በቅርቡ የሕዝብ የተወካዮች ምክር ቤት የገቢ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የገንዘብ ሚኒስቴርን የ2011 የዘጠኝ ወር እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ባዳመጠበት ወቅት የመንግሥት መስሪያ ቤቶች የግዢ አካሄድ ችግር ያለበት መሆኑን ጠቁሟል። የቋሚ ኮሚቴው አባል አቶ ኑር አሚን ሰይድ ሪፖርቱን መሠረት አድርገው በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ለፌዴራል መስሪያ ቤቶች የሚደረገው የማዕቀፍ ግዢ ጥራቱን ጠብቆ በወቅቱ እየተከናወነ አይደለም።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ሥርዓቱን ያልተከተለ ግዢ እየፈፀሙ እንደሆነ በመግለፅ በሌላ በኩል ደግሞ የተማከለ ግዢ እንዲፈፀምላቸው እየጠየቁ ያሉ ተቋማት ሥራቸው ላይ ተፅእኖ እየፈጠረባቸው እንደሆነ አብራርተዋል። በተጨማሪም በርካታ ተቋማት በእነሱ በኩል እንዲገዙ የተፈቀደላቸውን ዕቃ መንግሥት ባስቀመጠው የግዢ ሥርዓት መሠረት እያከናወኑ ባለመሆኑ የጥራት የመጠንና በወቅቱ ዕቃዎች ለአገልግሎት ያለመቅረብ ችግር በስፋት እየተስተዋለ መሆኑን አመልክተዋል። እንደዚህ ዓይነት አካሄዶች ደግሞ ለሙስናና ብልሹ አሠራር በር ከመክፈታቸውም ባሻገር የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት ለብክነት የሚዳርጉ በመሆናቸው ጠንካራ ክትትል ማድረግ ይጠበቃል ብለዋል።
በገንዘብ ሚኒስቴር የፊሲካል ፖሊሲና የበጀት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እዮብ ተካልኝ በበኩላቸው የማዕቀፍ ግዢ በተጠበቀው መጠን በወቅቱ መከናወን እንዳልቻለ በመግለፅ ችግሩ የተከሰተበትንም ምክንያት አብራርተዋል። እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ጨረታው ከወጣ በኋላ መመሪያውን ሳያሟሉ የቀረቡ አቅራቢዎች ስለነበሩ ሁለት ጨረታዎች እንዲሰረዙ ተደርጓል። በተጨማሪም የዕቃዎች መለያ (ስፔስፊኬሽን) ሲዘጋጅም የደረጃዎች ኤጀንሲ በወቅቱ መረጃ አለመስጠቱ ለመዘግየቱ አንዱ ምክንያት ነበር።
እንደ ሀገር የማዕቀፍ ግዢ የሚከናወንባቸው ሰባት ሎቶች ናቸው። ከዚህ ውስጥ ዘግይቶም ቢሆን በአሁኑ ወቅት መጨረስ የተቻለው የሦስቱን ሎቶች ብቻ ነው። የእነዚህ ሎቶች አሸናፊ የሆኑትም ምርጫ ከተደረገ በኋላ እንዲያውቁት ተደርጓል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ሆኖ በአቅራቢዎቹ ከውል በኋላም ዕቃውን ለማዳረስ ጊዜ የሚወስድባቸው በመሆኑ ተቋማቱ ዕቃ ባለማግኘታቸው ሥራ እንዳይስተጓጎል በማሰብ ገንዘብ ሚኒስቴር የማይደርሱትን ሎቶች በመለየት እያንዳንዱ ተቋም በሕግና በመመሪያው መሠረት ግዢ እንዲፈፅም ትእዛዝ ሰጥቷል። በዚህ መሠረትም ግዢ እየፈፀሙ ናቸው። በመሆኑም ተቋማቱ ራሳቸው እንዲገዙ ፈቃድ ስለተሰጠ በመዘግየቱ እነሱ ላይ የተፈጠረ ችግር የለም። ነገር ግን መንግሥት የማዕቀፍ ግዢ በመከናወኑ በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንስለት የነበረውን ገንዘብ ማዳን አለመቻሉ አንድ ችግር ነው ብለዋል።
