የትምህርት ጥራት ስብራትና መፍትሔው

በሀገር አቀፍ ደረጃ የትምህርት ጥራት ላይ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት መንግሥት የተለያዩ ስትራቴጂያዊ ርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል። እየተወሰዱ ካሉት ስትራቴጂዎች አንዱ በዩኒቨርሲቲዎች ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ መሰጠት የጀመረው የመውጫ ፈተና አንዱ ነው። ይህም የትምህርት ጥራቱን በማስጠበቅ ተገቢውን እውቀት፣ ክህሎትና ስብዕና ያሟላ ምሩቃን ለማፍራት እንደሚያግዝ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

የመውጫ ፈተናውም በምሩቃን ፕሮፋይል መሰረት ተዘጋጅቶ እየተሰጠ ሲሆን፤ መምህራንና ተማሪዎች ለትምህርት ጥራት መሻሻል በትኩረት እንዲሰሩ ከማስቻሉም ባለፈ ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይልን በማፍራት ጥራት ያለውና በአግባቡ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለገበያው ለማቅረብ ይታመናል።

በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማሻሻል እና ጥራቱን ለማሳደግ የዩኒቨርሲቲ የመውጫ ፈተና አይነተኛ ሚና እንዳለው ዕሙን ነው። በዚህም ለመጀመሪያ ጊዜ በተሰጠው የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ከተቀመጡት ተማሪዎች ውስጥ 40 ነጥብ 65 በመቶዎቹ የማለፊያ ነጥብ ማስመዝገብ ችለዋል።

በሌላ በኩል የትምህርት ጥራትን ለማሻሻልና ከኩረጃ በጸዳ መልኩ ተማሪዎችን ለማስፈተን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በዩኒቨርሲቲዎች መሰጠት ከጀመረም ሁለት ዓመታትን አስቆጥሯል። በሁለቱም ዓመታት የተመዘገበው የተማሪዎች ውጤት ብዙዎችን እያነጋገረ ይገኛል።

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ከማን ምን ይጠበቃል?፣ የትምህርት ጥራት ውድቀትና መፍትሄው ምንድነው? በሚሉት ሃሳቦች ዙሪያ የዘርፉ ምሁራን ምን ይላሉ?

የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ብርሀነመስቀል ጠና (ዶ/ር)፤ የትምህርት ጥራት መሻሻል ለሀገር ዕድገት፣ በዕውቀትና ክህሎት የዳበረ ትውልድ ለማፍራት ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን በማንሳት፤ ተማሪዎችን ከታችኛው የክፍል ደረጃ ጀምሮ ማብቃት፣ የትምህርት አመራሩን በውጤት መለካት፣ መምህራንን በመደበኛው የትምህርት ጊዜ በአግባቡ እንዲያስተምሩ ማድረግ፣ ተማሪዎች ላይ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ተገቢ ነው ይላሉ።

የተማሪዎች ዋና ተግባር ትምህርት በመሆኑ አዕምሯቸውን ሰብስበው መማር እንዳለባቸውም ያስረዳሉ።

የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ሁሉም ባለድርሻ አካላት ችግር ላይ ከመነጋገር ባለፈ ጉድለቱን ለመሙላት በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው የገለጹት ዶክተር ብርሀነመስቀል፤ የተማሪ ቤተሰቦች ልጆቻቸውን ከኩረጃ በጸዳ መልኩ መፈተን የሚችሉና እኔ እችላለሁ በሚል መንፈስ በራስ መተማመን እንዲኖራቸው አድርገው ማሳደግ እንዳለባቸው ያስገነዝባሉ።

በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መሰጠት በጀመረው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ላይ የሚመዘገበው የተማሪዎች ውጤት አጥጋቢ አለመሆኑን ጠቁመው፤ ትምህርት ሚኒስቴር እና የትምህርት ባለድርሻ አካላት የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ውጤት ከባለፈው ዓመት ለምን ሊያሽቆለቁል ቻለ፣ ምንም ተማሪ ያላሳለፉ እና ሁሉንም ተማሪ ያሳለፉ ተማሪዎች ምን ሰርተው ነው የሚሉትን በመለየት ልምድ እንዲለዋወጡ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ይገልጻሉ።

