የባህር በር የአብሮ መሥራት እና የትብብር መንፈስ

ኢትዮጵያውያን በታሪካቸው ማንንም በድለው አያውቁም፡፡ በመካፈልና ሰጥቶ በመቀበል የምናምን የፍትህና የሚዛናዊነት ልኮች ነን፡፡ በታሪክ ውስጥ የተነሱ ማናቸውንም የወሰንና የይገባኛል ጥያቄዎች አንዱን የበላይ አንዱን የበታች አድርገን አናውቅም፡፡ ሰጥቶ በመቀበል መርህ ውስጥ ሀገርና ሕዝብ የሆንን ነን፡፡

በቀይ ባህር (በወደብ) ጉዳይ ላይ የተነሳው ጥያቄም ይሄን መሰል የጋርዮሽ አንድምታ ያለው ነው፡፡ ምንም እንኳን ተፈጥሮ ለእኛ አድልታ የቀይ ባህርን ታሪክ ከታሪካችን ጋር አስተሳስራናለች። ዛሬም ጥያቄያችን ታሪክ ጠቅሰን ታሪካችንን መልሱልን የማለት አይደለም፡፡ ጎረቤቶቻችንን አስታውሰን የአብሮ ማደግን ጥያቄ ነው ያነሳነው፡፡ ጥያቄው ይሁንታን አግኝቶ ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት እንድትሆን ደግሞ ትልቁ መነሻችን ውይይት ሆኖ ከፊት ተቀምጧል፡፡ ውይይት ልዩነቶችን አስታርቆ ወደአንድነት የሚወስድ ሂደት ነው፡፡

እንደ ቀይ ባህር ባሉ ለብዙዎች የሕልውና ጥያቄ በሆነ ጉዳይ ዙሪያ ተወያይቶ እንደመግባባትና ተግባብቶ አብሮ እንደመሥራት የተሻለ መንገድ የለም፡፡ ብዙኃኑን ያቀፈ የሃሳብ ልውውጥ ያስፈልጋል፡፡። እንደ ሀገር መነሻችን የይገባኛል ጥያቄ ቢሆንም መድረሻችን ግን አብሮ መሥራት ነው፡፡ በባህል፣ በታሪክና በምጣኔ ሀብት ለተሳሰሩ ሀገራት ከብቻነት ይልቅ የአብሮነት ሃሳብና ተግባራዊነት ነው የሚበጀው። ይሄን መሰሉ አካሄድ ደግሞ ማንንም ሳይበድልና ማንንም በዳይ ሳያደርግ ተያይዞ ማደግን የሚያመጣ ነው፡፡ ዘመኑ ከጦርነት ወደሰላማዊነት የተሸጋገረበት ነው፡፡

የኃይል ርምጃዎች ማንንም ፊተኛ እንዳላደረጉ በደንብ የገባን ጊዜ ላይ ነን፡፡ የትኛውም ፍላጎት፣ የትኛውም ጥያቄ ሰላም ለበስና ምክንያታዊነትን ያስቀደመ እስከሆነ ድረስ በውይይት የማይፈታበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ የባህር በር ጥያቄያችን ከምክንያታዊነትና ከሰላም ናፋቂነት አኳያ ውይይትን መሠረት ማድረጉ ለአብሮነት የሰጠነውን ዋጋ የሚያሳይ ነው፡፡

በተረፈ አፍሪካዊ መልክ ኖሮት በአፍሪካውያን ተጠንቶ እልባት እንዲሰጠው በቀድሞ አካሄዳችን ‹አፍሪካዊ ችግሮችን በአፍሪካዊ መፍትሔ› ልንቃኘው የሚገባ ጭምር ነው፡፡ ፍላጎትን መሠረት ያደረጉ እንደነዚህ ዓይነት ጥያቄዎች ከአብሮ መሥራት ባለፈ መቀራረብንና መነጋገርን ብሎም አፍሪካዊ እይታዎችን እንድናመነጭ መንገድ የሚጠርጉ ናቸው፡፡

