የግብርናው ዘርፍ ለኢኮኖሚ ዕድገት ትልቁን ድርሻ ቢያበረክትም የተቀመጠለትን ግብ በማሳካት በሚፈለገው መጠን ዕድገቱን ማፋጠን አልቻለም። ለእዚህም እንደ ምክንያት ከሚጠቀሱ ነጥቦች መካከል ሰፊ የውሃ ሀብት እያለ ግብርናው በዝናብ ላይ ጥገኛ መሆኑ፣ ከአነስተኛ መስኖ በመሻገር ለትላልቅ የመስኖ እርሻ ልማት ትኩረት አለመሰጠቱ፣ የምርምር ውጤቶች ሚና አናሳ መሆን፣ የመልካም አስተዳደር ችግርና ዘርፉን ለማነቃነቅ የብዙሃን መገናኛ ሚና አናሳነት ይገኙበታል።
አሁን ግብርናው መዘመን አለበት። ምክንያት ቢባል ደግሞ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን የግብርና ግብአት ፍላጎት ማሟላት ስለሚገባ፤ እንዲሁም ቢዘገይም የምግብ ዋስትናን ዕውን ማድረግ ስለሚያስፈልግ ነው። የግብርና ምርምሮች ባግባቡ ተተግብረው የአርሶ አደሮችን ህይወት እንዲለውጡ ማድረግ ይገባል። ለዚህ ደግሞ ዘርፉን የሚመሩ ኃላፊዎች በቁርጠኛነት ከተፋዘዘበት ሁኔታ ማውጣት ይጠበቅባቸዋል።
የግብርናን ውጤት በብዛትና በጥራት አምርቶ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን በልዩ ትኩረት መስራት ይገባል። ሰሞኑን ግብርና ሚኒስቴር የጀመረው ንቅናቄም ግብርናን ለማዘመን በተግዳሮቶቹ ላይ በመዝመት እመርታዊ ለውጥ ለማምጣት ሁለንተናዊ ንቅናቄ ማድረግ ነው። ድህነትን ለማሸነፍ፤ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ፤ የምግብ ዋስትናን ዕውን ለማድረግ ግብርናን ማዘመን አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። ለዚህ ተግባር መሳካት ሃላፊነት ያለበት ደግሞ ሁሉም በመሆኑ ስራው ለአንድ ወገን የሚተው አይደለም።
ግብርና ሚኒስቴር ከተለያዩ የግልና የህዝብ ብዙሃን መገናኛ ለተውጣጡ ባለሙያዎች “የሚዲያ ባለሙያዎች ሚና በግብርና ልማት እንቅስቃሴ ውስጥ” በሚል መሪ ሃሳብ ሰሞኑን በአዳማ ከተማ የምክክር መድረክ አካሂዷል።
የእንስሳት ሀብት ዘርፍ ልማት ዳይሬክተር አቶ ታሪኩ ተካ እንደሚሉት፤ በእንስሳት እርባታ ስራ የዘመነ የእንስሳት አረባብ እየተካሄደ አለመሆኑን እና ገበያ ተኮር መሆን እንዳልተቻለ ይጠቁማሉ። በመሆኑም፤ የዶሮ ስጋ፤ የእንቁላልና የወተት አቅርቦት ከህብረተሰቡ ፍላጎት ጋር አልተጣጣመም ሲሉም ይናገራሉ። የወተትና የስጋ እሴት ሰንሰለት በርካታ የሰው ሃይል የስራ ዕድል እንደሚይዝ የሚጠቁሙት ዳይሬክተሩ፤ ዘርፉ የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ እያበረከተ እንዳልሆነ ነው የሚጠቁሙት፤ የእንስሳት አረባቡ ቢዘምን፤ ምርታማ በሆኑ ዝርያዎች ቢተካና የእንስሳት ጤና ቢስተካከል የህብረተሰቡን ፍላጎት በማሟላት አትርፎ ወደ ውጪ መላክ ይቻላል፤ ይላሉ።
