በኢትዮጵያ ከ1966 ዓ.ም በፊት ከነበረው የመሬት ስሪት፤ እንዲሁም የ1966 ዓ.ም ተከትሎ የመጣው ለውጥ ቀደም ሲል የነበረውን የርስትና ጉልት ግንኙነት በመሻር በሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም በመመራት ኢኮኖሚውን የሚመሩትን ዋና ዋና ነገሮች ከግል ባለቤትነት ወደ ሕዝብ ባለቤትነት ሲያሸጋግር መሬትን የሕዝብ ሀብት ለማድረግ በሚል «መሬት አይሸጥም አይለወጥም» የሚለውን ጥብቅ የሆነና ከሌሎች ንብረቶች የሚለየውን ገደብ ይዞ ብቅ አለ፡፡
መንግሥት መሬት የሕዝብ ሆኖ እንደሚቀጥል፣ የመሬት ተጠቃሚ የሆኑ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች መሬት የማግኘት መብት እንዳለቸውና መሬት የመጠቀም መብታቸውና ባለይዞታነታቸው ሕጋዊ ዋስትና እንደሚሰጣቸው በመግለጽ «የገጠርም ሆነ የከተማ መሬት የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግሥትና የሕዝብ ብቻ ነው» የሚል ሥርዓት እስከተዘረጋበት ወቅት ድረስ ኢትዮጵያውያን በእነዚህ የመሬት ስሪት የተለያዩ የአኗኗር ዘይቤዎችን አሳልፈዋል፡፡ መሬት ካለው ተፈጥሮዋዊ ባሕርይም ሆነ ግዙፍነት የተነሳ በኢትዮጵያ እስካሁን የፖለቲካል ኢኮኖሚ ማዕከል ሆኖ መዝለቁን ምሁራን ያነሳሉ፡፡
በተለይም አብዛኛው ሕዝብ በእርሻ የሚተዳደር በመሆኑ የመሬት ጉዳይ የኢኮኖሚያዊ መሣሪያ ብቻ ሳይሆን በፖለቲካዊ አውድ ውስጥም በርካታ ውጣ ውረዶችን ሲያስተናግድ ቆይቷል፡፡ የካናዳ ሕፃናት ፈንድ ዳይሬክተርና የኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ተንታኝ የሆኑት ዶክተር ጉቱ ቴሶ እንደሚሉት፤ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ሲባል ሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል ሀብት ያገኛል ማለት አይደለም፡፡ ፍትሐዊ የሚያሰኘው እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በለፋውና በጣረው፣ በተማረውና ባወቀው ልክ ሀብት ማግኘትና ማፍራት ሲችል ነው፡፡ ሰው ተምሮ፣ ሰርቶ፣ ለፍቶም ፍትሐዊ ሀብት ክፍፍልን ላያገኝይችላል፡፡
ምክንያቱም የተለያዩ ችግሮችና መሰናክሎች ሊያጋጥሙ ይችላሉ፡፡ በግብርና ውስጥ ያለው ሰውና በንግድ ውስጥ ያለው ተመሳሳይ ችግር ላይገጥማቸው ይችላል። እኩል ሊለፉና ሊጥሩ ቢችሉም የሀብት መጠናቸው ሊለያይ ይችላል፡፡ ነገር ግን በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ሲባል እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በሚገባው ደረጃ በትምህርቱና በሥራው እንዲሁም በልፋቱ መጠን ገቢ ማግኘት አለበት የሚል ነው፡፡ እንደ ዶክተር ጉቱ ማብራያ፤ ከዚህ በተቃራኒ ያለው ኢ-ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ደግሞ አንድ ሰው ሳይለፋና ሳይሰራ፣ እውቀቱንም ጉልበቱንም ሳይጠቀም ንብረት የሚያፈራበት ሂደት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ሰው በገጠሩም ይሁን በከተማው በርካታ ሀብት ንብረት ሲያፈራ ይስተዋላል፡፡
