የዛሬው የ“ህይወት” አምድ እንግዳችን ለሀገራችን ያበረከቱት አስተዋጽኦ በተለይ በትምህርት ዘርፍ ከልጅነት እስከ እውቀት ዘመናቸው የሠሩትን ሥራ፣ የሀገር ወዳድነት ስሜታቸውና ሌሎችም የህይወት ቆይታቸው ብዙ ነገር ይነግረናል።
ውልደት እና ዕድገት
ውልደታቸው ጅማ ሶኮሩ ነው። ሰኔ 24 ቀን 1925 ዓ.ም ከአቶ አለማየሁ በለጠ እና ከወይዘሮ ጠንፍየለሽ አፍናቻው አብራክ የተገኙት የዛሬው ዶክተር ሉልሰገድ አለማየሁ።
እርሳቸው ልጅ በነበሩበት ዘመን ጣሊያን ሀገራችንን ተቆጣጥሮ ነበርና በርካታ የስቃይና የችግር ጊዜን ከነቤተሰቦቻቸው ማሳለፋቸውን በትውስታ ያነሳሉ። “ጣሊያን ትዕዛዝ እየተሰጠ ጅማ ላይ ክርስቲያኖች ይገደሉና ጭንቅላታቸውም በጠገራ ብር ይሸጥ ነበር። ያኔ ታዲያ የአባቴ ጓደኛ የነበሩት የአካባቢው ቆሮ (ቆሮ ማለት ከንጉሡ ቀጥሎ
ሦስተኛ ሥልጣን፣ በአራት አጥር የተከለለ መኖሪያ ቤት ያለው ሰው ማለት ነው)። እኜህ ሰው እኛንና ሌሎችንም ወዳጆቻቸውን መስኪድ ውስጥ ደብቀው ከአሰቃቂው ሞት አተረፉን። ሆኖም ግን ጥሩ ኑሮ የነበርን ሰዎች በጣሊያን ወረራ በጣም ችግረኛ ሆንን፤ አንዳንዴም የምንበላው ይቸግረን ነበር። ወደነበርንበት ደረጃ ለመመለስ ደግሞ ቤታችን፣ሀብት ንብረታችን ሁሉ ተወስዷል። ያኔ ጥሩ ነገሩ በህይወት መትረፋችን ብቻ ነው።”
ጣሊያን ከወጣና ንጉሡ ከተመለሱ በኋላ የሁሉም መንፈስ መነቃቃት ጀመረ። ያኔ ጅሬ ዋና ከተማ ላይ እናቴ ቤት ተከራይተው ትንሽ ሥራም ሞክረው ኑሮ ጀመርን።
አባቴ የአባጅፋር ጸሐፊ ነበሩ። ለትምህርት ቦታ ይሰጣሉ። ያስተማሩኝ እሳቸው ናቸው። ሴት ልጅ አትማርም ሲባል እንኳን እርሳቸው ግን እህቴንም አስተምረዋል። ሦስት ወንድሞቼንም አስተምረው ለሥራ አብቅተዋል። በወቅቱ ፊደል ጠፍቶ አባቴ በነበራቸው ጥሩ የእጅ ጽህፈት ፊደሉን አራብተው በጅሬ ከተማ በታዛ ስር ሰላሳ ልጆችንም አስተምረዋል።
ሀገራችን ነፃ ወጥታ የሰዎች ሁሉ መንፈስ የታደሰበት ወቅት ላይ አንድ ወዳጃችን ጅማ ከተማ ገንዘብ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ሥራ ለመጠየቅ ሄዶ ሲመለስ እዛ እኮ እንዴት ያለ ጥሩ ትምህርት ቤት ተከፍቷል ብሎ ነገረኝ። ይሄ የቀዳማዊ ሀይለሥላሴ ትምህርት ቤት በደርግ ጊዜ መንደራ ትምህርት ቤት ተብሏል። ይህን ስሰማ አባቴንም ሳላስፈቅድ ከሌሎች ጋር ያንን ሁሉ ዳገት ቁልቁለት ወጥተን ወርደን ትምህርት ቤቱ ሄድን። መግባት እንፈልጋለን አልናቸው።
