የኢትዮጵያ ዓመታዊ ምርት በአፍሪካ የግብርና እድገት ፕሮግራም የተቀመጠውን ግብ አሳክቷል

– ባለፉት አምስት ወራት ከ11 ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ምርት ተሰብስቧል

– ለመስኖና ለበልግ የሚያስፈልገው ማዳበሪያ ግዥ ሙሉ ለሙሉ ተፈጽሟል

– ከ2015/16 የመኸር ምርት 513 ሚሊዮን ኩንታል ይጠበቃል

አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ የግብርናው ዘርፍ ዓመታዊ የምርት ዕድገት በአፍሪካ የግብርና እድገት ፕሮግራም የተቀመጠውን ግብ ማሳካቱ ተገለጸ። ባለፉት አምስት ወራት ከ11 ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ምርት ተሰብስቧል።

የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ የሚኒስቴሩን የ2016 በጀት ዓመት የአምስት ወራት አፈጻጸም አስመልክተው ትናንት በሰጡት ማብራሪያ፤ በ10 ዓመቱ መሪ ዕቅድ የግብርና አጠቃላይ ምርትን በስድስት በመቶ ለማሳደግ ግብ ተጥሎ ለአፈጻጸሙ ስኬታማ ርብርብ ተደርጓል ብለዋል።

ባለፉት ሦስት ዓመታት አማካይ ውጤቶች ዓመታዊ የምርት እድገት ስድስት በመቶ ያህል መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ይህም በአፍሪካ የግብርና እድገት ፕሮግራም ከተቀመጠው ግብ ጋር ሲታይ ተመሳሳይ መሆኑን አስታውቀዋል።

በ2015 ዓ.ም የተደረሰበት የግብርና እድገት እንደ አህጉር በአፍሪካ ደረጃ አጠቃላይ የግብርና ልማት ፕሮግራም ማዕቀፍ ያስቀመጠውን የስድስት በመቶ የዕድገት ምጣኔ ያሟላ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ ወጤት ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ በተፈጥሮአዊና በሰው ሰራሽ ክስተቶች እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ በተፈጠሩ አሉታዊ ጫናዎች እየተፈተነች የተመዘገበ አፈጻጸም መሆኑን አመላክተዋል።

በማክሮ ኢኮኖሚው ውስጥ የግብርናው ዘርፍ የተሰጠውን ተልዕኮና ሥራ እየተወጣ ይገኛል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ባለፉት አምስት ወራት የግብርናው ዘርፍ በዋና ዋና ዘርፎች ላይ ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በመኸር ሰብል አሰባሰብ፣ የበበጋ መስኖን በፍጥነት ከማስኬድ አንጻርና በአረንጓዴ ዐሻራ የተተከሉ ችግኞችን በመከታተል ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል። በተያዘው የምርት ዘመን ባለፉት አምስት ወራት ከ11 ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ምርት መሰብሰብ መቻሉንም ጠቅሰዋል።

የመኸር ሰብሎች ልማት፣ በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች በጥሩ ሁኔታ ላይ እንዳለና አሰባሰቡም በሜካናይዜሽን ጭምር እየታገዘ በመከናወን ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በእንስሳት ልማት በኩል በተለይም በሌማት ትሩፋት የተጀመሩ ሥራዎች እየሰፉና ውጤት እያሳዩ መምጣታቸውን የተናገሩት ሚኒስትሩ፤ በሚቀጥሉት ወራት ለሚከናወኑ የግብርና ሥራዎች የግብዓት አቅርቦት ዝግጅት ጥሩ መደላድል እየተፈጠረ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ በ1015/16 የምርት ዘመን በአምስት ወራት ውስጥ በመኸር በዘር ተሸፍኖ 17 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሄክታር ማሳ በሰብል ተሸፍኖ ነበር። ይህን ሰብል የመሰብሰብ ሥራ እየተከናወነ ነው። አስካሁን በባህላዊና በኮምባይነር ከ11 ነጥብ ዘጠኝ ሄክታር መሬት ላይ ሰብል ተሰብስቧል።

ከተሰበሰበው ምርት 140 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ማግኘት መቻሉን ገልጸው፤ በአጠቃላይ ከ2015/16 የመኸር ምርት 513 ሚሊዮን ኩንታል ይጠበቃል ብለዋል።

የበጋ መስኖ ሥራው ከሌላ ጊዜ አስቀድሞ በስፋት የተጀመረና ውጤታማ አፈጻጸም እየታየበት መሆኑን ገልጸው፤ በ2016 የመስኖ ስንዴ ልማት ከሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ከ117 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

ለመስኖና ለበልግ የሚያስፈልገው የአፈር ማዳበሪያ ሙሉ ለሙሉ ግዥ የተፈጸመ መሆኑን አያይዘው የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ የመጫን ሂደቱ እየተከናወነ እንዳለም ተናግረዋል።

ባለፉት አምስት ወራት ሚኒስቴሩ በትኩረት ከሚከታተላቸው የሆርቲካልቸር፣ ቡና፣ ሻይ፣ ቅመማ ቅመም እና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች ከ764 ሚሊዮን በላይ ዶላር ገቢ ማስገኘት እንደተቻም ጠቅሰዋል።

ለዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር አገልግሎት የሚውሉ የችግኝ ዝግጅት እየተደረገ እናዳለና ባለፉት አምስት ወራት ውስጥ ብቻ አንድ ቢሊዮን ችግኞች እንደተዘጋጁ ተናግረዋል።

አዲሱ ገረመው

 አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You