የፌዴራል የግዢና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ማርታ ሉዊጂ “ያለፈው ሦስት ዓመት የማዕቀፍ ግዢ ውል የሚጠናቀቀው ኅዳር ላይ ነው። እኛ በታኅሣሥ የማዕቀፍ ግዢው ያለበትን ደረጃ ሰንገመግም ገና የቴክኒክ ግምገማውም ስላልተጠናቀቀና በወቅቱ እንደማይደርስም በመገንዘብ በታኅሣሥ ሁሉም መስሪያ ቤቶች በራሳቸው ግዢ እንዲያከናውኑ አስታውቀናል።“ ሲሉ ይገልጻሉ።
እንደ ዋና ዳይሬክተሯ ገለጻ፤ ለግዢ በወቅቱ አለመከናወን የማዕቀፍ ግዢው መዘግየት ዋናው ምክንያት አይደለም። ጥራትንም በተመለከተ በቀዳሚነት መቆጣጠር ያለበት ራሱ ግዢ የሚከናወንለት ተቋም ነው። ግዢ በማዕቀፍ እንዲከናወን የተደረገው ተመሳሳይ ፍላጎት ያላቸው መስሪያ ቤቶች ግዢ በአንድ ላይ ሲሆን፣ መንግሥት የተሻለ ዋጋና ጥራት እንዲያገኝ ስለሚያስችል፤ ብክነትንም ለመቀነስ ስለሚረዳ ነው።
በዚህ በኩል እስከ ቅርብ ጊዜ ጥሩ አፈጻፀም እንዳለ ወይዘሮ ማርታ ጠቅሰው፣ ከ2010 ጀምሮ የግዢ ትዕዛዝ ከተሰጠ በኋላ ከውጭ ምንዛሬ እጥረት ጋር በተያያዘ በታሰበው መልኩ ሲከናወን አልነበረም ይላሉ። ሁልጊዜ ውልም ከተገባ በኋላ በመስሪያ ቤቶችም በአቅራቢዎችም በኩል የሚታዩ ክፍተቶች አሉ ይላሉ።
እንደ ወይዘሮ ማርታ ገለጻ፤ በመስሪያ ቤቶች በኩል ከግዢ እቅድ ጀምሮ እቅዱን በደንብ አለማዘጋጀት በእቅዱ መሠረት ወቅትን ጠብቆ ግዢ አለመፈጸም ይታያል። አንዳንዶቹ ጨረታ ሲያዘጋጁ በደረጃው መሠረት ቢያወጡም አቅራቢዎችን ሲገመግሙ የሚያቀርቧቸው መስፈርቶች በጨረታ ሰነዱ ከተቀመጠው ውጪ በመሆኑ አድላዊ የሆነ የግዢ ሕግ ጥቶች ያለባቸውም ሆነው ይገኛሉ። በአቅራቢዎችም በኩል አቅራቢዎች አሸናፊ ከሆኑ በኋላ ውል ገብተው የዋጋ ማቅረቢያ ሰነድ ለመስጠት ፈቃደኝ አለመሆን፤ የውጪ ምንዛሬ እጥረትን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች በወቅቱ አለማቅረብ፤ አንዳንዶቹም በመጋዘናቸው ዕቃዎችን ይዘው የለንም፤ አልገባም በማለት የሚያመላልሱ አሉ።
ከላይ የቀረቡት ዓይነት ችግሮች አድርሰውብናል ተብሎ ቅሬታ ከቀረበባቸው አቅራቢዎች መካከልም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 397 የጥፋተኝነት ሪፖርት ቀርቦ ውሳኔ ተሰጥቶባቸዋል። ከውጭ ምንዛሬ ጋር በተያያዘ ለሚነሳውም ቅሬታ ባገኙት ያህል እንዲያቀርቡ እየተሰራ ሲሆን በማዕቀፍም ሆነ በግል ግዢ ሲከናወን ከአቅራቢዎች ጋር እየተፈጠረ ያለውን አለመግባባት ለመቀነስም ከንግድ ምክርቤትና ዋና ዋና አቅራቢዎች ውይይት እየተደረገ ነው።
