ሀገር የማንነታችን መገለጫና የህልውናችን መሰረት ናት። እናት ደግሞ የሀገር ተምሳሌት ናት። እናት መኖሪያችን ፣እናት ፍቅራችን፣እናት የህይወታችን ትርጉም ናት። ብቻ እናትና ሀገር የማይነጣጠሉ የህይወታችን ክፋዮች ናቸው።
ወ/ሮ ሀረገወይን አሰፋ የ36 ዓመት ጎልማሳ ስትሆን በትዳር ውስጥ ለ13 ዓመታት ያህል አሳልፋለች። በዚህ ጊዜ ውስጥ ሁለት ልጆችንም አፍርታለች። የትዳር አጋሯ ኑሮውን በውጭ ሀገር ካደረገ ረዥም ጊዜያትን አሳልፏል። ከአንድ ዓመት በፊት ግን ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ኑሮውን አዲስ አበባ አድርጓል ።ሆኖም በጥንዶቹ ቤት ዘወትር አለመግባባቶች ይፈጠራሉ። ሁልጊዜም ሽማግሌ ገብቶ ያስታርቃቸዋል ።ወ/ሮ ሀረገወይንም ትዳሬ ችግር ውስጥ ነው በማለት ለሚቀርቧት ሰዎችም ትናገር ነበር።
ህዳር 29/2015ዓ.ም ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ተኩል ሆኗል። በወ/ሮ ሀረገወይንና በባለቤቷ መካከል ጭቅጭቅ ተፈጥሯል። በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ልዩ ቦታው አርሴማ አደባባይ ገባ ብሎ ካለው መኖሪያ ቤት ውስጥ ፍቺ መፈጸም አለብን በሚል በተፈጠረ አለመግባባትና ከሌላ ወንድ ጋር እጠረጥርሻለሁ፤ እምነት አጉድለሻል በሚል ከፍያለ ጭቅጭቅ ተፈጥሯል።
የከረረው ጭቅጭቅና ያስከተለው መዘዝ
በሁለቱ ጥንዶች መካከል ያለው ጭቅጭቅ ገላጋይ ባለማግኘቱ ተባብሷል። ጭቅጭቁ ተባብሶ ወደ ድብድብና የኃይል እርምጃ ተሸጋግሯል።አባወራ እጀታው የእንጨት በሆነ የአጥንት መከትከቻ መጥረቢያ አንገቷ ላይ ደጋግሞ ይመታል። በዚህ ጊዜ ወ/ሮ ሀረገወይን ዱላውን መቋቋም ሲያቅታት ተዝለፍልፋ ትወድቃለች። በዚያውም ህይወቷ ያልፋል።
የፖሊስ ማስረጃ
መረጃው የደረሰው ፖሊስ ወንጀሉ በተፈጠረበት ቦታ ይደርሳል። የሰውና የቴክኒክ ማስረጃም ይወስዳል። እጀታው የእንጨት በሆነ የአጥንት መከትከቻ መጥረቢያ አንገቷ ላይ ደጋግሞ በመምታት ጉዳት አድርሶ ህይወቷ እንዲያልፍ ያደረገ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ባደረገው ምርመራ ማጣራት ችሏል።
በሟች ሀረገወይን አሰፋና በባለቤቷ መካከል የተፈጠረ አለመግባባት የትዳር አጋሩንና የልጆቹን እናት ህይወት እንዲያጠፈ አድርጎታል። ተጠርጣሪና ሟች በትዳር አብረው ሲኖሩ በተደጋጋሚ አለመግባባት ተከስቶ በሽማግሌ ሲታረቁ እንደቆዩ ለፊቺም ፍርድ ቤት ከደረሱ በኋላ በሽማግሌ ጥረት አብረው እንደቆዩ የፖሊስ መረጃ ያሳያል።
የቤተሰብ ምስክርነት