የተማሪዎች ውጤት ለምን ሊያሽቆለቁል እንደቻለ ጥናትና ምርምር ሊደረግ ይገባል የሚሉት ዶክተር ብርሀነመስቀል፤ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ሁሉም የትምህርት ተቋማት እና ባለድርሻ አካላት በጋራ በመሆን የመፍትሄ ሃሳብ በማስቀመጥ የትምህርት ጥራትን ማሻሻል እንደሚገባ ያስረዳሉ።

ተማሪዎች ለውጤት መብቃት እንዲችሉ መምህራን በአግባቡ ማስተማርና ክትትል ማድረግ እንዲሁም ተማሪዎች ትምህርታቸው ላይ ብቻ ትኩረት ካደረጉ የሚፈለገውን የትምህርት ደረጃ ማምጣት እንደሚቻል ይገልጻሉ።

በቀጣይ ዓመታት በሀገሪቱ የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥና ተማሪዎችን ማብቃት ካልተቻለ ሀገሪቱ ችግር ውስጥ ትወድቃለች የሚሉት ዶክተር ብርሀነመስቀል)፤ የተማሪዎች ቀጣይ እጣ ፋንታ ምንድነው የሚሆነው የሚለው መንግሥትን ሊያሳስበው ስለሚችልና የትምህርት ስብራት ምክንያት ስለሚሆን መፍትሄው ምንድን ነው የሚለውን በሚገባ ማየት ተገቢ መሆኑን ያብራራሉ።

ከዚህ በተጨማሪም ለተማሪዎች የሚሰጠው ፈተና ፈታኝ መሆኑን ማረጋገጥና መገምገም ተገቢ ነው ይላሉ።

የዩኒቨርሲቲ የመውጫ ፈተና እና የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ለትምህርት ጥራት መሻሻል ከፍተኛ ሚና ያላቸው በመሆኑ በመልካም ጎን ሊታዩ ይገባል ባይ ናቸው።

ተማሪዎች ለፈተና ብቻ ሳይሆን ሀገር መለወጥ የሚችል እውቀት ለማግኘት መጣር እንዳለባቸው የሚያመላክቱ አማራጮች መሆናቸውን ገልጸው፤ እውቀት ተኮር ትውልድ ለመቅረጽ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ያመላክታሉ።

በዩኒቨርሲቲዎች የመውጫ ፈተና መጀመሩ ተማሪዎች ፈተናን ለማለፍ ሳይሆን ተጨባጭ ዕውቀት ለማግኘት እንዲጥሩ እገዛ እያደረገ ነው የሚሉት የሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጀማል የሱፍ (ዶ/ር) ናቸው።

የትምህርት ጥራት መምጣት የሚችለው በተማሪዎች ብቻ ባለመሆኑ ዝቅተኛ ውጤት የተመዘገበባቸውን ትምህርት ክፍሎች በመለየት መምህራን ምን እንደጎደላቸው እራሳቸውን እንዲጠይቁ እና ተማሪዎቻቸውን በአግባቡ እንዲያበቁ እየተደረገ ነው ይላሉ።

የመውጫ ፈተናው በእውቀት ላይ ተመስርቶ ትውልድን ለማፍራት እና በሥራ አለሙ ላይ ብቁ የሆነ የሰው ኃይል ለማፍራት እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸው፤ የዩኒቨርሲቲ የመውጫ ፈተናና የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መሰጠት መጀመሩ ተማሪዎች ጊዜያቸውን ለትምህርት እንዲሰጡ፣ መምህራን በአግባቡ እንዲያስተምሩ እና የትምህርት አመራሩ ለትምህርት ጥራት ትኩረት እንዲያደርጉ እገዛ እያደረገ መሆኑን ያስገነዝባሉ።

የትምህርት ጥራት ሊረጋገጥ የሚገባው ከዚህ ቀደም ባሉት ጊዜያት ነበር የሚሉት ዶክተር ጀማል፤ አሁን የተጀመረው ርምጃም የሚበረታታ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

የትምህርት ጥራትን በሚፈለገው ደረጃ ለማሻሻል ቁርጠኝነትና ዝግጅት ከተማሪዎች፣ ከመምህራን እና ከትምህርት አመራሩ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።

የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ ካልተቻለ የሀገር ዕድገት፣ በዕውቀትና ክህሎት የዳበረ ትውልድ ማፍራት የማይቻል በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለትምህርት ጥራት መሻሻል በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You