በነባሩ የ2001 የመንግሥት ገዢና ንብረት አስተዳደር ሕግ ጥሰት ሲገኝ ኤጀንሲው እርምጃ የሚወስድበት አግባብ የለም። የሚሉት ዋና ዳይሬክተሯ፣ አዲስ የሚዘጋጀው ይህንን ጨምሮ ከጊዜው ጋር ሌሎችንም ሕጎች እንደሚያካትት ይጠበቃል ብለዋል። በተለምዶ ግን በተገኘው የኦዲተ ግኝት መሠረት ማስተካከያ እንዲያደርጉ ለየተቋማቱ ግብረ መልስ እንደሚሰጥ ጠቅሰው፣ ይሄንን ተከትለው ካልሰሩ ግን ለገንዘብ ሚኒስትር ሪፖርት እንደሚደረግ ይገልጻሉ።
ወይዘሮ ማርታ እንዳብራሩት፤ እንዳጠቃለይ ከግዢ ጋር የተያያዙ ችግሮች እየተከሰቱ ያሉት ግን በተቀመጠው የግዢ ሥርዓት መሠረት መከናወን ባለመቻላቸው ነው። ለምሳሌ ግልፅ ጨረታ መጠቀም ጥሩና ደረጃውን የጠበቀ ዕቃ በወቅቱ የሚያቀርብ አቅራቢና ተመጣጣኝ ዋጋ ለማግኘት ያስችላል። ነገር ግን ሁሉም የመንግሥት ግዢዎች የግድ በግልፅ ጨረታ መፈፀጸም አለባቸው ማለት አይደለም። እንደየሁኔታው እያንዳንዱ ተቋም ከግልፅ ጨረታ እስከ አንድ አቅራቢ ሰባት ዓይነት መንገዶችን መጠቀም የሚያስችለው አሠራር አለ። ለምሳሌ በትምህርት ተቋማት በአብዛኛው የመጽሐፍና የምግብ ፍጆታ ግዢ በለቀማ (አንድ ዓይነት መጽሐፍ ከተለያዩ አቅራቢዎች በተለያየ መጠን) መግዛት የሚያስችል ሥርዓት አለ። ነገር ግን በነዚህም ተቋማት ውስጥ የአቅምና የውሳኔ አሰጣጥ ችግር በመኖሩ በአግባቡ ሲጠቀሙበት አይታይም። በእነዚህ ተቋማት አብዛኛው የነበረው ችግር የግንዛቤና በግዢ ክፍሎቻቸው በየወቅቱ አማራጮችን አቅርቦ የሚያስፈፅም የተደራጀ የሰው ኃይል አለመኖር ነው። ይህንንም ለመቅረፍ በቅርቡ የአርባ ስድስቱን ዩኒቨርሲቲዎች የግዢ ባለሙያዎች፤ የግዢ አፅዳቂ ኮሚቴዎች፤ ፋይናንስና የዩኒቨርሲቲዎቹ አመራሮች ባሉበት ውይይት ተደርጓል።
“የግዢ ሥርዓቱና መመሪያው ላይ ብቻ ሳይሆን ኤጀንሲው የሥራ ድርሻን በተመለከተ የግንዛቤ ውስንነት” አለ የሚሉት ዳይሬክተሯ፣ ‹‹የግዢ አሠራሮች በየወቅቱ ይከለሳሉ በየዓመቱም ሁሉም የፌዴራል መስሪያ ቤቶች በየትኛው የግዢ ዘዴ መቼና እንዴት እንደሚፈፅሙ የሚያስረዳ የግዢ እቅድ እንዲያዘጋጁ ይደረጋል። ያንንም በግዢ አፅዳቂ ኮሚቴ በግዢ ክፍሉና የበላይ ኃላፊው ታይቶ ለኤጀንሲው ይልካል። ይሄን የሚያደርጉት የተፈቀደላቸውን በጀት መሠረት አድርገው ነው።›› ይላሉ።
ወይዘሮ ማርታ እንዳብራሩት፤ ኤጀንሲው ደግሞ በመንግሥት ግዢና ንብረት ኦዲት ዳይሬክቶሬት በኩል የግዢ ሥርዓቱን ተከትሎ ተፈፅሟል ወይ የሚለውን የሚቆጣጠረውና የሚከታተለው ይህንኑ ሥርዓት መሠረት አድርጎ ነው። በዚህም በየዓመቱ ሁሉንም የፌዴራል መንግሥት ተቋማትን በግዢና ንብረት አስተዳደር ዙሪያ ያደረጉት እንቅስቃሴ ኦዲት ይደረጋል። በዚህ ውጤት መሠረት መስተካከል ያለበት ነገር ካለ ግብረ መልስ ይሰጣቸዋል። ተገቢውን ሥርዓት ተከትለው የግዢ እቅድ አቅደዋል ወይ ባቀዱት መሠረት ግዢውን አከናውነዋል ወይ የሚለውን ገምግሞ ግብረ መልስ ከመስጠት አንፃር ኤጀንሲው ክፍተት ነበረበት። ይሄ ሊከሰት የቻለው ደግሞ በሞያተኛ እጥረት ነው።