በጣም ገረማቸው፤ ምክንያቱም ያኔ ከተማ ወጥተው ልጆችን እያስገደዱ እንዲማሩ ያደርጉ ነበር። ጃንሆይም ልጆች ተገድደው በየትምህርት ቤቱ እንዲገቡ ያዙ ነበር። ስለዚህ በእኛ የትምህርት ፍላጎት ክፉኛ ተደነቁ፤ እጃቸውን ዘርግተው ተቀበሉን። ክፍል ገብተን ሲያዩንም እንፅፋለን፣ እናነባለን፣ ሂሳብ እንሰራለን። በቀጥታ ወደ ሁለተኛ ክፍል አስገቡን። ሁለት ወር ሳንቆይ ደግሞ ወደ አራተኛ ክፍል ገባን። ትምህርት በዚህ መልኩ ቀጠለ።
ከጅሬ ጠዋት ወደ ትምህርት ቤት መውረጃው ቀጥ ያለ ቁልቁለት ስለሆነ በሩጫ ደስ ደስ እያለን እንሄደዋለን። ችግሩ ጠዋት የወረድነውን ዳገት መመለሱ ላይ ነው። በባዶ ሆድ በድካም ዳገት መውጣት ከባድ ነው። ያም ሆኖ ምሽት ሁለት ሰዓት የጅብ ድምጽ እያደመጥን እንገባለን። ማለዳ ደግሞ ተመሳሳይ ሥራ ነው። ያም ሆኖ ትምህርት መማር እፈልጋለሁ እላለሁ ለምን? ስባል “ሀገሬን ለመርዳት” ነበር የምለው። ሀገር መርዳት በምን እንደሆነ አላውቅም፤ ብቻ ሀገራችን ከጦርነቱ ነጻ በመውጣቷ ልዩ ስሜት አድሮብኛል፤ ተምሬ ሀገሬን ለመርዳት እፈልጋለሁ።
ትምህርት በጀመርኩ በሁለተኛ ዓመት ውስጥ አምስተኛ ክፍል ደርሼ ነበር። ከዛም ቤተሰቦቼ ከጅሬ ወጥተው ከተማው መግቢያ ላይ ቤት ተከራዩ። መንገዱ ለእኔ ቀለለልኝ። በዛን ወቅት ካናዳውያንና አሜሪካውያን ትምህርቱን ለማስፋፋት ከትምህርት ሚኒስቴር ተልከው ጅማ የእርሻ ትምህርት ቤት፣ የመምህራን ማሰልጠኛም አቋቋሙ። ለተማሪዎች ደግሞ ሚያዝያ 27 ትምህርት ቤትን ከፈቱ። ትምህርት ቤቱ ሲከፈት መጀመሪያ ከገቡ ተማሪዎች መካከል እኔ አንዱ ነበርኩ።
ሁለት ዓመት እዛ ተማርኩ። በዛን ወቅት የሁለተኛ ደረጃ መግቢያ ፈተና ሲሰጥ ፈተናውን ከተቀበሉት መካከል አንዱ ነኝ፤ በ1942 ዓ.ም መጨረሻ ፈተናውን አልፌ የመጀመሪያው የጅማ መምህራን ማሰልጠኛ ከገቡት ከስምንት ጠቅላይ ግዛት ከተውጣጡት 26 ልጆች አንዱ ሆንኩ። ለሦስት ዓመት ተማርን፤ ሆኖም ተቋሙ በእኛ ተጀምሮ በእኛ አበቃ። የመምህራን ማሰልጠኛው ወደ ሐረር ተዛወረ እኔ ግን ከፍተኛ ውጤት ስለነበረኝ በሽልማት ታጅቤ ተመረኩ።
የሥራ አለም ሀሁ…
በ1945 ዓ.ም ለመምህርነት እጣ አውጥተን ሸዋ ደረሰኝ። ሸዋ በጣም የሚፈለግ ቦታ ቢሆንም በወቅቱ የማውቀው ሰው ስላልነበረ ወንድሜ ያለበት ቦታ ይርጋለም ለመሄድ ሲዳሞ ከደረሰው ልጅ ጋር ተለዋውጬ ወደእዛ ሄድኩ። አለታወንዶ ላይ ለሦስት ወር ተመድቤ ቆየሁና ወደ ይርጋለም ተዛወርኩ። ከዛን ጊዜ ጀምሮ የምወደውን የማስተማር ሥራ ቀጠልኩ።
ዶክተር ሉልሰገድ የሁልጊዜ ምኞታቸው “ማንን የት አድርሼ” የሚል ነበር ። ተማሪያቸው የነበሩ ይህንን የሚያውቁ ሰው ታዲያ በአንድ ወቅት እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሰህ መልዕክት ሲያስተላልፉላቸው ይህንን በማስታወሻነት ጽፈውላቸው አንብቤያለሁ። ቀንጨብ ያደረኩት እንዲህ ይላል“…ገና ከጥንቱ ከጠዋቱ ጀምሮ አንተ ያወቅከውን እንዲያውቁ፣ አንተ የደረስክበት እንዲደርሱ እንዳውም ከዛ ልቀው እንዲገኙ ኢትዮጵያውያን ወገኖችህን በትምህርት ለመኮትኮት፣ ለማነጽ፣ በእውቀት ለማበልጸግ የምታደርገው ጥረትና ድካም ሁሉ በአዲሱ ዓመት ምኞትህ እውን ሆኖ ዳር እንዲደርስልህ ምኞቴም ጸሎቴም ነው” ይላል።