ኢ- ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ከኢ-ፍትሐዊ አሠራር ይነሳል፡ ፡ አገሪቷ ውስጥ ያለው የአሠራር ዘዴ ሕጎችና ደንቦች እንዲሁም መርኆዎች በሙሉ ኢፍትሐዊ ሲሆኑ የሀብት ክፍፍሉም በዚያው ልክ ፍትሐዊነት የጎደለው ይሆናል፡፡ ዶክተር ጉቱ በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው የአሠራር ዘዴ የተወሰነውን ቡድን የሚጠቅም መሆኑን በመጥቀስ፤ ለአብነትም የአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን መሬት በርስትና በጉልት ብቻ እንደሚወሰድ፤ ይህም በንጉሡ ዙሪያ የተከበቡት የጥቂት አካላት ንብረት ብቻ አድርጎት እንደነበር፡፡ በዚህም ምክንያት በወቅቱ አብዛኛው ሰው ጭሰኛ ለመሆን መገደዱን፤ በወቅቱ ኢ-ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንደነበር የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል፡ ፡
ይህም ለተማሪዎች እንቅስቃሴ መጀመርና የደርግ ሥርዓት እንዲመጣ ምክንያት መሆኑን አውስተዋል፡፡ ይህ ማለት የሚቀረጹና ሕዝቡ የሚከተላቸው ሕጎች በአግባቡ ካልተቃኙ ለ ኢ-ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል አጋላጭ መሆኑ አይቀሬ ነው ይላሉ፡፡ ዶክተር ጉቱ እንዳሉት፤ የአጼ ኃይለሥላሴን ሥርዓት ቀይሮ ሥልጣን የያዘው የደርግ መንግሥት መሬት ከባላባቶች በመውሰድ ለጭሰኞች አከፋፍሏል፡፡ ይሁን እንጂ የደርግ ሥርዓት መሬት የመንግሥት ነው የሚለው አቋሙ ሰው በሚለፋው መጠን ንብረት እንዳያፈራ የሚገድብ ነበር፡፡ ትርፍ ቤቶች በከተማ ደረጃ እንዳይኖሩ ተከልክሎ ነበር፡፡ ይህም ኢ-ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር አድርጓል፡፡ ምክንያቱም በወቅቱ ላልለፋው፣ ላልጣረው፣ የምጣኔ ሀብት ደረጃው ላልፈቀደው ሰው ሀብት የሚሰጥበት ሁኔታ ነበር፡፡
ዶክተር ጉቱ አክለውም፤ የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ መንግሥት ከመጣ ወዲህ ደግሞ «መሬት የመንግሥትና የሕዝብ ነው» የሚል አቋም መያዙን፤ ነገር ግን በተጨባጭነትም በኢትዮ ጵያ ውስጥ የሚታየው መሬት የመንግሥት እንደሆነና ከግለሰብ ለመንጠቅ አመቺ ሁኔታዎች መኖራቸውን፤ መሬቱን መንግሥት እንደፈለገው ማድረግ የቻለባቸውን አጋጣ ሚዎች ጠቅሰው ይናገራሉ፡፡ «አዲስ አበባ ዙሪያ የነበሩት አርሶ አደሮች የአንድ ሰው እጅ ጠባቂ እንዲሆኑ ያስቻላቸውም በትንሽ ገንዘብ ከቤታቸውና መሬታቸው በመነሳታቸው ነው፡፡ የተደራጀና በሥልጣን ዙሪያ የተሰበሰበ ቡድን ነው ይህንን ኢ-ፍትሐዊ አሠራር እንዲኖር ያደረገው። ለእነርሱና ለባለሀብቱ የሚመች አድርገው ነው ሕግጋቱን የቀረጹት፡፡ ይህ ኢ-ፍትሐዊ አሠራር ነው በአገሪቷ አንዱን ባለ ጸጋ ሌላውን ደግሞ ድሀ ያደረገው፡፡ ይህ ዓይነት አሠራርና ሥርዓት ከንግድ ሥርዓቱ ጀምሮ በውስን ግለሰቦች እጅ ሥር እንዲሆን በመደረጉ አገሪቷ ላይም ኢኮኖሚያዊ ጫና አሳድሯል፡፡
