ሰሞኑን በአካባቢ የደን እና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን አማካኝነት የተዘጋጀ “ሀገር አቀፍ የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ዘርፍ የዘጠኝ ወር እቅድ አፈፃፀም የግምገማና የምክክር መድረክ” ተካሂዶ ነበር። ይህ ከግንቦት 11 – 13/2011 አ.ም ለሦስት ቀናት በሃዋሳ ሴንትራል ሆቴል የተካሄደው ውይይት እንደማንኛውም የውይይት መድረክ ቢሆንም በይዘቱ ግን ለየት ብሎ ተገኝቷል። የውይይቱ ይዘት ከላይ እንደተመለከትነው ሆኖ የታዳሚዎቹ ስብስብና ስብጥር ፍፁም ሙያ ተኮር፤ ጉዳዩ ከአገርም ያለፈ ዓለም አቀፍ ስጋትና የጋራ አጀንዳ መሆኑ የታዳሚውን ቀልብ ስቦ ሰንብቷል።
መድረኩ የሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት፤ ማለትም ከክልል እስከ ፌዴራል ተቋማት፤ ከመንግሥታዊ ካልሆኑ እስከ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ምርምር ተቋማት፤ ከተጠሪ ተቋማት እስከ ፓርላማ ተወካይ ድረስ የታደሙበት ይህ የውይይት መድረክ በርካታ ፋይዳ ያላቸው ርዕሰጉዳዮች የተነሱበት፣ በእያንዳንዱ ላይ በጥልቀት ውይይት የተደረገበት፣ ይበጃሉ የተባሉ መልዕክቶች የተላለፉበት ሆኖ ተጠናቋል።
ይህ ፅሑፍ ቀዳሚ ታሳቢ ያደረገው በጉባኤው ላይ ያልነበሩ አንባቢያንን ከመሆኑ አኳያ ምን ምን ጉዳዮች እንደተነሱና መልዕክቶቻቸውን ከማሸጋገር አንፃር የቃኘና መረጃ ማቀበል ላይ ያተኮረ ነው። ውይይቱ የየክልሎችን (ከአቅም በላይ በሆነ መክንያት ካልተገኙት ቤንሻንጉል ጉሙዝና ድሬዳዋ) የዘጠኝ ወር እቅድ አፈፃፀም በማቅረብና ማዳመጥ የጀመረ ሲሆን በቀረቡት ሪፖርቶች ላይም ውይይቶች ተስተናግደዋል።
ከውይይቱ ዓላማዎች አንዱ ተሞክሮ ልውውጥ ነበርና ሪፖርቶቹም ሆኑ ውይይቱ ለዚህ ምቹ አጋጣሚ ሆነው መገኘታቸው በተሳታፊዎቹ ተነግሯል። ይህ የደን፣ አካባቢ ጥበቃና የአየር ለውጥ ጉዳይ አለምን በአንድ ቋንቋ እያናገረ፣ በአንድ የተግባር አቅጣጫ ወደ አንድ ግብ እያንቀሳቀሰ ያለ በመሆኑ ለችግሩ መፍትሔ ናቸው የተባሉት አንድ፣ ሁለት ተብለው በጉባኤው ተነቅሰዋል፤ መፍትሔዎቻቸውም ተመላክተዋል።
መድረኩ አሁን በዘርፉ እየተስተዋለ ላለው ችግር ዋናው መንስኤ ራሱ ሰው መሆኑ የተነገረበት፤ መፍትሔውም እራሱ ሰው መሆኑ የጋራ ግንዛቤ የተያዘበት፤ ሁሉም ሰው፣ መላው ህብረተሰብ ለዚሁ፤ ከእያንዳንዳችን ህይወት ጋር በቀጥታ ለተያያዘ ጉዳይ በጋራ መንቀሳቀስ ያለበት መሆኑ የጋራ ይሁንታን ያገኘበት፤ ለዚህም በጋራ፣ በመናበብ እና በቅንጅትለመሥራት ስምምነት ላይ የተደረሰበት ሆኖ አልፏል።
ቀደም ሲል እንደገለጽነው፤ ጉዳዮቹን ከማብራራትና ውስን ነጥቦች ላይ ከማተኮር ይልቅ ምን ምን ጉዳዮች ተነሱ፣ ምን ምን እንቅፋቶች አጋጥመው ነበር፣ ከማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበረሰባዊ ፋይዳዎች አኳያ ዘርፉ ምን ምን ተግዳሮቶች ነበሩበት፤ እኛስ እንደ አንድ ዜጋና የችግሩ ተጠቂ ከእነዚህ ነጥቦች ምን ምን እንማራለን? የሚሉትን ታሳቢ አድርገን ባጭሩ እንመልከት። ባለፈው የዘጠኝ ወር እቅድ አፈፃፀም ወቅት እያንዳንዱ ክልልም ሆነ ተቋም ያጋጠሙት ችግሮች ተመሳሳይነት ያላቸው የመኖራቸውን ያህል የተለያዩም (እንደየስነ-ምህዳራቸውና ብዝሀ-ህይወት ሀብታቸው) ነበሩ። ሆኖም ለጋራ ግንዛቤ እዚህም እዚያም ያጋጠሙ ችግሮችን መመልከቱ ጠቃሚ ይሆናል በሚል በጥቅል እንያቸው።