በመንግሥት ስር ካሉት ከ180 በላይ መስሪያ ቤቶች በየወቅቱ ጥያቄ እንደሚቀርብ ጠቅሰው፣ ያንን ለመወጣት የሚያስችል የሰው ኃይልም የቢሮ አደረጃጀትም ኤጀንሲው እንደሌለውና እነዚህንም ችግሮች ለመቅረፍ የተጀመሩ ሥራዎች ግን እንዳሉ ያመለክታሉ።
እንደ ዋና ዳይሬክተሯ ገለጻ፤ ጥራትን በተመለከተ የጥራት ደረጃን ከመጀመሪያው የሚያዘጋጀው እያንዳንዱ ተቋም ነው። ተቋማቱ የሚፈልጉትን ዕቃ በዚህ የጥራት ደረጃ ብለው ያቀርባሉ ይሄ የግዢ ፈፃሚ ተቋማት ተግባር ነው። በቀረበው ስፔስፊኬሽን መሠረት ዕቃው ደረጃውን ጠብቆ አሟልቶ መግባቱንም የሚቆጣጠረው ራሱ መስሪያ ቤቱ ነው። ይሄ በማዕቀፍም ሲገዛ በቀረበው የጥራት ደረጃ መሠረት ካልቀረበ አይቶ መመለስ የመስሪያ ቤቱ ነው። በዚህ በኩል በርካታ ተቋማት ዝርዝር መስፈርቶችን ያሟሉ የግዢ ጥያቄዎችን ማቅረብ ላይ ክፍተት አለባቸው። የተገዛውንም ዕቃ በተቀመጠው መስፈርት መሠረት መሆኑን አጣርቶ የመቀበልም ችግር አለባቸው።
ይሄ ሊከሰት የሚችለው በአንድ በኩል እውቀቱም ግንዛቤውም እያለ ከሥነ ምግባር ጋር በተያያዘ ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ከአቅም ውስንነት ጋር በተያያዘ ነው። ይህንንም ለመቅረፍ በቀዳሚነት መስራት ያለበት ራሱ ተቋሙ ነው። ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ ኤጀንሲው በአካል በስልክ በጽሑፍ ለሚቀርብ ጥያቄ ምላሽ በመስጠትና የሞያተኞችን ብቃት ለማሳደግም የሚያደርገው ድጋፍ አለ ። በየወቅቱም ሥልጠናም ይሰጣል። በአሁኑ ወቅትም የሁሉም ተቋም የግዢ ክፍል በሞያው በሰለጠኑ ሰዎች እንዲመራ ለማስቻል ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር የሞያ ሥልጠና በተከታታይነት እየተሰጠ ይገኛል። በተጨማሪም ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት የሚሰጠውም ሥልጠና አምስተኛ ዙር ደርሷል። እስካሁን ከአንድ ሺ በላይ ሠራተኞችን ለማሰልጠን የተቻለ ቢሆንም፣ ሥልጠና ከወሰዱ በኋላ የሚለቁ በመኖራቸው ይህን ለማስቀረት ተቋማቱ ሊሰሩ ይገባል።
እንዳጠቃለይ የዘርፉን ችግር ለመፍታት ግን አብዛኛውን ችግር ይቀርፋል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የኢ ፕሮኪዩርመንት (የኤሌክትሮኒከስ ግዢ ሥርዓት) ኦን ላይን እየተዘጋጀ ነው ያሉት ሥራ አስኪያጇ፤ እየተጠናቀቀ ባለው በጀት ዓመት በሰባት መስሪያ ቤቶች ለመሞከር መታቀዱን ተናግረዋል። ይህ ተግባራዊ ሲሆን ተገቢው መረጃ ስለሚገኝና የውድድር ሥርዓቱንም ስለሚያሳልጠው ችግሮች ይቀረፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 13/2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