የብዙኃኑን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትም የገታ ነው» በማለት ዶክተር ጉቱ በከተማም ሆነ በገጠር ኢ-ፍትሐዊ የሀብት አከፋፈል እንዲኖር ያደረጉትን ፍትሐዊነት የጎደላቸውና በየጊዜው የሚወጡ ሕጎች መሆናቸውን የሚናገሩት፡፡ በመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ውስጥ ያሉት አመራሮችን ተጠቃሚ ለመድረግ፣ ግብርና ቀረጥ እንዳይከፍሉ በአቋራጭ መንገድ ሀብትን እንዲያካብቱ ያደርጉ የነበሩ የአሠራር ዘዴዎች በምጣኔ ሀብት ላይ ያሳረፉት ተጽዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም የሚሉት ዶክተሩ፤ አንድ ባለ ሀብት ከመንግሥት አመራር ጋር እየተደራደረ መሬቱን እንደፈለገው ለማድረግ አመቺ ስለሚሆንለት በመርህ ደረጃ መሬት የመንግሥት ሳይሆን የሕዝብ መሆን እንዳለበት የሚጠቁም ግልጽ ሕግ ያስፈልጋል ባይ ናቸው፡፡
መንግሥት ሲባልም በሥልጣን ላይ የተቀመጠና ሕዝቡን እንዳሻው የሚያደርገው ሳይሆን፣ በመሬት ጉዳይ ከማህበረሰቡ ጋር ተደራድሮ ውሳኔዎችን ማሳለፍ መቻል እንዳለበት ይመክራሉ፡፡ ዶክተር ጉቱ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ከጅምሩ መሬት የሕዝብና የመንግሥት ነው የሚለውን መርህ የሚከተለው ራሱ እንደ ፈለገ ለማድረግ ከማሰብ የተነሳ ነው በማለት፤ መሬት ሁሉ የአንድ ቡድን ሳይሆን የኢትዮጵያውያን ሁሉ ነው ተብሎ የሚደሰኮረው የሚጠቅም ርዕዮተ ዓለም እንዳልሆነ፤ ይህም አገሪቷን ወደማይፈለግ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ እንደሚከታት፤ አንድ ግለሰብ ተንከባክቦ ያለማውን ቦታ ሌላው ሰው ባስፈለገው ወቅት እንደፈለገው ሊያደርገው እንደማይገባ፤ ነገር ግን ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ለመላው ኢትዮጵያውያን እንዴት ማዳረስ ይቻላል የሚለውን ትኩረት በመስጠት ይህንን ሊመልሱ የሚችሉ አዳዲስ ሕጎች መቅረጽ እንደሚያስፈልግ ይጠቁማሉ፡፡
«አንድ አካባቢ ነዳጅ ቢገኝ ለአካባቢው ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን ለመላው ዜጎች እንዴት ማዳረስ እንደሚገባ ማጤን፣ ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሥራ ዕድል እንዳለ ሆኖ፤ ጥቅል የአገሪቷን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ይጠቅማል፡፡ በተቋማት ውስጥ የአንድ ወገን አሊያም ብሔር ተወላጆች ብቻ መሰግሰግ አይገባም፡፡ ሕጉ ሲቀረጽም አንድ አካባቢ የሚገኘውን የተፈጥሮ ሀብቶችና ገጸ በረከቶች ለአካባቢውም ሆነ ለመላው የአገሪቱ ዜጎች መጥቀም አለበት» ይላሉ ዶክተር ጉቱ ብዙኃንን ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል ሃሳብ ሲሰነዝሩ፡፡ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የአካውንቲንግና ፋይናንስ ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ሲሳይ ሙላቱ በበኩላቸው፤ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ዜጎች እኩል የመልማት ዕድል እንዲኖራቸው ማድረግ ነው ይላሉ፡፡