በቀይ ባህር ላይ ኢትዮጵያውያን ያነሳነው ጥያቄ ቀድሞ ሊነሳ የሚገባው እጅግ የዘገየ ቢሆንም ዋናው ነገር ግን የጥያቄው ተገቢነት ነው፡፡ በፖለቲካም ሆነ በዓለም አቀፍ የሚዛናዊነት ንጻሬ ውስጥ እንደትልቅ መመዘኛ ሆኖ የሚታዩት ጉዳዮች አንዱ ሃሳብ ነው፡፡ በሃሳባችን ልክ መሆን በራሱ ትልቅ ስኬት ነው፡፡

ጥያቄያችን በቀይ ባህር፤ የባህር በር ባለቤትነት ላይ የቆየና ታሪክ የሚመሰክረው የባለቤትነት ይዞታ ቢኖረንም፤ በጋራ አስበን፣ በጋራ መክረን በጋራ እንጠቀም የሚል ነው። ይሄ የእኛ የኢትዮጵያውያን ሚዛናዊነትን የተላበሰ ነው እንጂ፤ ታሪካችን በሆነው በዓባይ ወንዝ ላይ አንድ ጭልፋ ውሃ እንዳንጨልፍ ተከልክለን የቆየንበት ጊዜ ነበር፡፡

እኛ የፍትህ ወዞች ነን፡፡ እውነት አፍ ቢኖራት ኢትዮጵያውያንን ቀርባ እንደምታናግር ብዙዎች የመሰከሩልን ማንነታችን ነው፡፡ በተለያዩ ጊዜ ያነሳናቸው ሕዝባዊ ጥያቄዎች እኛን ብቻ ተጠቃሚ አድርገው ሌላውን እንዲጎዱ የሚፈቅዱ ሳይሆኑ ተያይዘን እንራመድ ዓይነት መልክ ያላቸው ነበሩ፡፡

የሰው የማንፈልግ፣ የራሳችንንም እንዲነ ኩብን በማይፈቅድ የሉዓላዊነት ጥላ ውስጥ በቅለን የጸደቅን ሕዝቦች ነን፡፡ በፍቅርና በጨዋነት ለመጡብን ብቻ እንድንሸነፍ የሚፈቅድ ተፈጥሮ አለን፡፡ ዓባይና ቀይ ባህር ተፈጥሮ በኢትዮጵያዊነት ላይ ያደራቸው የታሪክና የማንነት ጉምቱ መነሻዎች ናቸው፡፡

የባለቤትነት ጥያቄዎቻችን በጨዋነት ጀምረው በጨዋነት ካበቁ፣ ውይይትና በአብሮ ማደግ መርህ ስር ሰፊ መድረኮችን ማዘጋጀት ከቻልን የባህር በር ጥያቄያችን መልስ የሚያገኝበት ሂደት የተቀላጠፈ ይሆናል የሚል የባለሙያ አስተያየቶች እየተደመጡ ናቸው፡፡ ብዙዎች በታሪኮቻችን ሲያጌጡ ኖረዋል፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር በቅርብ ርቀት ላይ ያለች ሀገር ናት፡፡ ይሄ ብቻ አይደለም በስማችንና በታሪካችን ሲጠራ ዘለግ ላሉ እልፍ ዓመታት መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ይሄ ሁሉ በሆነበት ምክንያት ውስጥ ግን ወደብ አልባ ሀገር ሆነን ከሶስት አስርት ዓመታት ከራቀ ጊዜ ቆይተናል፡፡

የባህር በር ጥያቄ አሁን ላለውም ሆነ ወደፊት ለሚፈጠረው ትውልድ የሕልውና ጉዳይ ነው። ከኢኮኖሚና ከፖለቲካ፣ ከደህንነትና ከፍላጎት አንጻር ይሄ ነው የማይባል ጥቅም ያለው ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር በሕዝብ እንደራሴዎች ፊት ባሰሙት ንግግር ላይ ሰፋ ያለ ምክንያታዊና ቁጭት ለበስ ሃሳቦችን አንስተው ማወያየታቸው ይታወሳል፡፡