መምህርነት ውስጣቸው መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር ሉልሰገድ በሚያስተምሩበት አካባቢ መብራት ባለመኖሩ የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች ፈተና እንዳይወድቁ ማታ ማታ በማሾ ያስለጥኑ ነበር።
የእሳቸው የመምህርነት ሙያ ፍቅር ወደ ትምህርት ቤት የመጣውን ማስተማር ብቻ ሳይሆን ወደትምህርት ቤት ያልገባውንም በመቀስቀስ ወደ ትምህርት ገበታ እንዲቀርቡ ማድረግ ጭምር ነው። ሆኖም ግን ከትምህርት አስተዳደሩ ጋር ስላልተስማሙ ቅጣት በሚመስል መልኩ ከሚያስተምሩበት ይርጋለም ከሀዋሳ ወጣ ብላ ወዳለችው ለኩ ሸበዲኖ መዛወራቸውን ይናገራሉ።
“ቦታው በጣም ቀዝቀዝ ያለ ነው። መኪና አይገባም። ኑሮው በጣም ችግር ነው፤ የአይጥ አገር ነው፤ አልጋ ላይ አይጥ ይመጣል። ልጆቹን ቆላ ቁስል ጨርሷቸዋል። የሚማረው ደግሞ የከተማው ሰው ብቻ ነው። ሲዳማው አይማርም። ይሄ በጣም ስላስጨነቀኝ አንድ ሰው ይዤ ወደ ይርጋለም አቀናሁ። ያለውን ሁኔታ ሁሉ አስረዳሁ፤ መርጃ ማስተማሪያና ሌሎችም የትምህርት መጽሐፍ ተሰጠኝ ይሄንን ተሸክመን በእግራችን ሄደን በእግራችን መጣን። በየአምስት ቀን ደግሞ የገበያ ቀን አለ፤ በዛ ቀን ያመጣሁትን መጽሐፍና ሌላውንም ማስተማሪያ በተማሪዎች አሸክሜ ገበያ መካከል ገብተን ቀስቅሰን ስንወጣ ገበያተኛው ትምህርት ቤቱ ግቢ ይመጣል።
ያኔ መስበክ እጀምራለሁ። ትምህርትቤቱ የተከፈተው ለከተማው ነዋሪ ብቻ ሳይሆን ለሁላችሁም ነው። ባለመማራችሁ ቀረጥ አስከፋዩ አላግባብ ጭማሪ ያስከፍላችኋል፤ ብትማሩ ግን አንብባችሁ ትክክለኛውን ነው የምትከፍሉት። እላለሁ። እኔ ተመድቤ መጋቢት ወር ላይ ስሄድ የነበረው የተማሪ ቁጥር 225 ነበር። ሰኔ መጨረሻ የተማሪው ቁጥር 520 ደርሶ ነበር” ሲሉ ያስታውሱታል። ሆኖም ግን “የት እንደማደርሰው አሳያለሁ” ብለው በወኔ በተነሱበት ትምህርት ቤት ቆይታቸው ከወራት የዘለለ አልነበረም። ሰኔ መጨረሻ ላይ ወደ አዲስ አበባ ተዛወሩ።
ቆይታ በአዲስ አበባ
