በታዳጊዎቹ ላይ ግብረሰዶም ወንጀል የፈፀመው ግለሰብ አስተማሪ ቅጣት

አሁናዊ ሁኔታው በጣም አሳዛኝ ደረጃ ላይ ደርሷል። አደገኛ በሆነ ሁኔታ ግብረሰዶማዊነት እየተስፋፋ ነው። ሆስፒታል ውስጥ ጾታ አንሞላም እስከማለት የተደረሰበት ሁኔታ እያጋጠመም ይገኛል፤ ልጁ ከትምህርት ቤት ወደቤቱ ተመልሶ እማዬ! ” እኔ ወንድ ነኝ ሴት? ወደፊትስ ሴት መሆን አልችልም ?” ብሎ እስከመጠየቅ ተደርሷል። ወንዶች የሴቶች ቀሚስ ለብሰው ቦርሳ ይዘው ፋሽን እያሳዩ ነው። አንተ አንቺ አትበሉ ተብሎ በተለያዩ ቦታዎች ስልጠናዎች እየተሰጠ ነው። ይህ እንግዲህ ሲጠቃለል እንደ አገር አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሳችንን ያመላክታል።

ይህ ሁሉ ነገር ግን ሲጠቃለል የሚያሳየው ከባህልና ከሀይማኖታችን አፈንግጠን እየወጣን ስለመሆናችን ነው። ሁላችንም እንደምንገነዘበው አሁን በየቦታው ሺሻ፣ ጭፈራ ቤት ራቁት ጭፈራ፣ ስካር እንዲሁም ገንዘብ መውደድ በጣም በዝቶ ተንሰራፍቷል። ግብረሰዶም ደግሞ እነዚህ ሁኔታዎች በጣም ይመቹታል፤ በመሆኑም እግር በእግር እየተከተለ ትውልዱን ሊያጠፋ እየገሰገሰ ነው ።

ግብረ ሰዶም የፈጣሪ እግዚአብሔርን ሀሳብ በመጻረር ትውልድ እንዳይቀጥል የሚያደርግ ነው። እግዚአብሔር ለአዳም/አደም ቢያስፈልገው ኖሮ ያደርገው ነበር፤ ነገር ግን ሄዋን ስለሆነች የምታስፈልገው ያደረገውም እንደዛ ነው። ኖህም ወደመርከቡ ሲያስጋባ እንስሳትን ወንድና ሴት አድርጎ ነው። እጽዋትን ብናይ ሴቴና ወንዴ ናቸው። ኤሌክትሪክም ኔጋቲቭና ፖዘቲዝ ነው። ከተፈጥሮ ጋር የተቃረነ ስራ እየተሰራ እያየን ግን መሪዎቻችን፣ የሀይማኖት አባቶች እንዲሁም ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ተቃውሞን ካላሰሙ ትውልድ ማለቁ ነው።

በመሆኑም 98 በመቶ በላይ ሀይማኖተኛ የነ ሕዝብ የሚኖሩባት፣ ባህልና ወግ ያላት አገር እስልምናውም ክርስትናውም በእግዚአብሔር ተፈጥረናል፤ ከሞትን በኋላ ደግሞ ገነት ወይም ጀነት እንገባለን ብሎ በሚያምንበት አገር ላይ እንደዚህ አይነት ስራ ነግሶና ተንሰራፍቶ ማየት የማንም ችግር ሳይሆን የራሳችን ንዝላልነት ያመጣው በመሆኑ ሁላችንም ወደምንጫችን ወደቀደመው ማንነታችን መመለስ ይገባናል።

በእኛ ባህልና ወግ ባልና ሚስት እንኳን በሰው ፊት አይሳሳሙም፤ ነገር ግን ድህነታችንን ተጠቅመው የተለያዩ ግብረሰናይ ድርጅቶች እየመጡ ቆሻሻ ተግባራቸውን ሲፈጽሙብን ዝም ልንል አይገባም። (comprehensive sexual education) በትምህርት ደረጃ ሲሰጥ እንዴት ዝም እንላለን። እንዲህ አይነቱን ጸያፍ ሒደትና ተግባር “አይሆንም!” ብለን በጋራ ልንጋፈጠው ይገባል። መጥፎና ከፈጣሪም የሚያጣላ ተግባር ከመጥፋታችን በፊት ልብ ልንላቸው የሚገቡ ነገሮች ናቸው።