የዘወትር ጭቅጭቅና ፀብ መነሻ የሆነው ከሌላ ወንድ ጋር እጠረጥርሻለሁ አላምንሽም በሚል ምክንያት በሚጣሉበት ወቅት በመካከላቸው በተደጋጋሚ ጊዜ ሽማግሌ ሆነው ሲያስታርቁ የቆዩት አገላጋይ አክሊሉ ላንቀ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጻዋል። እሳቸው እንደተናገሩት፤ በተደጋጋሚ አለመግባባቶች እንዳለ ሟች በተደጋጋሚ እየመጣች እንደምትነግራቸውና ትዳሬ ችግር ውስጥ ነው ፀልዩልኝ እያለች እንደምትማጸናቸው አስረድተዋል።
ሽማግሌውም በፀሎት፣ በምክር ትዳር እንዳይፈርስ ብዙ ጥረት እንዳደረጉ ባለቤቷን በማግኘት ‹‹በዓይንህ ያላየኸውን ነገር አትመን ተው›› በማለት ‹‹ከአንተ የተወለዱ ልጆችን ማሳደግ፤ ከሚስትህ ጋር ጊዜ ማሳለፍ ፤ሚስትህን መንከባከብ የአንተ ኃላፊነት ነው›› በሚል ብዙ እንደነገሩት ተናግረዋል።
ሟች ሀረገወይን አሰፋ ባለቤቷ ሀገር ውስጥ ባለመኖሩ ለረዥም ዓመታት ልጆቿን ለብቻዋ አሳድጋለች። ባለቤቷ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ልጆቻቸውን በጋራ ለማሳደግና አብረው ወደ ውጭ ሀገር ለመሄድ አስበው ነበር ። ነገር ግን ሳይሆን ቀርቷል።
የሟች እህት ወሰን አሰፋ እንደምትናገረው፤ ባለቤቷ ከውጭ ሀገር ከመጣ ከአንድ ዓመት በላይ እንደሆነውና የመጣውም ከሟች ጋር የመኖሪያ ቤታቸውን ሠርተው አንድ ላይ ለመኖር እንደነበርና ሟች የውጭ ፕሮሰስ ጨርሳ እንደነበር። ሆኖም ቤተሰብ ለሽኝት እንጂ ይህ ይመጣል ብሎ እንዳላሰበ ትናገራለች።
የሟች ሀረገወይን አሰፋ ቤተሰቦች በሰላም ያሳደርከን፤ በሰላም አውለን ብለው ወደ ስራቸው ሄደዋል። ስልክ ተደውሎ የሰሙትን ነገር ግን ማመን አቅቷቸዋል። የሟች እህት በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ስትናገር ‹‹በድንገት ቶሎ ድረሺ ›› ተብሎ እንደተደወለላትና በቦታው ስትደርስ ፖሊስና ሕዝብ ተሰብስቦ እንደደረሰች ትናገራለች። ከመኪና ስትወርድ ክፉኛ መደናገጧን ‹‹እህቴ በህይወት ካለች ህይወቷን እናትርፍ፤ ከሞተችም ንገሩኝ›› ስትል እንደጠየቅችና ሆኖም አስደንጋጭ በሆነ መልኩ በሰው እጅ እንደተገደለች እንደተነገራት ትገልጻለች።
የሟች ወንድም ቶማስ አሰፋ እንደሚናገረው፤ ችግሩ እንደተፈጠረ እህቱ ደውላ እንደነገረችው እና በዛው ሰዓት ወደ ሟች መኖሪያ ቤት ያመራል። በቦታው ሲደርስ ፖሊስ በአካባቢው በብዛት እንደነበር እርሱም ወደ ውስጥ መግባት እንዳልቻለ ይናገራል። በኋላም ፖሊሶች ፈቅደውለት ወደ ውስጥ እንደገባ ያየው ነገር ልብ ሰባሪ እንደነበር ገልጿል።
ሌላኛው የሟች ቤተሰብ የሆነው ሰለሞን ታደሰ ስለጉዳዩ ሲናገር፤ በግል ጉዳይ ለረዥም ሰዓት በስልክ እያወራ እንደቆየ፤ በዚህም ምክንያት ከቤተሰብ ስልክ ደውለው እርሱን ማግኘት ስላልቻሉ ሰው ተልኮ ስለ ጉዳዩ እንደሰማ ይገልጻል። ቤት ሁሉም እራሳቸውን እንደሳቱ እንደተነገረው፤ ምንድነው ብሎ ወደ ቤት ሲሄድ የተፈጠረውን ነገር እንደተመለከተ ይናገራል። ‹‹ተነጋግሮና ተግባብቶ መኖር በሚቻልበት በዚህ ዘመን በአጉል ጥርጣሬ ተነስቶ በአሰቃቂ ሁኔታ የትዳር አጋሩን ህይወት ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ማጥፋት የከፋ ወንጀል መሆኑን ይናገራል።