ላለፉት ዓመታት ወተት ከውጭ ለማስገባት ከፍተኛ የወጭ ምንዛሬ እየወጣ መሆኑን የሚያመለክቱት አቶ ታሪኩ፤ በ2010 ዓ.ም ብቻ የ10 ሚሊዮን ዶላር የወተት ምርት ከውጭ አገር ግዢ ተፈጽሞ ወደ አገር ውስጥ መግባቱን ይናገራሉ። በቂ ባለሙያ፤ የተፈጥሮ ጸጋ እያለ ወተትን ለአገር ውስጥ ፍጆታ አሟልቶ ወደ ውጭ በመላክ ለውጭ ምንዛሬ ግኝት የድርሻውን እንዲወጣ መደረግ የሚችልበት ዕድል መፈጠር አለበት ባይም ናቸው። ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እየወጣ የሚገባውንም በአገር ውስጥ ምርት በመተካት ማስተካከል ይገባል ይላሉ።
የወተት ምርትንና ምርታማነትን ለማሳደግ የተቀየሰ ስልት አለ ያሉት አቶ ታሪኩ፤ በዚ|ህ ረገድ የአካባቢ ዝርያን ምርታማነት ማሻሻልን በቀዳሚነት ጠቁመው፤ በእያንዳንዱ አርሶና አርብቶ አደር እጅ ያሉትን እንስሳት አያያዛቸውን በማስተካከል፤ በተጠናከረ የኤክስቴንሽን ሥርዓት አርሶና አርብቶ አደሩን በመደገፍ በስፋት ምርት የሚሰጡ እንስሳት ዝርያዎችን እንዲይዙ ማድረግ እንደሚገባና የአካባቢ እንስሳትን ከውጭ ዝርያዎች ጋር በማዳቀል የወተት ምርትን ማሻሻል እንደሚያስፈልግ አውስተዋል።
የአቅም ግንባታ ስራዎችን ማጠናከር ትኩረት ያሻል የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ ማለትም የአዳቃይ ባለሙያዎችን ክህሎት በማሳደግ፤ በአረባብ፤ በአያያዝ፤ በአመጋገብ እና በጤና አጠባበቅ ላይ ተከታታይነት ያለው ስራ ለመስራት የሚያስችል ጠንካራ ስርዓት መዘርጋት ይገባል ይላሉ። የወተት ገበያ መሰረተ ልማት ማጠናከር፤ የወተት ምርት በየቀኑ ተሰብስቦ ጥቅም ላይ የሚውልበት ወይም የሚቀነባበርበትን ፈጣን ሥርዓት መዘርጋት፤ ጠንካራ የግብይት ሥርዓት ማበጀትና የጥራት ማስጠበቅ ሥርዓቱን ማጠናከርም አስፈላጊ መሆናቸውን አብነት አንስተው ጠቃቅሰዋል።
አቶ ታሪኩ የስጋ ሀብት ልማቱን አስመልክተውም ፤ የኢትዮጵያ የዳልጋ ከብት፤ የበግና የፍየል የስጋ ምርትና ምርታማነት ዝቅተኛ ነው ይላሉ። ለዚህ ምክንያቱም የእርባታ ሥርዓቱ ያለመዘመን መሆኑን ይጠቅሳሉ። ይህንንም ማሻሻል ማስፈለጉንም ይጠቁማሉ። የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችንና አሰራሮችን በመጠቀም የዳልጋ ከብት፤ በግና ፍየል ምርታማነትን ማሻሻል፤ የእንስሳት መኖ ማሻሻል፤ የግልገሎችና ጥጆች ሞትን መቀነስና የእንስሳትን ስነ ተዋልዶ ሥርዓቱን ማሻሻል ዘርፉን ለመቀየር እንደአቅጣጫ መያዙንም ያመለክታሉ። በስፔሻላይዝድ የዳልጋ ከብት ማደለብ ስራ ዘርፉን መምራትና የግል ባለሀብቶች በዘርፉ እንዲሰማሩ ማድረግም እንደአቅጣጫ ከተያዙት ውስጥ እንደሚካተቱም ያመለክታሉ።
የዶሮ ሀብት ልማቱም ከባህላዊና ተለምዷዊ አሰራር አለመላቀቁን የጠቆሙት አቶ ታሪኩ፤ ዘርፉ የተለያዩ ተግዳሮች የተጋረጡበት መሆኑን ይናገራሉ። የዶሮ እንቁላል ቁጥር እና ክብደቱ አነስተኛ መሆን፤ ዶሮዎቹ እንቁላል የሚጥሉት ለአጭር ወቅት መሆን፤ እንዲሁም የስጋ ምርታቸው በጣም አነስተኛ መሆን ከችግሮቹ መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸውን ያስረዳሉ።
