እሬቻ፣ ዕርቅና ሰላም

ኢትዮጵያ በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት የሚከበሩባት ሀገር ናት። በክርስትና እምነት ከሀገር አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና የተሰጣቸው የጥምቀትና የመስቀል ደመራ በዓላትን መጥቀስ ይቻላል። በእስልምና እምነትም እንዲሁ ከዚህ ባሻገር በሀገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦች ዘንድ የሚከበሩ እንደ ሲዳማ ፊቼ ጨምበላላ አይነት ታላላቅ በዓላት አሏት፡፡ እነዚህ የማይዳሰሱ በዓላት የቱሪስት መስህብ በመሆን ለሀገሪቱ የሚያበረክቱት የኢኮኖሚ ፋይዳ ትልቅ ስለመሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ከእነዚህ በዓላት መካከል በዩኔስኮ የተመዘገበው የገዳ ሥርዓት አካል የሆነውና በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ በትልቅ ደረጃ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል አንዱ ነው።

የኢሬቻ በዓል በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ከሚከበሩ በዓላት ቀዳሚውን ሥፍራ የሚይዝ ክብረ በዓል ነው። በዓሉ የሚከበረው የክረምት ወቅት አልቆ የፀደይ ወቅት በሚጀምርበት ወቅት ነው። የዝናብ፣ የጎርፍ እና የጨለማን ወቅት አሻግሮ ለፀደዩ ብርሃን ላዳረሰ አምላክ ምስጋና በማቅረብ ማለት ነው። በአሁኑ ጊዜ የኢሬቻ በዓል በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ አህጉር በቀል ሆኖ በብዙ ሚሊዮኖች የሚከበር እና በሚሳተፈው የሕዝብ ቁጥር ተወዳዳሪ የሌለው በዓል ነው። ይህ ማለት የኢሬቻ በዓል የኦሮሞም ብቻ ሣይሆን በምስራቅ አፍሪካ ጭምር ታላቅ በዓል እየሆነ ስለመምጣቱ ማሳያ ነው።

የኢሬቻ አጀማመር በገዳ አቆጣጠር (አንድ ገዳ 7 ዓመት ከ8 ወር ወይም 8 ዓመት) ከ6 ሺህ 660 ዓመት በፊት የተጀመረ እንደሆነ አዋቂዎች ይናገራሉ። የገዳ ሥርዓት ባለበት፤ የኦሮሞ ሕዝብ በሚገኝበት ሁሉ ኢሬቻ አለ። በዓሉ ዋቄፈንና ከተባለውና ከጥንቱ የኦሮሞ ሕዝብ እምነት የፈለቀ እንደሆነም ይጠቀሳል።

የኦሮሞ ሕዝብ ምድር እና ሰማይን ለፈጠረው ፈጣሪው ዋቃ ምስጋናውን ለማድረስ የኢሬቻ በዓልን ያከብራል ይላሉ የማኅበረሰብ ባህላዊ መሪዎች። ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ ከዘመን ወደ ዘመን በሰላም ላሸጋገረው አምላክ ምስጋና የሚያቀርብበት በዓል ነው።

የኦሮሞ ሕዝብ ክረምቱ በማለፉ በኢሬቻ ቀን ምስጋናውን ለፈጣሪ ያቀርባል። በክረምት ወራት ተራርቆ ሳይገናኝ የቆየ ዘመድ አዝማድ መስከረም ላይ ይገናኛል። ሕዝቡም ክረምቱን በፈጣሪ ፍቃድ የሞላው ውሃ ጎድሎ ከዘመድ አዝማድ አገናኝን ብሎ ምስጋናውን ለፈጣሪ ያቀርባል።

የኦሮሞ ሕዝብ የኢሬቻ በዓልን ለማክበር ሲወጣ እንደ ሣር ወይም አበባ ያሉ እርጥብ ነገሮችን በእጁ ይዞ ይወጣል። የዚህ ትርጉምም ፈጣሪያችን ሆይ አንተ ያጸደቅከው ነው አብቦ ፍሬ ያፈራው፤ ለዚህም እናመስግንሃለን በማለት እርጥብ ነገር ተይዞ ይወጣል፡፡ ሲሉ የታሪክ ምሁራን ይናገራሉ።