መርማሪ ሳጅን ሀብታሙ ገብሬ እንደሚናገሩት፤ ተጠርጣሪው ወንጀሉን ከፈፀመ በኋላ ከዚህ በፊት ሽማግሌ ሆኖ ያስታርቃቸው የነበረ ጓደኛው ጋር ደውሎ ጉዳዩን እንደነገረ ጓደኛው በስልክ መረጃውን ለፖሊስ እንዳደረሰ ተናግረዋል። የተጠርጣሪው ጓደኛ በወቅቱ ስለነበረው ሁኔታ ሲናገር ተጠርጣሪው ለእርሱ ደውሎ የግድያ ወንጀል እንደፈፀመ እንደነገረው ተናግሯል።
ይህንን የሰማው ጓደኛው ወደ ተጠርጣሪው ሰው ቤት ያመራል። በቦታው እንደደረሱም ተጠርጣሪ ወንጀለኛም በሩን ይከፍትላቸዋል። ሁኔታውንም ለፖሊስ ደውሎ እንዳሳወቀ ይነግራቸዋል። መኖሪያ ቤቱ ወደ ውስጥ ገባ ያለ በመሆኑ ፖሊሶች ለማግኘት የተወሰነ ስለተቸገሩ እርሱ እየመራቸው ወደ ሟች መኖሪያ ቤት እንደደረሱ ያስረዳል።
አንዳንድ ጊዜ በመፍራት ፣ ቻይ በመሆን ፍቅራችንንና ትዳራችንን ያቆየን የሚመስለን ሰዎች አንጠፋም። ይህም ሟች ከባለቤቷ ጋር ያለው አለመግባባት በቤተሰብ እየተፈታ ወደ ቤቷ ትመለስ ነበር። ልጆቿን ይዛ ሁለት ቀን ቤተሰብ ጋር ቆይታ በመጣች ማግስት ነው ይህ የወንጀል ድርጊት የተፈፀመው።
የሟች እህት እንደምትናገረው እንደማንኛውም ሰው በመካከላቸው አልፎ አልፎ ፀብ እንዳለ ቤተሰብ ገብቶ እንደሚያስታርቅ ትናገራለች። ህይወቷ ከማለፉ ጥቅት ቀናት በፊት ሟች ልጆቿን ይዛ ወደ ቤተሰብ እንደመጣችና ለተወሰኑ ቀናት እዛው ትቆያለች። ሟች በቆይታዋም ደስተኛ ነበረች። ተጨዋውተው ተሳስቀው ወደ ቤቷ እንደተመለሰችም ገልጻለች።
የሟች ወንድም በበኩሉ እንደሚናገረው፤ ባለቤቷ ውጭ ሀገር እንደመሆኑ መጠን ሟችና ልጆቿ ብዙ ጊዜ ቤተሰብ ጋር እንደሚያሳልፉ ተናግሮ፤ በሟችና በተጠርጣሪው መካከል አልፎ አልፎ ግጭት እንደነበር እና ሆኖም እስከ ሞት የሚያደርስ ሁኔታ ይፈጠራል ተብሎ እንደማይታሰብ ተናግሯል።
የወይዘሮዋ ሞት ከራሷ አልፎ የወለዷቸው ልጆቻቸው ላይም ትልቅ ጠበሳ አሳድሯል። የሟች ወንድም ሲናገር ልጆቹ ትመጣለች ብለው በር በር ሲያዩ ያለው ስሜት የሚያም እንደሆነ ይገልፃል። እንደ ቤተሰብ ከባድ ጊዜ እያሳለፉ እንደሆነ ተናግሮ ከዚህ በኋላ ልጆቹን ስለሁኔታው ማስረዳት ሌላ ፈተና እንደሆነባቸው ገልጿል።
የሟች እህት ስለሁኔታው በእንባ ታጅባ ስትናገር፤ ተለያይቶ እህትና ወንድም ሆኖ መኖር እየተቻለ እርሱ ውጭ ሀገር እየኖረ የአብራኩ ክፋይ ልጆቹን በሥነ ሥርዓት ለብቻዋ እናትም አባትም ሆና ያሳደገችን ሴት እንዲህ በጭካኔ መግደል አዕምሯቸው ያልተቀበለው ነገር እንደሆነ ገልፃለች።