አሁን አሁን ደግሞ እየተሰሙ ያሉ ጸያፍ አባባሎችም ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል። በአገራችን ወይዘሮም ወይዘሪትም መባል አንፈልግም የሚሉ ሴቶች እየተስተዋሉ ነው፤ ይህ ከምን የመነጨ ነው? ማዕረግ የለኝም የሚል ሰው ሌላ ችግር አለበት ማለት ነውና ትኩረት ያሻል።

በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎችና የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ በየመንደሩ፣ በየሥርቻው፣ በየጎድጓዳውና ጉድጓዱ ራሳቸውን ደብቀው ያደፈጡ ሁሉ ቢቆጠሩ ብዛታቸው የትየለሌ ሆኗል። መጠሪያ ስማቸውም ግብረ ሰዶማዊ (ጌይ) ብቻ ሳይሆን ‘ዜጋ’ የሚለውንም ይጠቀሙበታል። በዚህ ሕይወት ውስጥ ያልገቡ ሌሎች ወገኖች ደግሞ ‹‹ቀጥ›› በሚል ይጠራሉ።

ይህን ሁኔታ የአገራችን በተለይም የከተማችን እውነት ነው። አሁን አሁን በጣም በጥቂቱ ከሰባት እስከ 32 ዓመት ድረስ ሕይወታቸውን በግብረ ሰዶማዊነት ያሳለፉት ግብረ ሰዶማውያንና ግብረ ሰዶማውያት (ወንዶችና ሴቶች)፣ ‹‹ዝምታው ይሰበር ትውልድ ይዳን በእኛ ይብቃ›› በሚል ርዕስ (ዘጋቢ) ዶክሜንተሪ ፊልሞችን እንዲዘጋጁ ትብብር እያደረጉ ትውልድን ለማዳን አንዳንድ ወገኖች እየሰሩበት ነው።

‹‹ስለኢትዮጵያ ዝም አንልም ግብረ ሰዶማዊነት በኢትዮጵያ የ666 አሠራር›› የሚል ርእስ ባለውና ለምረቃ በበቃው በዚሁ ፊልም ውስጥ ይህንኑ ቃለ መጠይቅ ካካሄዱት ከእነዚህ ግብረ ሰዶማውያን ማብራሪያ ለመረዳት እንደተቻለው ሕጋዊና መደበኛ ሚስት አግብተው፣ ትዳር መስርተውና ልጆች ወልደው በሽምግልና ዕድሜያቸው ግብረ ሰዶም የሚፈጽሙ አዛውንቶች አሉ። አንዳንድ ጊዜ ‹‹አባባ መሽቷል እባክዎን ወደ ቤትዎ ሂዱ›› እያሉ ወጣቶች በሽማግሌዎቹ ይቀልዱባቸዋል። ይሳለቁባቸዋልም። እነዚህም አዛውንቶች ታዋቂነታቸው በ‹‹ዜጎች›› ዘንድ ብቻ ስለሆነና በአካባቢያቸው ማኅበረሰብ ዘንድ የሚታወቁት ባለትዳርና የልጆች አባት ስለሆኑ ከማኅበረሰቡ ዘንድ እንዳይገለሉና ተከብረው እንዲኖሩ አድርጓቸዋል።

አሁን አሁን ችግሩ አይን እያወጣ ብዙዎችም ሰለባ እየሆኑበት ያለ ይመስላል። ለዚህ ደግሞ ማሳያው መንግሥት ወይም የሚመለከተው የክብር መዝገብ ሰጪ አካል የማያውቃቸው ከአንድ በላይ የሆኑና ከተመሳሳይ ጾታ ጋር የሚደረጉ ጋብቻዎች እየተበራከቱ መሆኑ ነው።

በኢትዮጵያ ግብረ ሰዶማዊነት እየተስፋፋና ግብረ ሰዶማዊ ጥቃትም እየተፈጸመ ስለሆነ ድርጊቱ ከመስፋፋቱና ‹‹ለኛም መብት ይሰጠን›› የሚል ጥያቄ ከመነሳቱ በፊት መንግሥት ከእንጭጩ ሊገታው ይገባል።