አዲስ አበባ ኮተቤ ደጃዝማች ወንድራድ ትምህርት ቤት ተዛወሩ። ቅድስተማርያም አካባቢ ደግሞ ቤት ተከራዩ። የትራንስፖርት መጓጓዣ የነበረው ከአራት ኪሎ ላምበረት ድረስ ብቻ ነው። ቀሪውን በእግራቸው ይኳትናሉ። ከስራ መለስ ታዲያ የአውቶብስ ማቆሚያው አራት ኪሎ ትምህርት ሚኒስቴር አጠገብ ስለነበር ትምህርት ሚኒስቴር ጎራ ማለትን ያዘወትራሉ። እዛ ጎራ የሚሉት እንግሊዘኛ ቋንቋን ከውጭ ከሚመጡ ሰዎች ለመልመድ በሚል ነበር። እንደለመዱት ጎራ ሲሉ ታዲያ አንድ ቀን ሀገራችንን ሊረዱ የመጡ ከልባቸው የሚሠሩ አሜሪካኖችን አገኙ። በ“ፖይንት ፎር” አዲስ የመጣ አሜሪካዊ ረዳት ይፈልግ ነበርና እዛ የሚሠሩ ሁለት ኢትዮጵያውያንን እስኪ ይሄንን ልጅ እዩልኝ ብሎ አገናኛቸው።
እነሱም እስኪ ተረት ፅፈህ አምጣ ብለው አዘዙኝ። ተረት የኖርኩበት ስለሆነ አሳምሬ ጻፍኩላቸው። አይተውት ግን አላመኑኙም፤ ከዛም አጠገባቸው ቁጭ ብዬ እንድጽፍ አዘዙኝ። ሁለት አይነት ተረት ጻፍኩላቸው። ከዛም አሳለፉኝ እና በመማሪያ መጻህፍት አገልግሎት ተቀጠርኩ ይላሉ።
በዚህ መልኩ ከሚወዱት መምህርነት ዘወር አሉ። ሆኖም ግን የትምህርት መርጃ በማዘጋጀት አሁንም የመማር ማስተማሩን ሂደት መደገፋቸው አልቀረም። “አረንጓዴው ጓደኛዬ፣ የጽህፈት ፋና…” የመሳሰሉትን ማስተማሪያዎች መፃፍ ቀጠሉ። በጠቅላላ አራት መጻህፍት ጽፈዋል። እነዚህ የዛሬ 60 ዓመት አካባቢ የተጻፉ ናቸው።
ዶክተር ሉልሰገድ ዛሬም ድረስ በጣም የሚያዝኑት በደርግ ሥርዓት ነው። የደርግ ሥርዓት ቦታውን ሲረከብ መጽሐፍቶቹ ፊት ለፊት ላይ የአፄ ሀይለሥላሴ ፎቶ ስለነበር የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሀላፊ በነበሩ ሰው ትዕዛዝ መጽሐፎቹ በሙሉ እንዲቃጠሉ ተደረጉ። “አረንጓዴው ጓደኛ ስንት ምርምር ተደርጎ የተጻፈ ነው፤ ተማሪዎች በሦስት ወራቸው ማንበብና መጻፍ እንዲችሉ ማድረግ የሚያስችል መጽሐፍ ነበር። ሁሉም ተቃጠለ፣ ገደል ገባ” ሲሉ አንገታቸውን እየነቀነቁ ይቆጫሉ።
“ፖይንት ፎር” ዓላማው በትምህርት ዘርፉ ኢትዮጵያውያን ሰልጥነው በወቅቱ ቦታውን ይዘው በነበሩት ነጮች እንዲተኩ ማድረግ ነው። እሳቸውም በዚሁ መንገድ የመማሩ ዕድል አጋጠማቸው። በመጀመሪያ ባችለር ኦፍ ሳይንስ ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኮኖራዶ፣ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ካሊፈርኒያ ማስተር ኦፍ ኢዱኬሽን እና ዶክተር ኦፍ ኤዱኬሽን ነው ያገኙት።
መጀመሪያ ባችለር ዲግሬን እንዳገኘሁ መድሃኒ ዓለም ትምህርት ቤት ለእንግሊዛዊ ዳይሬክተር ረዳት ሆኜ ተመደብኩ። ሰኔ መጨረሻ ላይ ትምህርት ቤት ሲዘጋ ለትምህርት ሚኒስትሩ ደብዳቤ ጻፍኩ። እሱ እንግሊዛዊ እኔ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ነኝ። እሱ በኢኮኖሚክስ እኔ ደግሞ በኤዲኩሽን ነው የሰለጠንኩት። እሱ በአምስት ዓመት የገደለውን ትምህርት ቤት እኔ በአምስት ወር አሻሽያለሁ፤ የላኩትንም ሪፖርት እዩልኝ። ስለዚህ ዳይሬክተርነቱ ለእኔ ይገባል አልኩ።