በአገሪቱ የሚገኙ ደኖችን በብዛት የያዘው የኦሮሚያ ክልልን ሪፖርት ያቀረቡት የኦሮሚያ ክልል ግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ቦና ያዴሳ እንዳስታወቁት የደን፣ አካባቢ ጥበቃና አየር ለውጥ ተግባራትን በተመለከተ በክልላቸው በርካታ ተግዳሮቶች ያሉ ሲሆን፤ ከሁሉም የከፋው የህግ ክፍተት መኖሩና እሱን ተከትለው የሚከሰቱ ህገ-ወጥ ተግባራት መከሰታቸው ነው።
እንደ አቶ ቦና አስተያየት በክልሉ በግል ባለሀብትነት በተሰማሩ ወገኖች ከሚፈፀም ህገ-ወጥነት ጀምሮ እስከ ህገወጥ ሰፈራ መስፋፋትና መሬት ወረራ ድረስ ወንጀል መፈፀሙ የደን ልማቱንና የአካባቢ ጥበቃውን ሥራ አስቸጋሪ አድርጎታል። በዘርፉ የክትትልና ቁጥጥር ስርዓት አለመኖር ወይም ማነስ፣ ብክለትና ብክነት መታየት፣ ደን ክለላን በተመለከተ ማን ከላይ፣ ማን አስከላይ፣ ማን ፈቃጅ እንደሆነ ተለይቶ በህግ አለመቀመጡና አንዱን ካንዱ መለየት አለመቻሉ፤ በየጊዜው የአመራር መለዋወጥ መኖሩ፣ የፍሳሽ አወጋገድና አያያዝ ስርዓት በአግባቡ አለመሆን፣ የደን ውድመትና ጭፍጨፋ፣ የአሠራር ግልጽነት አለመኖር፣ የወንዝ ተፋሰስ ልማትን በእቅድና በቅንጅት ያለመሥራት፣ የደን ቃጠሎና የዱር እንስሳት መሞት፣ ህገ-ወጥ አደን፣ የመቁረጥ እንጂ የመትከል ባህል በህብረተሰቡ ውስጥ ገና ግንዛቤ ያላገኘ ጉዳይ መሆኑ እና ሌሎችም ለዘርፉ የተሳካ አፈፃፀም ተግዳሮቶች ሆነው በሁሉም በሚባል ደረጃ ተጠቅሰዋል። በጀትና የሰው ኃይል እጥረትም ዘርፉን ሰንገው ከያዙት ተግዳሮቶች ተርታ መመደባቸው በብዙዎች (በተለይ በክልሎች) የተነሳ ጉዳይ ነው። የኦሮሚያ ክልል ግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ እንዳሉት በግል ባለሀብቱ ዘርፍ ከፍተኛ ችግር አለ።
“ልማታዊ ባለሀብት” የሚል ስያሜ አስቀድመን ስለሰጠነው በአሁኑ ሰዓት እራሱን የሚያየው ልክ እቺ አገር በሱ እጅ እንዳለችና እሱ የፈለገውን እንዲያደርግ ስልጣን ያለው አካል አድርጎ ነው፤ “ህግ ጥሳችኋል” ሲባሉ “የሥራ ዕድል ፈጥረንላችኋል፣ የውጭ ምንዛሪ እያመጣንላችሁ ነው፣ ለምናችሁ ነው ያመጣችሁን፣ ምን አድርጉ ነው የምትሉን” የሚሉ መልሶችን መስማት እየተለመደ ነውና ሀይ ሊባሉ የግድ ነው፤ እስከአሁን ወደ ሥራ ያልገቡትንም ማስገባት ይገባል። ደን እየጨፈጨፉ ግዛትንና ግንባታን ማስፋፋት፣ ብክለትና የመሳሰሉት ጥቂቶቹ በባለሀብቱ እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮች ናቸው። ችግሮቹንም ተከትሎ እስኪአሁን በርካታ የምርት ሂደታቸውን እንዲያቆሙ የተደረጉ ኢንዱስትሪዎች አሉ።
ሌሎቹን፣ በተለይም የህግ ክፍተቶች ያሉባቸውን ችግሮች ለመፍታት ደንቦችና መመሪያዎች እየተዘጋጁ ሲሆን ወደ ተግባር ለመቀየር ዝግጅታቸው የተጠናቀቁም መኖራቸውን ኃላፊው ተናግረዋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የደቡብ ክልል ከ500 በላይ ህገ-ወጥ ኢንዱስትሪዎች ላይ ዕርምጃ መውሰዱ ሪፖርቱን ባቀረቡት የክልሉ አካባቢ ጥበቃና ደን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ቀቀቦ የተጠቀሰ ሲሆን ለአካባቢ ጥበቃና ደህንነት ትኩረት የማይሰጡ የግል ተቋማት ላይ ዕርምጃ መውሰዱ የሚቀጥል መሆኑም አያይዘው አመላክተዋል።
ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ተከስቶ የነበረውን የፀጥታ ችግር ተከትሎ በደን ይዞታዎች (በክልሉ በተለይም በምዕራቡ ክፍል) ላይ ጭፍጨፋና ህገ-ወጥ ወረራ በመከሰቱ የደረሰው ጉዳት ሌላው በዘርፉ ያጋጠሙ ችግሮች ሆነው ማለፋቸውንም ዋና ዳይሬክተር ተጠቅሷል። ሌላው የግንዛቤ ችግር መኖሩና እሱን በዘላቂነት ለመቅረፍ እየተወደሰዱ ያሉ ዕርምጃዎችን የሚመለከት ነው።
በዚህ ዘርፍ የደቡብ ክልል ዕርምጃ የሚጠቀስ ሲሆን በመደበኛ ስርዓተ-ትምህርት ውስጥ (ከ5 – 8ኛ ክፍል) ትምህርቱ እንዲስጥ በማድረግ 40 ደቂቃ የጊዜ መጠን ተሰጥቶት ተማሪዎች በመደበኛ ትምህርትነት እየተከታተሉት መገኘታቸው ሲሆን ይህም በጉዳዩ ላይ በቂ ዕውቀትና ክሂሎት የሚያስጨብጥ ነው ተብሎ ተብራርቷል። ይህም ኅብረተሰቡ በግንዛቤ ማነስና በሌሎች ምክንያቶች የተፈጠሩ የአካባቢ ችግሮችን ከመሰረቱና በትውልድ ደረጃ ለመቀየር የሚያሰችል ነው በሚል በብዙዎች ተመስግኗል።
የደን ችግር ከፍተኛ የካርቦን ክምችት መሆኑ፣ የብዝሀ-ህይወት አደጋ ላይ መውደቅ፣ የስርዓተምህዳር ልማትና ጥበቃ በሚፈለገው ደረጃ አለመሆን፣ የጋራ ግንዛቤ ለመጨበጥ የጋራ ፎረም አለመኖር፤ የመረጃ አያያዝ፣ አሰጣጥና አጠቃቀምን በተመለከተ የአቅምና ክሂሎት ክፍተት መኖር፣ የአገራችን መገናኛ ብዙሃን ታዋቂ ሰዎችን ሲዘክሩና ሲያወድሱ ከመዋል ውጪ ስለአካባቢ ጥበቃ ትንፍሽ ሲሉም አለመሰማታቸው፣ መስኩ ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር አለመቻሉ፣ ለአገሪቱ ጂዲፒ አስተዋፅኦ ማድረግ ሲገባው አለመሆኑ፣ ዜጎች ንፅህናው በተጠበቀ አካባቢ የመኖር ሰብዓዊና ተፈጥሯዊ መብታቸው ሆኖ ሳለ ይህ አለመደረጉ፣ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ላይ ችግር መኖሩ፣ የዜጎች የምግብ ዋስትና አለመረጋገጥና ሥራ አጥንት መኖር፣ የአካባቢ ጥበቃና የአየር ለውጥ ተቋማዊ መዋቅር እስከታች ድረስ አለመውረድና የመሳሰሉት በክልሎች ሪፖርቶች የተነሱ ሲሆን በተለይ በአማራ፣ ትግራይ እና ጋምቤላ በስፋት ተንፀባርቀዋል።
አስተዳደራዊ ጣልቃ ገብነት፣ ወርቅ እናገኛለን በሚል የተሳሳተ ግንዛቤ የደን አካባቢዎችን መቆፈር፣ የከርሰ-ምድር ውሃ መድረቅ፣ በክልሎች ልምድ የመለዋወጥ ልምድ አለመኖር፣ ስትራተጂካዊ አሠራርን አለመከተል፣ ደካማ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም መኖር፣ በአካባቢ የሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን አለመጠቀም(በተለይ ላቦራቶሪዎቻቸውን)፣ የደን ቦታ ልየታ ችግር መኖር፣ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ወደ መሬት አለመውረድ (ወርዷል የሚሉም አሉ)፣ ደንን ልየታ፣ ምዝገባና አያያዝ አሠራር ያለመጠናከር፣ ደን ጭፍጨፋ፣ ደን ቃጠሎ፣ የተፈጥሮ ደኖችን ወደ ግል ማዞርን በተመለከተ መመሪያ አለመኖር፣ በአንዳንድ ወገኖች በኩል የባለቤትነት ስሜት ማጣት ወዘተ በዘርፉ በተደጋጋሚ የሚነሱ ተግዳሮቶች እንደሆኑ ከቀረቡት ሪፖርቶችና ውይይቶች ለመረዳት ተችሏል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2011
ግርማ መንግሥቴ