ዘርፉን ካሉበት ችግሮች አላቅቆ ምርታማ ለማድረግ የተቀየሰ ስልት መኖሩን ያመለክቱና፤ በ41 በመቶ የባህላዊ አሰራሩን መቀነስ እና የመኖ፤ የጤና፤ የመጠለያ፤ የእርባታ መገልገያ አቅርቦትና አያያዝን ማስተካከል፤ የዶሮ መኖ አቅርቦትን ማሻሻል፤ የዶሮ ዝርያ አቅርቦትን ማሻሻል እና የአረባብ ሥርዓቱን ማዘመን እንደሚያስፈልግ ይጠቁማሉ። የዶሮን የማባዣ ዘዴ በማሳደግ ከውጭ የሚገቡ ጫጩቶችን በአገር ውስጥ ምርት መተካት፤ የእንስሳት ጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ማስፋት፤ የአርሶ አደሩንና የአርቢውን ዕውቀት ማሳደግ፤ ስፔሻላይዝድ የዶሮ እርባታን ማስፋፋት፤ እንዲሁም የእንቁላል እና የዶሮ ስጋ ገበያ መሰረተ ልማት የማጠናከር ስራ ለማከናወን መታቀዱን ነው አቶ ታሪኩ የሚያብራሩት፤
የግብርና ዘርፉን አስመልክተው የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሳኒ ረዲ፤ እንደሚያብራሩት፤ በቀላሉ ሊመረቱ የሚችሉ ምርቶች ላይ በማተኮር ባለፉት 15 ዓመታት ግብርናው በአማካኝ ሰባት በመቶ እያመረተ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ደርሷል። በቀጣይ ግን ዘርፉ ለውጥ ያስፈልገዋል ይላሉ። አሁን አራት የግብርና ምርት ማቀነባበሪያዎች ተጠናቅቀው ወደስራ በመግባት ላይ በመሆናቸው ይህንን ባማከለ መንገድ መመረት ይኖርበታል ሲሉም ይናገራሉ።
የተቀናጀ፤ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው፤ መላውን ህዝብ በየደረጃው ተተቃሚ የሚያደርግ ሥርዓት መዘርጋት የግብርና ገጠር ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ ዓላማና የትኩረት አቅጣጣ መሆኑን ያመለክቱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ግብርናው ፈጣንና ቀጣይነት ያለው እድገት እያስመዘገበ፤ ኢንዱስትሪው ከግብርናው በላይ እንዲያድግ በማገዝ የመሪነት ሚናውን እንዲወጣ ማድረግ እንዳለበት በስልቱ መቀመጡንም ያመለክታሉ። በብድር ያደገና የተለወጠ አገር የለምና የዘርፉን ዕድገት በማስቀጠል ካፒታል ማመንጨት ይኖርበታል፣ በቂ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘትም አለበት። ለኢንዱስትሪው ግብዓት የሚሆን ጥሬ ዕቃ በሚፈለገው ዓይነትና መጠን፤ እንዲሁም በተመጣጣኝ ዋጋ ማምረትና ለኢንዱስትሪና ለአገልግሎት ዘርፉ የገበያ ዕድል መፈጠር አለበት ሲሉ ይናገራሉ።
ግብርናው ለአጠቃላዩ አገራዊ እድገት አስተዋጽኦ አለው። የውጭ ምንዛሬ በማስገኘትና ሰፊ የስራ ዕድል በመፍጠርም የበኩሉን ይጫወታል። ይሁን እንጂ፤ አሁንም የመሪነት ሚናውን አልለቀቀም። በአሁኑ ወቅት በአማካኝ የሰባት በመቶ እድገት ነው ያስመዘገበው፤ በዚህ ረገድ የግብርናው ዕድገት ከፍላጎትና ከዘርፉ የማደግ ዕድል ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ነው። አገሪቱ ሊታረስ የሚችል ሰፊ መሬት ቢኖርም መልማት የሚችል አብዛኛው መሬት ግን አልለማም። በሌላ በኩል ሰፊ የገጸ ምድር እና የከርሰ ምድር ውሃ ሀብት ቢኖራትም በመስኖ መልማት የሚችለውን ያህል ሄክታር መሬት ግን እየለማ አይደለም።
