ጽዳትና ውበት የአዲስ አበባ ቋሚ መለያ እንዲሆኑ የተጀመረው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፡- ጽዳትና ውበት የአዲስ አበባ ከተማ ቋሚ መለያ እንዲሆኑ የተጀመረው ከተማዋን ጽዱ የማድረግ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ከተማ ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ገለጸ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ የበጋ ወራት የፅዳት ንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሀ ግብር የአስተዳደሩ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የትምህርት ማኅበረሰብ፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ የጽዳት አምባሳደሮች፣ የስፖርት ማኅበረሰብና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት ትናንት አካሂዷል፡፡

በመርሀ ግብሩ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሂክማ ከይረዲን እንደገለጹት፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቆሻሻ ብክለት የሚያስከትል መሆኑ ቀርቶ ገቢ ማግኛ ሀብት ማድረግ ተችሏል፡፡

ቆሻሻን መልሶ በመጠቀም ሂደት ለበርካቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩን የገለጹት ሥራ አስኪያጇ፣ ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ከመደገፍ አልፈው ወደ ባለሀብትነት ተሸጋግረዋል ሲሉ ገልጸዋል።

ይህንን መልካም ተሞክሮ ለማስቀጠልም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

ወይዘሮ ሂክማ ጽዳት የአዲስ አበባ መለያና ቋሚ የኅብረተሰብ ባህል ሆኖ እንዲቀጥል ለማስቻል በመስኩ የተመዘገቡ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ከተማዋን የማጽዳት ሥራ ዓለም አቀፍ እውቅና አስገኝቷል ያሉት ሥራ አስኪያጇ፤ በከተማ ፅዳት ዘርፍ እስካሁን የተመዘገቡ ውጤቶችን በማጠናከርና መልካም ተሞክሮዎችን በማስፋት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ አብራርተዋል፡፡

አዲስ አበባን በዓለምአቀፍ ደረጃ ለኑሮና ለሥራ ተመራጭ ለማድረግ የተያዘው እቅድ እንዲሰምር አዳዲስና ዘመናዊ አሠራሮችን ከመዘርጋት ተጨማሪ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል በበጋው የጽዳት ንቅናቄ መርሀ ግብር ላይ በንቃት እንዲሳተፍ ወይዘሮ ሂክማ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ለማ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ አዲስ አበባን ጽዱና ውብ ከተማ ለማድረግ ባለቤት ሊሆን የሚገባው ማኅበረሰቡ ነው ብለዋል።

በከተማዋ ነዋሪዎች ዘንድ የቆሻሻ አወጋገድና በተለይም የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ ላይ በርካታ መሻሻሎች መኖራቸውን የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፤ ቆሻሻን ወደ ሀብትነት ለመቀየር በሚደረገው ጥረት የውጭ ምንዛሬን ጭምር የማምጣት አቅም እየተፈጠረ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በየሳምንቱ ዓርብ ከጠዋቱ 1:30 እስከ 2:30 ሰዓት ድረስ ተቋማት ግቢያቸውን እና ከግቢያቸው 50 ሜትር ርቀት ሠራተኞቻቸውን በማስተባበር ማጽዳት እና ቅዳሜ ደግሞ በሁሉም የመኖሪያ ብሎኮች የሚገኙ ነዋሪዎች ከጠዋቱ 12:00-2:00 ሰዓት ድረስ አካባቢያቸውን በማጽዳት የበጋው የጽዳት መርሀ ግብር አካል መሆን እንዳለባቸው እሸቱ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡

መስከረም ሰይፉ

አዲስ ዘመን ዓርብ ኅዳር 28 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You