በጥቅምት ወር በምዕራብና በደቡብ አጋማሽ አካባቢዎች ከባድ ዝናብ ይኖራል

አዲስ አበባ፡- በጥቅምት ወር በምዕራብና በደቡብ አጋማሽ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በመጪው ወር በምዕራብና በደቡብ አጋማሽ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ይጥላል።

በጸሐይ በመታገዝ ከሚፈጠር ከባድ ደመና ጋር ተያይዞ በምዕራብና በደቡብ አጋማሽ የሚፈጠረው ከባድ ዝናብ ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ላይ የአፈር መሸርሸርና በእርሻ ማሳዎች ላይ ውሃ መተኛት ሊያጋጥም ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል።

የደቡብና ደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ ዋና ዋና ተፋሰሶች ላይ የእርጥበት ሁኔታው እንደሚጠናከር ያመላከተው ኢንስቲትዩቱ፤ በተጨማሪም የመካከለኛው አዋሽ፣ የደቡባዊ ተከዜ ተፋሰሶች ላይ መጠነኛ እርጥበት እንደሚኖር አስታውቋል።

የደቡብና የደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያን ጨምሮ በምዕራብና በደቡብ ምዕራብ ቀጣይነት ያለው የዝናብ ሁኔታ እንደሚኖር የገለጸው ኢንስቲትዩት፤ በሰሜን አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ደረቃማ፣ ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ፀባይ ጎልቶ እንደሚታይ አመላክቷል።

በሚቀጥለው ወር በምዕራብና በደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የተሻለ የዝናብ ስርጭት እንደሚኖራቸው በመጥቀስ፤ በደቡብ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የተሻለ የእርጥበት ሁኔታ እንደሚኖር ገልጿል።

በተለያዩ አካባቢዎች ላይ አልፎ አልፎ ጠንካራ ደመናዎች እንደሚፈጠሩ የተመላከተ ሲሆን፤ በሰሜንና በደቡብ ወሎ፣ እንዲሁም አንዳንድ የትግራይ አካባቢዎችን ጨምሮ በደቡብ አፋር ዞን ሶስት፣ ዞን አራትና ዞን አምስት፣ እንዲሁም የምዕራብ አርሲ አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ በመግለጫው ተመላክቷል።

ወቅታዊ ዝናብ ማግኘት በሚጀምሩትና የደቡባዊው የሀገሪቱ ክፍሎች በደጋማ አካባቢዎች ቀደም ብሎ የማሳ ዝግጅት ለማድረግና ዘር ለመዝራት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ኢንስቲትዩቱ በመግለጫው አስታውቋል።

በተጨማሪም የአየር ሁኔታው በደቡብና ደቡብ ምስራቅ፣ በምዕራብና ደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለሚኖሩ አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ለግጦሽ ሳርና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት እንዲሁም ቀደም ብለውና ዘግይተው ለተዘሩ ሰብሎች የውሃ ፍላጎት ለማሟላት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ተገልጿል።

 አማን ረሺድ

አዲስ ዘመን መስከረም 26/2016

Recommended For You