እንግሊዛዊው ዳይሬክተር ትምህርት ሚኒስቴር ብዙ ወዳጆች ነበሩት። ደብዳቤውን ሲያዩ ኡ…ኡ …አሉ። እንዴት እንዲህ ይደረጋል? ማመልከቻህን መልስው፤ እኛ በሌላ መንገድ እናድረገው አሉ። ያኔ የ31 ዓመት ወጣት ነኝ። ድንጋይ ፈልጬ ማደር እችላለሁ፤ ለራሴ ሳይሆን ለልጆቹ በማሰብ ነው ይሄን የማደርገው። ስለዚህ ደብዳቤውን ሰኔ ሰላሳ አስገባሁ። ሐምሌ ላይ የመድሃኒዓለም ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ሆነው ተሹመዋል የሚል ደብዳቤ ደረሰኝ። በማግስቱ እንግሊዛዊውን ዳይሬክተር ከቢሮው አስወጣሁት። መኖሪያውም ትምህርት ቤቱ ግቢ ነበር።
የአንደኛ ደረጃ መምህራን ወደ 100 ይደርሳሉ፤ሁሉም ኢትዮዽያውያን ናቸው፤ የሁለተኛ ደረጃው ከአንድ ኢትዮጵያዊ በስተቀር ሁሉም የውጭ አገር ሰዎች ናቸው። መስከረም 16 ቀን ኢትዮጵያውያን መምህራኖችን ስብሰባ ጠራሁ፤ ከጠቅላይ ግዛት ስድስት በጣም ጎበዝ ሰዎች አምጥቻለሁ። ስለዚህ ለ16 የውጭ መምህራን ደብዳቤ አዘጋጀሁ “ለአቶ … ከዛሬ ጀምሮ በመድሃኒዓለም ትምህርት ቤት ቦታ የለዎትም። ስለዚህ አዲስ አበባ ትምህር ቤቶች ጽህፈት ቤት ሄደው ይመደቡ” የሚል። ይሄን በግልባጭ አድርጌ የጥበቃ ሠራተኛውም እንዲደርሰውና እዛ ግቢ ዳግም እንዳይገቡ አደረኩ።
በማግስቱ የፈረንጆቹ መምህራን ስብሰባ ነበር። እኔም እንደማንኛውም ሰው ገብቼ ተቀመጥኩ። እንግዲህ ከስምንተኛ አልፈው ዘጠነኛ ወደእኛ የሚመደቡ ተማሪዎች በክህሎት ጥሩ ውጤት ያላቸውን እላይ፤ ዝቅተኛ የሆኑትን ደግሞ ኤ፣ቢ፣ሲ፣ዲ ተብለው ወደታች ይመደባሉ ተባለ። ይሄ አይሆንም ብዬ ተሟገትኩ፤ሁሉም ተማሪዎች ተደባልቀው መማር አለባቸው ስል ተከራከርኩ። ከዛ ሊያሸንፉኝ ስላልቻሉ እንግሊዛዊው ዳይሬክተር ከስብሰባው ወጣ። ዳግም ወደእዛ ግቢ ሳይመለሰ ወደ አገሩ ገባ። እኔም የራሴን ዩኒት መሪ ሾምኩ። መድሃኒዓለም ትምህርት ቤት ሁሉም ተማሪ እኩል ይደግ፤ ያንሠራራ የምልበት ነው። በየትምህርት ቤቱ የሚያገለግል ብዙ አሠራር የፈጠርነው በመድሃኒዓለም ትምህርት ቤት ነው።
የትምህርት ሚኒስቴርን ሪፖርት ካርድ ጥዬ የራሴን ሠራሁ። በእኔ ካርድ ላይ የትምህርት ዘመኑ በሦስት ይከፈላል። አስተማሪ ለሚበረው ክንፍ ይሰጣል፤ መሀል ያለውን ያስተምራል፤ ከታች ያለውን ወደላይ ያመጣዋል። እኔ ደግሞ ከስር ከስር እቆጣጠራለሁ፤ መምህሩም ጊዜ የለውም። ተማሪዎች ታዲያ በጥሩ ውጤት ፈተናውን አለፉ። የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና (ኢሲኤልሲ) ሲሰጥ የእኔ ተማሪዎች ሦስተኛ ወጡ ተባለ። አንደኛ ጀነራል ወንጌት፣ሁለተኛ ተፈሪ መኮንን ተባለ። ውጤቱን ስሰማ በወቅቱ የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ አካለወልድ ሀብቴ ነበሩ ቀጥ ብዬ ወደ እሳቸው አመራሁ።