በዛሬው የዶሴ መደሰናዷችንም በታዳጊዎቹ ላይ ግብረ ሰዶም ወንጀል የፈፀመው ግለሰብ በእስራት የመቀጣቱን ነገር ልንነግራችሁ ወድደናል። ከላይ እንደጠቀስነው ግብረ ሰዶማዊነት በየጓዳችን፣ በየሰፈራችንና በጎረቤትም ጭምር አብሮን እየዋለ እያደረ ነው። ኑሯችን የቀድሞው ማ|ሕበራዊ መስተጋብራችን በጠቅላላው እንዴት ዋልክ(ሽ)? እየተባባልን አንዳችን የአንዳችን ጤንነት የሚያሳስበን ጎረቤታሞች መሆናችን ላይ እያሳየን ያለነው ክፍተት እኔ ካልተነካው ስለሌላው ምን አገባኝ እያልን በዝምታና በቸልታ የምናልፋቸው ነገሮች ሁሉ ለእነዚህ እኩይ ተግባር ፈጻሚዎች የተመቻቸው ሁኔታው ፈጥረዋል።

የአብዛኞቻችን ልጆች እደጅ ወጥተው ከእኩዮቻቸው ጋር መጫወት መቦረቅ በእድሜያቸው የሚመጥናቸው ተግባር ነው። ይህንንም በተግባር ይፈጽሙታል። በዚህ መካከል ግን አንዳንድ ለሰይጣናዊ ድርጊት የሚያጫቸውም አይጠፋ። ታዲያ ምን ቢጠነቀቁ ሰይጣናዊ ድርጊት የተጸናወታቸው ግለሰቦችም ፍላጎታቸውን ለማሟላት ቀን መጠበቅ እና አሳቻ ሰዓትን መምረጥ ማሰብ የተለመደ ነውና ልጆቹን ይከታተሏቸዋል።

የግብረ ሰዶሙ ድርጊት የተፈጸመው በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ልዩ ቦታው ማር ተራ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ ነው። ከላይ እንዳነሳሁት የዚህ ሰፈር ልጆችም ተሰብስበው በመጫወት ላይ እያሉ በመካከል መጣላትም መታረቅ ይኖራል። ለምግብ አልያም ውሃ ሲጠማቸው ቤታቸው ድረስ ብሎ መመለስ ሁሌም የሚያዘወትሩት ተግባራቸው ነው። ይህ ተግባራቸው ብዙዎችን የሚያስደስት ቢሆንም እንደ ወንጀል ፈጻሚው አይነት ግለሰቦች ደግሞ ልጆቹን ከመንገዳቸው ለማሰናከል እና በራሱ ወጥመድ ውስጥ ለማስገባት ምን ዓይነት መንገድ ልጠቀም የሚለው ነገር እንቅልፍ ይነሳዋል።

ታዲያ በዚህ ሰፈር ነዋሪ የሆነው የ43 ዓመቱ ጎልማሳም እነዚህን ህጻናት የሚያጠምድበትን መንገድ ጊዜ ወስዶ አስቦበታል። በምን ቢያታልላቸው እና ቢያማልላቸው እጁ እንደሚገቡም ብዙ አስቦበታል፤ ምናልባትም ከመሰሎቹ ጋር ተማክሮበትም ይሆናል።

በአይኑ የገቡትን የአምስት፡፡ የስድስት እና የአስር ዓመት ታዳጊዎችንም በቀለበቱ ውስጥ አስገብቷል። ግን ደግሞ እነዚህ ልጆች በምን መልኩ ነው ወደእሱ የሚመጡት የሚለውን ማሰብና መወሰን ጊዜ ወደሰበት። ነገር ግን ወደኋላ አላለም። ልጆቹን በተለያየ ጊዜ በመጥራት ፍቅር በማሳየት አንዳንዴም አብሮ በመጫወት እንዲቀርቡት አደረገ። ይህ አካሄዱ ደግሞ ልጆቹ እንዲያምኑት አደረጋቸው። በህጻናቱ ንጹህ ህሊና የታመነው ይህ ግለሰብ ግን እምነታቸውን በልቶ መንገዳቸውን ሊያበላሽ ልጅነታቸውን ሊያሰናክል አሰበ። አሰላሰለም። አስቦም አልቀረ። ሶስቱንም ህጻናት በተለያየ ቀን በየተራ ቤቱ እያስገባ የግብረ ሰዶም ተግባሩን ፈጸመባቸው።