በበዓሉ ተሳትፎ ሰፊ ድርሻ ካላቸው አካላት መካከል ወጣቶች በቀዳሚነት ተጠቃሽ ናቸው፤ ወጣት ጆን አሕመድ ከበዓሉ ተሳታፊና አስተባባሪ ከሆኑ ወጣቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ እርሱ እንደሚናገረው፤ የኦሮሞ ሕዝብ ገዳ የሚባል የሃይማኖት፣ የአስተዳደር የዕርቅና መሰል እሴቶችን ይዞ የኖረ ሕዝብ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ የኢሬቻ በዓል የኦሮሞ ሕዝብ ጌታውን የሚያመሰግንበት ሥርዓት ነው ይላል።

የኢሬቻ በዓል በዓመት ሁለት ጊዜ እንደሚከበር የሚገልፀው ወጣት ጆን የመጀመሪያ ኢሬቻ ቱሉ የሚል ስያሜ ያለውና በተራራ ላይ የሚከበር ሲሆን ሌላኛው በወንዝ ዳር የሚከበረው ኢሬቻ መልካ እንደሆነ ያስረዳል። በተራራ ላይ የሚደረገው ኢሬቻ በጋውን በሰላም አሳልፈናል ክረምቱ ደግሞ የሰላም ይሁንልን ተብሎ ለፈጣሪ አደራ የሚሰጥበት ኩነት ነው ይላል፡፡

ላለፉት ዓመታት በዓሉ ተዳክሞ ስለመቆየቱ የሚናገረው ወጣት ጆን ሕዝቡ በተለይም ወጣቱ ባደረገው ትግል ይህንን በዓል መመለስ ተችሏል፡፡ ስለሆነም ወጣቱ ዕሴቱን በጠበቀ፤ ሰላማዊ በሆነ፤ ውበት ባለው መልኩ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በጠበቀ መልኩ መከበር እንዳለበት ይናገራል።

በዓሉ ሰላማዊ ሆኖ እንዲከበር ወጣቶች ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው የሚገልጸው ጆን በበዓሉ በቅድሚያ ሴቶች፤ በመቀጠል አባ ገዳዎች፤ በሶስተኛ ደረጃ ወጣቶች ሆነው ወደ ወንዝ ”መሬሆ” እያሉ ሲወርዱ ወጣቶች ወይም ቄሮዎች ኃላፊነታቸው በዓሉ ያለ አንዳች ኮሽታ ከየትኛውም ፖለቲካዊና መሰል ጉዳይ ነፃ ሆኖ እንዲከበር ማስቻል ነው፡፡ ኢሬቻ የሕዝብ በዓል እንደመሆኑ እሴቱን ጠብቆ ፈጣሪውን ብቻ በሚያመሰግንበት መንገድ ተከብሮ እንዲያልፍ ወጣቶች መወጣት ያለባቸው ሚና ትልቅ እንደሆነ ገልጿል።

በዓሉ ሰላማዊ ሆኖ እንዲከበር በአዲስ አበባ፣ በሸገር ከተማና በቢሾፍቱ የሶስቱም ከተማ ወጣቶች አንድ ላይ በመሆን እየሰሩ እንደሆነ የሚናገረው ወጣት ጆን በኢሬቻ በዓል አገልግሎት ላይ የሚውሉ ማንኛቸውም ነገሮች ባህልና እሴቱን ጠብቀው እንዲከበሩ በወጣቶች የሚዜሙ የባህል ጨዋታዎች ሳይቀር ተሰንደው ዝግጅት ተደርጎ የባህል ቡድን ተቋቁሞ እየተሰራ እንደሆነ ገልጿል።

