አለመክፈል በችግር የሚነሳ መሆኑን ይጠቅሳሉ ይህንን አስመልክቶ ጥናት መሰራቱን፤ ሁሉንም የሚዳስስ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱንም ይጠቁሙና፤ ፍኖተ ካርታው ሲሰራ የሌሎች አገሮች ተሞክሮ ታይቶ መሆኑን ይጠቁማሉ
በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ተወካይ እንዳልነበረ የሚጠቁሙት ዶክተር ኤርጌጎ፤ በእያንዳንዱ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ተወካይ እንዳልነበረ ይገልጻሉ አሁን በእያንዳንዱ የኢንዱስትሪ ፓርክ ተወካይ በመመደብ የአሰሪውንና የሰራተኛውን ጥቅም እና መብት ሚዛናዊ በሆነ መልኩ የማስተናገድ ስራ መጀመሩን ዶክተር ኤርጌጎ ይገልጻሉ
ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ከመወሰን ጋር ተያይዞ ጥያቄዎች ሲነሱበት የነበረ መሆኑን በመጠቆምም፤ ሰራተኛው ጥያቄውን ሲያነሳ ሊያኖር የሚችል፤ በቂ ገንዘብ ማግኘቱን ማዕከል አድርጎ ሊሆን እንደሚገባ እንዲሁም፤ አሰሪውም ሲከፍል የሚያዋጣውን አማካኝ ዋጋ የሚያነሳበት ሃሳብ አለ ሲሉ ያነሳሉ በሁለቱ ወገኖች መካከል የሚነሳውን የተራራቀ ሃሳብ ወደ አንድ የማምጣት ስራ አስፈላጊ እንደነበረ በመጠቆምም፤ በሚሻሻለው የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ጉዳዩ መካተቱ በጎ መሆኑንም ያነሳሉ::
አዲስ ዘመን ግንቦት 21/2011
ዘላለም ግዛው