
ታላቅን ማክበር፣ መደማመጥ፣ ለአባቶች ቦታ መስጠት፣ እርቅ መፈጸም፣ መታዘዝ፣ መረዳዳትና መሰል የሥነ ምግባር መርሆዎች የኢትዮጵያዊያን የጋራ እሴቶች መሆናቸው ይነሳል። እነዚህን የወል እሴቶች በመጠቀም ችግሮችን ፈትቶና አስታርቆ፤ የተበላሸን አቅንቶ፤ የነገውን መልካም ተስፋ አሳይቶ በይቅርታና በፍቅር መኖር እንደሚቻል ምሁራን፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት መምህራን ይናገራሉ።
የእስልምና ሃይማኖት መምህሩ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ እንደሚናገሩት፤ የእምነት መለያና መልካም እሴቶች አላቸው ከሚባሉት ሀገራት ውስጥ ኢትዮጵያ ትልቁን ድርሻ ትይዛች። እንደ ሀገር ትልልቅ ችግሮች በሽምግልናና በንግግር እንደተፈቱ የሀገሪቱ የረጅም ጊዜ ታሪኮች ያሳያሉ። በአባቶች ጥረት በይቅርታ የታለፉ ብዙ ጉዳዮችም አሉ። ችግሮች ሲፈጠሩ መወያየትና መነጋገር እንደሚቻል ታላላቆች አቅጣጫዎችን አሳይተዋል። እንዲህ አይነት ሚና ያላቸው አባቶች፣ ታላላቆችና የሃይማኖት አባቶች ዛሬም አሉ።
ችግሮች ሲፈጠሩ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባቶችና እናቶች ጉዳዮቹን በቤተሰብ ደረጃ ለመፍታት የሚይዙበት መንገድ እንዳለ የሚናገሩት ኡስታዝ አቡበከር፤ የሰው ህይወት የጠፉባቸው ትልልቅ ችግሮች ሳይቀሩ በተለያየ ባህልና ማንነት ቁጭ ብሎ ማየትና መፍታት የሚችል እሴት በሀገር ደረጃ መኖሩን ይገልጻሉ።
“ከሥነ ምግባር ጋር ተያይዞ መገለጫ የሆኑ፤ እንደ ኢትዮጵያ የምንታወቅባቸው በርካታ የጋራ እሴቶች አሉን። የተለያየ ባህልና ሃይማኖት ማንነት ያለን ሕዝቦች ነን። በዚህ ማንነት ውስጥ መከባበር፣ መተሳሰብ፤መረዳዳት፤ አንዱ ስለአንዱ ችግር መኖር፤ አንዱ ለአንዱ እውቅና የመስጠትና ተያያዥ የጋራ የሆኑ እሴቶቻችን እንደ ማህበረሰብ ኢትዮጵያዊነታችንን የሚገልጹ ናቸው። በመረዳዳታችን ከራሳችን አልፈን ለሌላው ማህበረሰብ በምንሰጠው ክብርና ቦታ የምንታወቅበት እሴትና ባህል አለን። እነዚህ እሴቶች መሠረታቸው አማኝነት ነው” ይላሉ።
ኡስታዝ አቡበከር፤ ማህበረሰቡ ላይ በተለይ ወጣቱ ላይ የሚታዩ የመደማመጥና የመተባበር ክፍተቶች ሰፊ መሆናቸውን ይናገራሉ። ሆኖም አሁን ባሉት አባቶችና እናቶች እንዲሁም የሃይማኖት መሪዎች ቀደም ሲል የነበረውን የመደማመጥና የመከባበር ታሪክ የማስቀጠል ሥራ መስራት ቢቻል “የትናንቱን ማንነቶቻችንን፣ መንፈሳዊ ልዕልናችንን፣ በመሰማማትና በመከባበር ችግሮችን ፈትቶና አስታርቆ የተባላሸን አቅንቶ የነገውን መልካም አሳይቶ በይቅርታና በፍቅር የጋራ ሀገራችንን ተባብረን እንድንኖርባት ማድረግ ይቻላል” ይላሉ። ይህ ከሆነ ብዙ ችግሮች እንደሚፈቱ፤ መሰማማት እንደሚቻልና የበለጠ መቀራረብ እንደሚፈጠር ነው የሚያነሱት።
በሀገር ሠላም ውስጥ ትልቁ ድርሻ የመከባበርና መሰማማቱ እሴት እንዲሁም የሽምግልና ባህል መሆኑን በመጥቀስ፤ በሠላም ግንባታ ሂደት የአባቶች ሚና ጎልቶ እንዲታይ፣ የወል የሆኑ እሴቶች የበለጠ እንዲጎለብቱ መንግሥትን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትልቅ ሥራ እንደሚጠበቅባቸውና፤ ወደፊት እንዲመጡ ማገዝና መደገፍ እንደሚገባም ኡስታዝ አቡበከር ይናገራሉ።
ሁሉ ነገር በአስተዳደራዊ ውሳኔና ተቋማዊ አቅጣጫ አይፈታም የሚሉት ኡስታዝ አቡበከር፤ እርስ በእርስ በሚያስተዋውቅ ማንነትና መገለጫዎች ችግሮች ሊፈቱ እንደሚችሉ ያመላክታሉ። በተለይም የፀጥታ መደፍረስ ሁሉንም ሰው እየጎዳና ዋጋ እያስከፈለ በመሆኑ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ማንንም ሳይጠብቁ ሀገርን የማስቀጠል ኃላፊነት እንዳለባቸው ይናገራሉ።