በዚህም በዋናነት መንግሥት ያሉትን ማኅበራዊ አገልግሎቶች እኩል መጠቀም በሚቻል መልክ ማዋቀር እንዳለበት ይመክራሉ፡፡ በዚህ ሂደት ዜጎች ከድኅነት ወለል በላይ ሆነው መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸው መሟላት እንደሚችል አመላክተዋል፡፡ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን ለማረጋገጥ አስቀድሞ በአገሪቷ ላይ ያለው ሀብት ምንድነው የሚለው ቀዳሚ ትኩረት መሆኑን የሚያስገነዝቡት ዶክተር ሲሳይ፤ የሀብት ምንጭ መታወቁ ዜጎችን እኩል ተደራሽ ለማድረግ ምቹ መንገድ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ ያላት ትልቁ ሀብት መሬት ነው፡፡ ይህም ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ለኅብረተሰቡ ማከፋፈልን ይጠይቃል፡ ፡
ባለይዞታው ከመሸጥ ከመለወጥ ውጪ ያሉ ሌሎች መሬቱን ተከትሎ የሚመጡ መብቶችን መጠቀም ይችላል የሚለውን አንድምታ በአግባቡ መጠቀም ይገባዋል፡፡ ከፍተኛ ሀብት በሚያከማቹ አካላት ላይ ተመጣጣኝ የሆነ ግብር መጣልም ያስፈልጋል፡፡ እንደ ዶክተር ሲሳይ ገለጻ፤ በአሁኑ ወቅት ባለ መሬቱ የራሱን ሀብት የመጠቀም መብቱ በመንግሥት መልካም ፈቃድ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ መሬት የመንግሥትና የሕዝብ ነው በሚለው የመንግሥት አቋም ውስጥ መንግሥት በፈለገበት ጊዜና ቦታ ማህበረሰቡን ከይዞታው ላይ ለማስነሳት ምቹ መንገድ የሚፈጥርለት በመሆኑ የሕዝብን የመሬት ባለቤትነት ባጎላ መልኩ ነው ሕጉ መቀመጥ ያለበት፡፡ ዶክተር ሲሳይ «በዋናነት ፖለቲካውን የሚዘውሩት አገራት በኢኮኖሚ ያደጉ አገራት ናቸው፡፡
በመሆኑም ኢኮኖሚው ሁሉን አቀፍ ለውጥ ለማምጣትና በጎ ተጽእኖን ለማሳረፍ እንደሚችል በመገንዘብ እያንዳንዱን ዜጋ መሠረት ያደረገና የሀብት ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ግልጽ የሆነ ሕግ ሊቀመጥ ይገባል» ይላሉ ፡፡ ሕጎች ግልጽ ሆነው ባልተቀመጡበት ወቅት ለትርጉም ክፍት ከመሆናቸው የተነሳ ማስተካከያ እስከሚደረግባቸው ድረስ የተጠቃሚውን መብት ሊጥሱ የሚችሉበት ሁኔታ ሰፊ መሆናቸውና ወጥ የሆነ የሕግ አሠራር እንዳይኖር በር ከፋች ይሆናሉ፡፡ በተለይም እንደ መሬት ያሉ አከራካሪ የሆኑ ጉዳዮች ሲኖሩ ተፈፃሚ የሚሆነው ስፋት ባለው የኅብረተሰብ ክፍል እንደመሆኑና መሬት ካለው ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተፅዕኖ አንፃር ጉዳዩ ትኩረት የሚሻው እንደሆነም ያስገነዝባሉ፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 16/2011
አዲሱ ገረመው