የይገባኛል ጥያቄያችንን ከሕልውና ጥያቄ ጋር አቆራኝተው፣ የማደግ እና የመለወጥ ተስፋችን እውን የሚሆንበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ቀይ ባህርና ዓባይ ወንዝ ኢትዮጵያን የሚበይኑ፣ ከኢትዮጵያዊነት ጋር የተቆራኙ፣ ለኢትዮጵያ ዕድገትና ጥፋት መሠረት የሚሆኑ በመሆናቸው ከዚህ ርዕስ መሸሽ እንደማያስፈልግ የጠቆሙበትን ሁኔታ ማስታወስ ይገባል፡፡

የወደፊቷን ኢትዮጵያ በሕዝብ ቁጥር አሰፋፈርና በፍላጎት መናር ስንቃኛት የባህር በር እጅግ አስፈላጊ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በምሥራቅ አፍሪካና በአፍሪካ መንደር ካለን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጽዕኖ ፈጠሪነት እንዲሁም የሕዝብ ቁጥርን ማዕከል ካደረገ የፍላጎት መጨመር ጋር ተያይዞ አግባብነት ያለው ጥያቄ መሆኑ እውቅና ይሰጠዋል፡፡

አሁን በተነሳው የይገባኛል ጥያቄ መሠረት ሀገራችን የባህር በር ለማግኘት የጋራ ተጠቃሚነትን ባስቀደመ መልኩ ብዙ አማራጮች እንዳሏት በብዙ የዘርፉ ባለሙያዎች ተገልጸዋል። እንደምሳሌ የተነሳው የዘይላ ወደብ ነው፡፡ የዘይላ ወደብ ከመቋዲሾ በብዙ ርቀት ላይ ስላለ ከሶማሊያ ይልቅ ለኢትዮጵያ አመቺ ሁኔታ ያለው ነው፡፡

በዚህም መሠረት ሶማሊያ በኢትዮጵያ በኩል የሚገባትን ጥቅም አግኝታ ኢትዮጵያ ወደቡን እንድትጠቀመው ማድረግ ቀላሉና አዋጩ መንገድ ነው፡፡ ልክ እንደዚህ ሁሉ ከኤርትራ ጋር በተፈጠረው መልካም ጉርብትና የጋራ ተጠቃሚነትን ማዕከል ባደረገ መልኩ የአሰብን ወደብ የምንጠቀምበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይቻላል፡፡

በሕዝብ ቁጥሯ ከአፍሪካ ቀድማ ከዓለም ከቀዳሚዎቹ የምትጠቀስ ሀገር፣ በየጊዜው የሚጨምር የሕዝብ ፍላጎት ባለባት ሀገር ላይ የባህር በር ጥያቄ ጥቅሙና ልክነቱ የማያወላዳ ቢሆንም፤ ሰላም ተኮር በሆነ የውይይት አማራጮችን ማየቱ ደግሞ የበለጠ ነገሩን ተመራጭ ያደርገዋል፡፡

የትኛውም የአብሮ ማደግ ሃሳብ በውይይት/በድርድር ካልሆነ የማይሰምሩ ናቸው፡፡ አሁን ላነሳነው ጥያቄም ሆነ ወደፊት ለምናነሳው ብሔራዊ ጥቅምን ለተንተራሰ ጥያቄ በጋራ ተጠቃሚነት ውስጥ የጋራ ተግባቦት ያለው አካሄድ እጅግ ተመራጭ ነው፡፡

ሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ አካሄዶች ተግባቦትን ለመፍጠር የመጀመሪያዎቹ ምርጫዎች ናቸው፡፡ የጋራ ፍላጎት በጋራ ምክርና ውይይት መልስ የሚያገኝ ነው። በሕዳሴ ግድባችን ላይ ያሳየንውን ሕዝባዊ አንድነትና መነቃቃት በባህር በር ጥያቄያችንም ላይ በመድገም ትንሳኤዎቻችንን ማፍጠን እንችላለን።

የባህር በር ጥያቄ የአንድ ፓርቲ ወይም ደግሞ የአንድ የሆነ ቡድን ሃሳብ ሳይሆን የሁላችን የጋራ እውነት ነው፡፡ አቋማችንም የጋራ መሆን አለበት፡፡ አብዛኞቹ ታሪኮቻችን የተወሰዱብን፣ የደበዘዙብንና የተወረሱብን ጉዳዮቻችንን የአንድ የተወሰነ አካል ብቻ ስላደረግናቸው ነው፡፡

ሌላው ዓለም ስለሀገሩና ስለታሪኩ አንድ ዓይነት አመለካከት ነው ያለው፡፡ እኛ ሀገር ግን ታሪክ ተከፋፍለን የእኔ የአንተ በሚባል ልክፍት ውስጥ ነን፡፡ ይሄ ዓይነቱ የመለያየት አስተሳሰብ ነው የጋራ እውነቶቻችን ላይ መግባባት አሳጥቶ ማንም ጣልቃ ሲገባባቸው ሀይ ባዮች እንዳንሆን ያደረገን፡፡

ዓድዋ የእኛ ነው፡፡ የሕዳሴ ግድባችን የጋራችን ነው፡፡ የቀይ ባህር/የወደብ ጉዳይም የህልውናችን ጉዳይ ነው፡፡ ስንጠይቅም በጋራ፣ ስንመካከርም አብረን መሆን አለበት፡፡ በሀገር ጉዳይ ላይ እኔን አይመለከተኝም በሚል እሳቤ ውስጥ ታሪክ አይፈጠርም፡፡ ታሪክ በራሱ ታሪክ ሰሪ ትውልድን ታኮ የሚመጣ ነው፡፡

ታሪክ ሰሪ ትውልድ ደግሞ አንድነትንና አብሮነትን ተቀብሎ በጋራ ሥርዓት ውስጥ የሚኖር ነው፡፡ የባህር በር ጥያቄም ከዚህ ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ነው፡፡ ጥያቄው በመንግሥት በኩል ይነሳ እንጂ አጀንዳው ሀገራዊ ነው። ሀገራዊ አጀንዳ ደግሞ ታሪክና ትውልድ የሚፈጥር የብዙኃነት መልክ ነው፡፡

ከዛሬ ወደ ነገ የሚሄድ፣ ታሪክ የሚመልስ፣ ትውልድ የሚያንጽ፣ ፍላጎትን መሻትን የሚያረካ የመኖርና ያለመኖር የሕልውና ጉዳይ ነው። ተባብረንና ተጋግዘን አብሮ ማሰብ ስንችል ነው መሰል ጥያቄዎቻችን ፍሬ አፍርተው የሚታዩት። በሀገር ጉዳይ ላይ የግለሰብ ወይም ደግሞ የፓርቲ ጥያቄ የለም፡፡ ሁላችንም ስለሆነውና ስለሚሆነው የሚያገባን ነን፡፡

በውይይት/በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ጥያቄዎቻችን መልስ አግኝተው የባህር በር ባለቤት እንደምንሆን ተስፋ አለን።

ተስፋዎቻችን ወደመሆን እንዲመጡ ደግሞ ሰላም ያለበት፣ ምክክር የቀደመበት አፍሪካዊ ሃሳብና መድረክ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የዲፕሎማሲ ሥራ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ በዘርፉ ልምድና ተሞክሮ ያላቸው ተናግረው ማሳመን የሚችሉ፣ ለመግባባት ቅርብ የሆኑ አካላት ያስፈልጉና፤ አበቃሁ፡፡

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You