ሌላኛው የሟች ቤተሰብ ሲናገር፤ በዚህ በረቀቀ ዘመን ካልተግባቡ መለያየት እያለ ለወንጀልና ሰው ለመግደል መቸኮል በእጅጉ ከባድ እንደሆነ ያስረዳል።
አለመግባባት ሲከሰት በኃይልና በጉልበት ለመጠቀም ከማሰብ ይልቅ በመነጋገር መፍታት ብልህነት ነው። መርማሪ ሳጅን ሀብታሙ ገብሬ እንደሚናገሩት፤ በባልና በሚስት መካከል የማያግባቡ ብዙ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። እንዲህ አይነት ነገር ሲከሰት በንግግር የሚፈታ ከሆነ በንግግር መፍታት ይገባል፤ ይህ የማይቻል ከሆነ በህጋዊ መንገድ መለያየት ሲቻል ወደ መጠፋፋት መሄድ አግባብ እንዳልሆነ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ሳጅን ሀብታሙ ሲናገሩ፤ እነዚህ ግለሰቦች በመካከላቸው ሁለት ልጆችን አፍርተዋል። ልጆች ደግሞ ከወላጆቻቸው ጋር ማደግ አለባቸው። አሁን እነዚህ ልጆች ሁለቱንም ወላጆች ነው ያጡት። እናትን በሞት አባትን ደግሞ በእስር። ይሄ ሁሉ መሆን ያልነበረበት እንደሆነ ተናግረዋል።
የሟችና የተጠርጣሪ የጋራ ወዳጅ የሆነው አገልጋይ አክሊሉ ላንቃ እንደሚናገረው፤ በመካከላቸው ብዙ ጊዜ አለመተማመን አለ፤ጥርጣሬ አለ፤ እርሱ እርሷን፤ እርሷ ደግሞ እርሱን፤ ያለማመን ችግር ነበር።ያለመተማመን ደግሞ መጨረሻው አያምርም። አንድ ሰው ከአንድ ሰው ጋር በአንድ ቤት እስከ ኖረ ድረስ መተማመን መኖር እንዳለበትና ይህ መሆን ካልቻለ ግን በሰላም መለያየት አማራጭ መሆኑን ያስረዳሉ።
የሟች እህት በበኩሏ ‹‹በዚህ ዘመን ማንኛውንም ነገር በመነጋገር መፍታት ይቻላል፤ ካልተስማሙ ደግሞ በሰላም መለያየት አማራጭ ነው። ህይወት ይቀጥላል ፤ተለያይቶ ልጆችን ማሳደግ ይቻላል።ነገር ግን ይህ ሁሉ አማራጭ እያለ የሰውን ነፍስ ማጥፋት ለምን›› ስትል ትጠይቃለች።
መርማሪ ሳጅን ሀብታሙ እንደሚናገሩት፤ አለመግባባት ሲከሰት ልጆችን ወደ ሌላ ቦታ በመውሰድ ሁለቱ ሰዎች በንግግር ችግሮችን ለመፍታት መሞከር አለባቸው። ቁጭ ብለው የእኔ ችግር ምንድነው፤ የአንተ ወይም የአንቺ ችግር ምንድነው የሚለውን መነጋገር መቻል አለባቸው። ዘመድ አዝማድ አሰባስበውም ችግሮችን ለመፍታት ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። በዚህ ካልሆነ በሰላም መለያየት መቻል አለባቸው እንጂ ወደዚህ አይነት መጥፎ ውሳኔ ለመድረስ መጣደፍ የለባቸውም ብለዋል።
የሁለቱም የጋራ ጓደኛ የሆነው አገልጋይ አክሊሉ በበኩሉ፤ እግር ከእግር ጋር እንኳ ይጋጫል፣ ሲኒ ከሲኒ ጋር ይጋጫል፣ አለመግባባት ሲፈጠር ማንኛውም ሰው እራሱን መግዛት እንዳለበት ተናግሯል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን መስከረም 26/2016