እንዴት የእኔ ተማሪዎች ሦስተኛ ይወጣሉ? የኔ ትምህርት ቤት ተማሪን በክህሎት የማይለይ ነው። ሌሎቹ ደግሞ ከጠቅላይ ግዛቱ አንደኛ እና ሁለተኛ የሚወጡ ተማሪዎችን ሰብስበው አንደኛ ሁለተኛ እንዴት ይባላሉ? ስል በማስረጃ አስደግፌ ሙግት ገጠምኩ። በኋላ ሚኒስትሩ ተወው አንደኛ የወጣኸው አንተ ነህ ብለው ሸኙኝ።
መድሃኒዓለም ትምህርት ቤት መግቢያ ላይ በጉልህ የሚነበብ “ከዚህ ከማይሞተው የሰው ልጅ ማደጊያ ሰፍራ ግቡ” የሚል ጥቅስ አለ። ይህን ጥቅስ ጽፈው ያስቀመጡት ዶክተር ሉልሰገድ ናቸው። “ይሄ የእኔ የፈጠራ ውጤት አይደለም። ጥቅሱ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኮሮላዶ ቤተመጽሐፍት ደጃፍ ላይ በእንግሊዝኛ አለ። ይሄን አምጥቼ ከእኛ ጋር እንዲስማማ አድርጌ ተረጎምኩና ጻፍኩ። አሁን ወደተለያየ ቦታ ስሄድና አግኝቼ ሳነበው ደስ ይለኛል።” በማለት ይናገራሉ።
ከመምህርነት ውጭ
አሜሪካን ድምጽ በልጆች ክፍለ ጊዜ የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ በሳምንት አንድ ጊዜ ‘ሜርሊን ዘ ስቶሪ ቴለር’ በተረት ትምህርት ይሰጣል። እኔ ደግሞ ተረት እወዳለሁ። ተረትም እጽፋለሁ። ስለዚህ ፕሮግራሙ አያመልጠኝም። አሜሪካን አገር ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ በሄድኩበት ጊዜ በቀጥታ አሜሪካ ድምጽ ሄድኩ። እና ዋናውን ሃላፊ ካላገናኛችሁኝ አልኩ። ጥቁር ይሄንን ጥያቄ መጠየቁ እየገረሟቸውም ቢሆን ወሰደው አገናኙኝ። ሜርሊን ዘ ስቶሪ ቴለር የተባለውን ሰው ለማየት ነው የመጣሁት፤ ታሪኩን ሁልጊዜም እሰማለሁ፤ አደንቀዋለሁ፤ እወደዋለሁ ብዬ ጠየቁት። እሱ እኮ ሰው አይደለም ፕሮግራም ነው አለኝ።
በአሜሪካን ድምጽ ፕሮግራም ሜርሊን ዘ ስቶሪ ቴለር፣ 13 ጃዝ እንግሊዘኛ ሙዚቃ በሬዲዮ አቅርቤያለሁ። የአሜሪካን ድምጽ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጀመረው ፕሮግራም በእኔ በ1949 ዓ.ም አሜሪካ ሆኜ ነው።