የቱለማ አባ ገዳና የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት ጸሐፊ አባ ገዳ ጎበና ሆላ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በዘመናት ሂደት ውስጥ የሚተዳደርበት፣ የሚከባበርበት፣ አብሮነትን የሚገልጽበት፣ ለሰላም፣ ለሀገር ሉዓላዊነትና አንድነት ተቻችሎና ተከባብሮ የሚኖርበትን የተለያየ እሴት የገነባ ነው ይላሉ።
ሕዝቡ ለሀገሩ ሉዓላዊነት መከበር የሚጠቀምበት የጋራ እሴት እንዳለው የሚገልጹት አባ ገዳ ጎበና፤ የተለያዩ የሃይማኖትና የሀገር ባህላዊ ክዋኔዎች ለአብሮነት ሲያገለግሉ እንደነበረም ይጠቅሳሉ። ኢትዮጵያ በረጅም የታሪክ ጉዞዋ ዘመናትን አብረው የተሻገሩ የሕዝቦቿ የጋራ እሴቶች ለሉዓላዊነቷ መከበር ትልቅ አስተዋጽኦ እንደነበራቸው ያነሳሉ። በተለያዩ ጊዜያት የነበሩ መሪዎች ቢቀያየሩም የሕዝቦች አንድነትና መከባበር ያለ መሸራረፍ የቀጠለ መሆኑንም ነው የሚገልጹት።
ሕዝቡ፣ በሃይማኖት መሪዎችና ታዋቂ ግለሰቦች፣ እንዲሁም በሀገር ሽማግሌዎች አማካኝነት ችግሮች ወደ ከፋ ደረጃ እንዳይደርሱ የማድረግ ልምድም ያለው ነው ይላሉ። ይህንን ለረጅም ዘመናት የቆየ የጋራ እሴት ዛሬም ተግባራዊ በማድረግ ለሀገር ሰላም ግንባታ ማዋል ይኖርባቸዋል ሲሉ ነው አባ ገዳ ጎበና የሚገልጹት። ሕዝቡ በፖለቲከኞች ሳይጠልፍ መቻቻል፣ መከባበርና ሀገርን መውደድ የሚገለጽበትን የጋራ እሴት በተጨባጭ በማሳየት አሁን ላይ በየቦታው የሚስተዋሉ ችግሮችን መፍታት ይኖርበታል በማለት ይናገራሉ።
የጋራ እሴትን ለሀገር ሰላም ግንባታ መጠቀም ከተቻለ የኢትዮጵያ ሰላም እንዳይረጋጋ የሚያደርጉ፣ አንድነቷ እንዳይጠበቅ የሚገፋፉና አብሮነት እንዲሻክር የሚጥሩትን ኃይሎች በቀላሉ ማሸነፍ እንደሚቻልም ይጠቅሳሉ። ለዚህ ደግሞ የሀገር ሽማግሌዎች ይቅርታንና ሀገርን የማስቀደም እሴትን በማስረጽ ለሀገሪቷ ሰላም መጠናከር የበኩላቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው ይመክራሉ።
“የሰላም እጦቱ ሕዝቡን ጎድቷል፤ ኢኮኖሚውን ወደ ኋላ ጎትቶታል። ለሀገር ሰላምና አንድነት ሲውሉ የነበሩ የጋራ እሴቶች ዛሬም በተጨባጭ መሬት ወርደው መታየት ይኖርባቸዋል። የጋራ በሆነው ቃላችን ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር ፤ ሀገራችን የጋራ ቤታችን ነች ማለት የምንችለው ሰላም ሲኖር ነው። ይህንን ሰላም ማምጣት የምንችለው ደግሞ በትውልድ ቅብብሎሽ ያገኘነውን የመከባበር የጋራ እሴቶችን በመጠቀም ነው” ይላሉ።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የደህንነት ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው፤ ብዝኃነትን የሚያስተናግዱ ሀገራት ችግሮች ባጋጠማቸው ወቅት የጋራ እሴቶቻቸውን ተጠቅመው እንደሚፈቱ ይገልጻሉ። በኢትዮጵያ እዚህም እዚያም የሚስተዋሉ ችግሮችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድም ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን በመጥቀስ፤ ይህም ጦርነትን መሠረት ያደረገ መፍትሄ አስፈላጊ ባለመሆኑ ልዩነቶችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት የሚያስችል ትልቅ ሥራ እንደሆነ ይናገራሉ።
የተጣሉ የሚታረቁበት፣ አብሮነት በጉልህ የሚንጸባረቅባቸው የጋራ እሴቶች በርካታ ናቸው ያሉት አምባሳደር ዲና፤ ህብረተሰቡ ተሳትፎ ሲያደርግ ችግሮችን ለመፍታት የቆዩ ሀገራዊ የጋራ እሴቶችና ልምዶች ቀምሮ ወደ ተግባር መግባት እንደሚያስፈልግ ይጠቁማሉ። ይህ እንዲሳካም የኅብረተሰቡ ተሳትፎና ሚና ከፍተኛ መሆን እንዳለበት ይጠቁማሉ።
ተናጋሪዎቹ፤ እንደ ሀገር የጋራ እሴት ባለቤት መሆን እድለኝነት መሆኑንና የወል እሴቶችን በመከተል ነገን ማስተካከል እንደሚገባ ጠቅሰው፤ በዚህ መንገድ ካልተሰራ ግን ለሚፈጠሩ ችግሮች ሁሉም ሰው ከተጠያቂነት እንደማይድን ገልጸዋል።
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 9 ቀን 2016 ዓ.ም