ይህ አስነዋሪ ተግባሩ ደግሞ እንዳይጋለጥ ልጆቹም አስፈላጊውን እርዳታ በጊዜው እንዳያገኙ አስፈራራቸው። የልጅ ነገር ሆኖም ፈሩትና ዝም አሉ። ነገር ግን የስድስት ዓመቱ ልጅ የደረሰበትን ነገር ከእናቱ ሸሽጎ መቆየትን አልመረጠም፤ ክፉና ደጉን ባልለየው አእምሮው የተፈጠረውን ነገር ባያውቀውም አገናዝቦ ምን እንደሆነ ባይረዳውም እናቱ ታውቅ ዘንድ ግን ሁሉንም ነገር ነገራት።

እናት በሰማችው ነገር እጅጉን ደነገጠች፡፡ አለቀሰች። አነባች ልጇን ያበላሸባትን ጎልማሳ ብትገለው ተመኘች፤ ነገር ግን እሱን ገድላ ልጇን የባሰ ላለማጣትና ላለመጉዳት ወሰነች። ግን ምን ታድርግ። ጠንካራዋ የታዳጊው እናት ሀዘኗን እና ቁጭቷን በውስጧ ይዛ ወደ ህግ ሄደች፤ ፍረዱኝ። ህጻን ልጄን አበላሸበኝ፤ ስትልም ክሷን እና አቤቱታዋን አቀረበች።

የእሷን አቤቱታ የሰሙ የመንደሯ ሰዎችም ልጆቻቸውን መጠየቅ ጀመሩ። አንዱ የታዳጊው ጓደኛ እሱም የችግሩ ተጠቂ መሆኑን እና ግለሰቡ በተደጋጋሚ በቤቱ እየወሰደው የግብረሰዶም ወንጀል እንደፈጸመበት ለወላጅ አባቱ አረዳቸው። ይህንን የሰሙም አባት ቤታቸው ቁጭ ብለው ደቂቃዎችን ማባከን አልፈለጉም በአፋጣኝ ወደአካባቢያቸው ፖሊስ ጣቢያ ሄዱ፤ ፖሊስም ወደ ህክምና ላካቸው። የህክምና ማስረጃቸውን ይዘው በመመለስም ክሳቸውን መሰረቱ።

ፖሊስ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር አውሎ ሶስት የክስ መዝገቦችን አደራጅቶ ምርመራውን በማድረግ ክስ መሰረተበት። ክሱን የመሰረቱት የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የሴቶችና ህጻናት ወንጀል ምርመራ ማስተባበሪያ ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ጸጋዬ ታምራት እንደሚሉትም፤ ” ከአንደኛው ከሳሽ በተጨማሪ የሁለተኛና ሶስተኛ ከሳሾችን አቤቱታ በመቀበልና ምርመራውን በማስፋት የህክምና እንዲሁም የአቃቤ ህግ ማስረጃዎችን በማጠናቀር ለፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ እንዲቀርብ ሆኗል”። ለፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የቀረበው ክስ ላይም ግለሰቡ የጥፋተኝነት ውሳኔ እንዲተላለፍበት አድርጓል።” ያሉት ምክትል ኢንስፔክተር ጸጋዬ፣ በዚህም መሰረት ግለሰቡ በ19 ዓመት 6 ወራት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ፍርድ ተሰጥቷል።

ግብረሰዶማዊነትን ለመከላከል በሚሰራው ስራ ላይ ሁሉም ሰው ጥቆማን ከመስጠት ጀምሮ አጥፊዎችን ለህግ በማቅረቡ ሂደት ላይ የበኩሉን መወጣት እንዳለበትም አሳስበዋል።

“ቤተሰብም ልጆቹ የት እንደሚውሉ፣ ምን እንደሚያደርጉ መቆጣጠር፣ አጠራጣሪ ነገሮችንም ሲያዩ ልጆቹን መጠየቅና መከታተል ያስፈልጋል።” ያሉት ምክትል ኢንስፔክተር ጸጋዬ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ወንጀሉ ተፈጽሞ ሲገኝ ቤተሰብ ልጆቹን መሸሸግ አልያም ሰው ምን ይለኛል ብሎ ሳይሳቀቅ በቀጥታ ወደ ህግ መምጣት እንዳለበትም መክረዋል።

እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You