ከዛ ትምህርቴን ጨርሼ በ1950 መጨረሻ ስመጣ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ተረት ለልጆች ላቅርብ ብዬ ጥያቄ አነሳሁ። ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ሰው ለልጆች ደግሞ ምን ፕሮግራም ያስፈልጋል ሲሉ በግድ አሳምኜ ጀመርኩ። ይህ ሉልሰገድ አለማየሁና የልጆች ክፍለ ጊዜ ነው ይላል። የፕሮግራም አዘጋጅ ስሙን በሬዲዮ መጥራት የጀመረ የመጀመሪያው እኔ ነኝ። ታዋቂው ጋዜጠኛ አሳምነው ገብረወልድ በጣም የሚደነቅ ወሬ አቅራቢ ነበር። ነገር ግን ሰሙን አይናገርም። “ዋጋሽን የምታገኚው ከመንግስተ ሰማያት ነው” የሚለው የቤተክህነት አካሄድ ይከተሉ ነበር። እኔ ግን ስሜን የምጠራው ደጋግሜ ነው።
ድጋሚ ለትምህርት ሄጄ ስመለስ ይሄ ሉልሰገድ አለማየሁ እና የልጆች ክፍለ ጊዜ ነው የሚለውን ፕሮግራም በ1964 ዓ.ም “የነገው ሰው” ብዬ ወለድኩት። በሳምንት ቅዳሜ ከዘጠኝ ሰዓት እስከ ዘጠኝ ተኩል የሚሰጥ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ፕሮግራም ነበር። ያንን ፕሮግራሜን ለሌሎች አስተላልፌ ወደ ውጭ ሄድኩ፤ ስመለስ ደግሞ ደርግ አቁሞታል። ይሄ በጣም ስለቆጨኝ የሞተውን ስም አንስቼ የነገው ሰው የሚባል ትምህርት ቤት ከፈትኩ።
“የነገው ሰው” ውልደትና ሞት
የነገው ሰው ትምህርት ቤቱን የከፈትኩት ከልጅነት እስከ እርጅና ሰርቼ አጠራቅሜ በሰበሰብኩት ገንዘብ ነው። ሀብት ንብረቴን ሁሉ አፍስሼ ለሀገሬ አንድ ነገር ለማበርከት ነው የሠራሁት። ከኢትዮጵያውያን ጋር “አብሮ መብላት እንጂ አብሮ መሥራት አይሆንም” ስባል አሻፈረኝ ብዬ ብዙዎችንም አማክሬ፣ አብረን ለመሥራት ፍላጎት ስለነበረኝ በተለያየ አቅጣጫ የሚሰጠኝን አስተያየትና ምክር አልቀበልም በሚል በስሜ የነገው ሰውን ትምህርት ቤት መሰረትኩ።
ከኢንቨስትመንት ፈቃድ ስጠይቅ ግን በግለሰብ ስም አይሆንም ስለተባለ አዲስ ፕሮጀክት ተዘጋጅቶ እኔም እንደማንኛውም ሰው ድርሻ ኖሮኝ ከሌሎች ጋር በጋራ አቋቋምን። ሆኖም ግን እንደተባለው አብሮ መብላት እንጂ አብሮ መሥራት አልተሳካም። ክሱ፣ ግጭቱና ጭቅጭቁ በረታ። ሸፍጡ አየለ። በዚህ ምክንያት ድርሻዬን ጥዬ ለመውጣት ተገደድኩ። የቦርድ አባላት የነበሩት ትላላቅ ምሁራን ሁሉ ትተው ወጡ።
አስር ወር በሆቴል ተቀምጪ የሠራሁት፣ ገንዘቤን ያወጣሁበት የነገው ሰው ትምህርት ቤት ወደ ዩኒቨርሲቲ አሳድገን እንደ አሜሪካኖቹ ሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ለማድርግ የወጠንነው ሁሉ እንደ አደይ አበባ አንድ ወቅት አብቦ ከሰመ። አሁን ለሌላ ትምህርት ቤት ተሸጠ ሲሉ ዛሬም በቁጭት ይብሰከሰካሉ።
የመጀመሪያ መጀመሪያ
