በክልሉ ከ4 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን የጤና መድህን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፡– በአማራ ክልል በ2016 በጀት ዓመት ከ4 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ክትትል እና ግምገማ ባለሙያ አቶ ቸርነት መንግስቴ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ዘንድሮ በአማራ ክልል በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ከ4 ሚሊዮን 345 ሺህ በላይ አዲስ አባላትን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዷል። ይህም 374 ሺህ አባወራዎችን የሚያካትት ይሆናል።

በክልሉ በ2015 በጀት ዓመት ጤና መድህን ተጠቃሚ ይሆናሎ ተብሎ በዕቅድ ከተያዙት ሰዎች 96 በመቶ ተደራሽ ማድረግ ተችሏል ያሉት አቶ ቸርነት፤ በአሁኑ ጊዜ በክልሉ 17 ነጥብ 5 ሚሊዮን የማህበረሰብ ጤና መድን አገልግሎት ተጠቃሚዎች መኖራቸውን አውስተዋል። በዚህም 3 ሚሊዮን 945 ሺህ በላይ አባወራዎች ተጠቃሚ ሆነዋል።

ለ551 ሺህ ለሚሆኑ መክፈል ለማይችሉ የማህበረሰብ ክፍሎች በክልሉ መንግሥት ድጋፍ በሚኖሩበት ወረዳ የተናጠል ድጎማ የተደረገ መሆኑንም አቶ ቸርነት አስታውቀዋል።

ባለፈው ዓመት ከማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ መሰብሰቡን አውስተው፤ ከዚህም ከአንድ ቢሊዮን 773 ሚሊዮን ብር በላይ ከአባላት፤ 249 ሚሊዮን 211 ሺህ 898 ብር ደግሞ ከተናጠል ድጎማ የተገኘ መሆኑን ገልጸዋል።

ለማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ክፍያ 25 በመቶ በፌዴራል መንግሥት ድጎማ የሚደረግ ሲሆን፤ ለዚህም በተያዘው ዓመት ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ የሚጠበቅ መሆኑን አስታውቀዋል።

አቶ ቸርነት በዓመቱ በጥር እና የካቲት ወራት ላይ የጤና መድህን አባላት እድሳትና ምዝገባ እንደሚካሄድ ገልጸው፤ ለአዲስ አባላት የምዝገባ 50 ብር የሚከፈል ሲሆን በአርሶ አደር አካባቢ ለሚኖሩ በቤተሰብ ቁጥር ልክ ከ350 ብር ጀምሮ እስከ 450 ብር ድረስ በመክፈል አገልግሎቱን ያገኛሉ ብለዋል።

በክልሉ በከተማ አስተዳደር ስር የሚኖሩ አባላት ከ400 ብር ጀምሮ እስከ 1700 ብር በመክፈል ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ አስታውቀዋል።

አገልግሎቱ በክልሉ ሁሉም ወረዳዎች ላይ ተደራሽ የተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተጨማሪም ከጤና ጽህፈት ቤት ጋር አብረው የሚሰሩ 184 በማህበረሰቡ የተቋቋሙ የጤና መድህን ጽህፈት ቤቶች የሚገኙ ሲሆን አባል የማፍራት እና የመታወቂያ ዕድሳት ሥራ እንደሚሠሩ አስታውቀዋል።

የጤና አገልግሎት ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ እና የግብአት እጥረት ምክንያት አባላት የሚያስፈልገውን አገልግሎት እንዳያገኙ ተግዳሮት እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ቸርነት፤ ችግሩን ለመፍታት ቢሮው ከመንግሥት እና ከግል ተቋማት ጋር በጋራ እየሠራ ነው ብለዋል።

ማህሌት ብዙነህ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You