ከተለያዩ ሀገራት ማለትም ከኬንያ፣ ከታንዛኒያ፣ ከሶማሊያ ከአውሮፓ ጭምር የበዓሉ ታዳሚ ለመሆን የሚመጡ እንግዶች የበዓሉን ምንነትና ታሪክና እሴት እንዲያውቁ የማስተዋወቅ ሥራ ለመሥራት ወጣቶች የኢሬቻ አምባሳደር ሆነው ኃላፊነት ለመወጣት ተዘጋጅተዋል ያለው ጆን፤ በተሳታፊዎች የሚያዙ ጽሑፎች ኢሬቻን ብቻ የሚገልፁ እንዲሆኑ፣ የሚያዝ ባንዲራ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት እውቅና ያለው ባንዲራና የአበገዳ ባንዲራ እንዲሆን በዚህ አግባብ ወጣቶች ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ዝግጁ እንደሆኑ ተናግሯል።

በሸገር ከተማ አስተዳደር ስር የሚከበሩ ሁለት የኢሬቻ በዓላት እንዳሉ የሚናገረው ወጣት ጆን እነዚህም በሰበታና ቡራዩ የሚከበሩ እንደሆኑ ተናግሯል፡፡ ይህ ማለት በአዲስ አበባና ቢሾፍቱ ከሚከበሩ በዓላት ጋር አንድ ላይ ትልቅ ኩነት ሆነው የሚያልፉ እንደሆኑና እነዚህ ሁሉ በሰላም ተከብረው እንዲያልፉ በየደረጃው ያለው ወጣት በየአካባቢው ተደራጅቶ ተወያይቶ የበዓሉን ዕለት እየጠበቀ እንደሆነ ገልጿል።

ኢሬቻ የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ባህል እየሆነ መጥቷል የሚለው ወጣቱ፤ የዓለም ጥቁር ሕዝብ የራሱ የሆኑ እሴቶች ሃይማኖቶች፣ መተዳደሪያ ሕጎች እንዳሉትና ኢሬቻ ከዚህ አንፃር ትርጉሙ ከፍ ያለ መሆኑን ያስረዳል። ‹‹ማንኛውም ሰው ኢሬቻ ለማክበር ከመሄዱ በፊት ለአምላኩ ምስጋና ከመቅረቡ በፊት ሰው ሁሉ መታረቅ አለበት›› ይላል፡፡ እርስ በእርሱ ሰላም አውርዶ ሆዱ ንፁህ ሆኖ ከቂምና በቀል ወጥቶ ነው ኢሬቻን ማክበር የሚችለው የሚለው ወጣት ጆን፤ ይህ እንደ ሀገር ሰላምን ለማውረድ ዕርቅን ለማስተማር ትልቅ ዋጋ ያለው በዓል ነው ይላል።

ጆን እንደሚያብራራው ይህንን በዓል ደግሞ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች አውቀው የእርሳቸው አድርገው ተቀብለው ማክበር አለባቸው፡፡ በዓሉ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የባህልና የሳይንስ ተቋም(UNESCO) ተመዝግቦ ዓለም አቀፍ ጥበቃ ማግኘት እንዲችል መሥራት እንዳለባቸው ተነግሯል።

ከዚህ ውጭ የኢሬቻን ትላልቅ ዕሴቶች ለዓለም ማስተዋወቅ እንዳለ ሆኖ በበዓሉ ላይ የተደረጉ የስም መጥፋት ሥራዎች ትክክለኛውን የኢሬቻ ምንነት በማጉላት ማስተካከል ያስፈልጋል የሚለው ወጣት ጆን በዓሉ ያለው አንድምታ መልካም ብቻ እንደሆነ ሁሉም ግንዛቤ እንዲኖረው መሥራት እንደሚያስፈልግ ይናገራል።

በሚሊዮን የሚቆጠር ሰው በዓሉን ለማክበር ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ ባዶ እጁን ሳይሆን በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ይዞ ነው የሚመጣው የሚለው ወጣት ጆን ይህንን ገንዘብ አዲስ አበባ ላይ ለግብይት የሚያውለው ስለሆነ ሁሉም ከኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ተጠቃሚ ለመሆን መጣር እንደሚገባው ያስረዳል። ይህ ደግሞ ለከተማዋ ተጨማሪ የኢኮኖሚ አቅም እንደሚፈጥር ይናገራል፡፡