በመድሃኒዓለም ትምህርት ቤት የተማሪዎች ካውንስል ለመጀመሪያ ጊዜ ጀመርኩ። ተማሪዎች ሲጣሉ ራሳቸው ፍርድቤት ነው የሚሄዱት። ይሄንን ካውንስል በሁሉም ትምህርት ቤቶች እንዲጀመር አደረኩ። የተማሪዎች መረጃ በሰነድነት እንዲያዝ ያደረኩ የመጀመሪያው ሰው ነኝ። ያኔ ምንም ነገር ተመዝግቦ ሰነድ ሆኖ የሚቀመጥ አልነበረም።
ዶክትሬት ይዤ ስመጣ የተመደብኩት ኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ነው። ኮተቤን ያቋቋሙኩት እኔ ነኝ። እዛ ስመደብ የትምህርት ዶክተር ነኝ። ስለዚህ ዳይሬክተር መባል አልፈለኩም። ስለዚህ ለራሴ መጠሪያ ስም መፈለግ ጀመርኩ። ከዛም ርዕሰ መምህር የሚለውን መጠሪያ አወጣሁ።
የውጭ አገር ቆይታ
ከሀገር የወጣሁት በደርግ ጊዜ ነው። ያኔ በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ዋና ራ አስኪያጅ ነበርኩ። ሥራ ላይ የቆየሁት ለአንድ ዓመት ነው።
ከመውጣቴ በፊት ለዩኔስኮ አመልክቼ ነበር። ዩኔስኮ ጠራኝ፤ ከዛም ጋና ሄድኩ። ጋና አንድ ዓመት ተኩል ቆየሁ። በቀጣይ ወደ ናይጄሪያ አመራሁ። እዛም ዲፓርትመንት ኦፍ ኢዱኬሽን ማኔጅመንትን ካቋቋሙት መካከል አንዱ ነኝ። በዘርፉ ብዙ አሻራዬን አሳርፌያለሁ። በተለያየ አገራት 22 ዓመት ቆይቻለሁ።
ስለኢትዮጵያ ምን ይታዮታል?
ኢትዮጵያ ውስጥ ወደፊት የሚታየኝ ታላቅ ብሩህ ተስፋ ነው። ዶክተር አብይ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ከወደቀበት እንዲነሳ እያደረገ ነው። በዚህ በጣም ደስተኛ ነኝ። አሁን 85 ዓመቴ ነው በቀረው ዘመኔ ከቤተሰቦቼ ጋር ለሀገራችን የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን። አሁን የዲያስፖራ ቤተሰቦች ነን። ልጆቼ ሁሉ ዜግነታቸው እንግሊዛዊ ነው። እኔ ግን ዜግነቴን አልተውኩም። አሁን አንገታችንን ቀና አድርገን ሀገር አለን የምንልበት ዘመን ላይ ደርሰናል ።
ቀጣይ ዕቅድ
አምላክ ያለ እንደሆነ መንግሥት ለዩኒቨርሲቲ መሥሪያነት የሰጠኝ አንድ መሬት አለኝ። ያ መሬት ክርክር አለበት። ልክ እንደተመለሰልኝ የሜዲካል ዩኒቨርሲቲ የማቋቋም ዓላማ አለኝ። ይሄንን ትልቅ ዩኒቨርሲቲ የምንሠራው በቤተሰብ ደረጃ ነው።
የቤተሰብ ሁኔታ
ባለቤቴን ያገባሁት እዛው መድሃኒዓለም ትምህርት ቤት እያለሁ ነው። ያገኘኋት ደግሞ አሜሪካን ነው። የሦስት ዲግሪ ባለቤት ናት። ሦስት ልጆች አፍርተናል። የመጀመሪያ ልጃችንን የወለድነው መድሃኒዓለም ትምህርት ቤት ግቢ ነው። ልጆቼ አንዱ ሜዲካል ዶክተር ነው። ሁለተኛዋ ጠበቃ ናት። ሦስተኛው ልጅ የአይቲ ባለሙያ ነው። ስምንት የልጅ ልጆችም አፍርተናል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 18/2011
አልማዝ አያሌው