በስራ ላይ ያለው የግብርና ፖሊሲ፤ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ዝርያ የመጠቀም አቅም፤ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ መስፋፋት፣ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ትብብር ማሳደጓ ምቹ ሁኔታዎች ናቸው የሚሉት አቶ ሳኒ፤ የግብርናው ዘርፍ እነዚህን ዕድሎች በመጠቀም ዕድገቱን ማፋጠን አለበት፤ ባይ ናቸው።
ግብርውና በዝናብ ላይ ጥገኛ መሆኑ ለፍጆታ የሚሆኑ የምግብ ሰብሎችን በማምረት ላይ መመስረቱ፤ የገበሬው በአቅም አነስተኛ ይዞታ ያለው አርሶ አደር መሆን፤ የማምረት አቅም ውስንነት፤ የእውቀትና የክህሎት ክፍተትና ቢሮክራሲ የዘርፉ ዕድገት ማነቆዎች ናቸው ይላሉ። አቶ ሳኒ፤ በዘርፉ ቀልጣፋና ውጤታማ ሥርዓትና አገልግሎት ያለመኖር፤ ደካማ የግብአት አቅርቦትና የምርት ግብይት፤ ባህሪውን ያገናዘበ የፋይናንስ ሥርዓት አለመኖርና ደካማ ተቋማዊ አደረጃጀት ሌላው ተግዳሮት መሆኑንም ጠቁመዋል። የተፈጥሮ ሀብት መመናመን፤ አነስተኛ ኢንቨስትመንትና የገጠር መሰረተ ልማት በሰብልና በእንስሳት ዘርፉ ያሉ ማነቆዎች ሲሆኑ፤ ተጽእኖዎቹ ምርትና ምርታማነት ዝቅተኛ እንዲሆን ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።
እ.ኤ.አ ከ1961 ጀምሮ እስካሁን ስንዴ ከውጭ አገር እየገባ ነው። ግን ለስንዴ ምርት ምቹ ሁኔታዎች በአገር ውስጥ አሉ። ለአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ተስማሚ፤ አካታች እና በሚያስገኘው ውጤት ላይ የተመሰረተ ለማድረግ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል።
ችግሮቹን ማስተካከል ያስፈልጋል። ይህ ሁኔታ ተቀይሮ የፍጆታ ምርት ከማምረት ተላቅቆ በገበያ የሚመራ የግብርና ሥርዓት መፍጠር፤ ዘርፉንም ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚጠቀም እንዲሆን ማድረግ ይገባል። አነስተኛ ይዞታ ያላቸውን አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም እንዲያመርቱና አመራረታቸውንም እንዲያዘምኑ ማድረግ ያስፈልጋል፤ ሲሉም ያክላሉ። ለግብርናው ዘርፍ የተለየ ጥረት ማድረግና በሁሉም ደረጃ የአስተሳሰብ ለውጥና የሰው ሀብት ልማቱ የጋራ መግባባት መፍጠር እንደሚያስፈልግም ያመለክታሉ። ለሰፋፊ እርሻ ልዩ ድጋፍ መስጠት፤ የመስኖ አጠቃቀምን ማሳደግ፤ የህግ ማዕቀፎችን በመከለስ ለግብርና ዕድገት ምቹ ሁኔታ መፍጠርም በመፍትሄነት መቀመጡን አብራርተዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት/2011
ዘላለም ግዛው