ስለዚህ የአዲስ አበባ ሕዝብ ኢሬቻን ብቻ ሳይሆን ሌሎች በዓላትም በከተማዋ እንዲከበሩ ተባባሪ መሆን እንዳለበትም ይናገራል፡፡ በተለያዩ የዓለም ሀገራት በሚደረጉ ፌስቲቫሎች የሚገኘው ገቢ ትልቅ መሆኑንና ኢሬቻም በዚህ ረገድ ትልቅ ፋይዳ ስላለው የአዲስ አበባ ሕዝብ የበዓሉን ታዳሚ በፍቅር በማስተናገድ ከኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ባለፈ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩን ከፍ በሚያደርግ መልኩ በዓሉን ለማክበር መዘጋጀት እንዳለበት ተናግሯል።

ኢሬቻ ሁሉን አቀፍነቱን፣ ዲሞክራሲያዊናቱን፣ አብሮ መኖርን እና ይቅርታን ያቀፈ በዓል ነው የሚለው ወጣት ጆን እነዚህን እሴቶች ይበልጥ በማስተዋወቅ ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ የእራሱ በዓል መሆኑን አውቆ ተሳታፊ እንዲሆን እና በሁሉም ረገድ በተለይ ወጣቶች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው ወጣት ጆን መልዕክቱን አስተላልፏል።

ወጣት ከድር እንዳልካቸው የኦሮሚያ ወጣቶች ማህበር ፕሬዚዳንትና የኦሮሚያ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ነው። እርሱ እንደሚናገረው ኢሬቻ በኦሮሞ ማኅበረሰብ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው በዓል ሲሆን የሰላም ምልክት ተደርጎም ይወሰዳል ይላል። ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ ሰማይና ምድርን ለፈጣሪው ምስጋና የሚያደርስበት በዓል ነው። ከዘመን ወደ ዘመን ላሸጋገረው አምላክ ምስጋና ያቀርባል፤ የሚመጣውን ዘመንም አምላክ የብራ አድርግልን ብሎ ፀሎቱን ለፈጣሪ ያቀርባል ይላል።

ወጣት ከድር እንደሚናገረው፤ በዚህ በዓል የወጣቶች ኃላፊነት ትልቅ ነው፡፡ በዓሉ የሕዝብ ሆኖ ሳለ ከዚህ ባፈነገጠ መልኩ ችግርና ሁከት ለመፍጠር የተዘጋጁ አካላት ስለሚኖሩ ይህንን አውቀው አካባቢያቸውን በንቃት መጠበቅ እንዳለባቸው እንደ ኦሮሚያ ከአራት ሚሊየን በላይ ወጣቶችን በዚህ ጉዳይ ላይ በማወያየት በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እንደተሰሩ ተናግሯል።

ከአዲስ አበባ አንድ ሺህ ወጣት፣ ከሸገር ከተማ አንድ ሺህ ወጣት በመመልመል ውይይት መደረጉንና በአዲስ አበባ ደረጃ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል ከፀጥታ ስጋት ነፃ ሆኖ እንዲከበር ዝግጅት መደረጉን ጠቁሟል፡፡ በቢሾፍቱም እንዲሁ ወጣቶች ተደራጅተው አካባቢያቸውን እንዲጠብቁ በማድረግ ክብረ በዓሉ ሰላማዊ ሆኖ እንዲከበር ዝግጅት ተደርጎ መጠናቀቁን ተግሯል።

በአዲስ አበባ ዙሪያ በሸገር ከተማ አስተዳደር ከ50 ሺህ በላይ ወጣቶች “በፎሌ” በመደራጀት ስለምን ለማስጠበቅ ሥራዎች እንደተሰሩ የሚናገረው ከድር፤ ከየአካባቢው ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ ወጣቶች ደግሞ በዓሉ በሰላማዊ መልኩ እንዲከበር የየድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው የጋራ መግባባት መፈጠሩንም ጠቁሟል፡፡ በዓሉ የኦሮሞ ሕዝብ የምስጋና በዓል እንጂ የየትኛውም ቡድን የፖለቲካ ትርፍ ማግኛ መድረክ እንዳልሆነ ተገንዝቦ ሁሉም የበዓሉ ታዳሚ ወጣት የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ ተደርጓል ብሏል።

ኢሬቻ በአዲስ አበባ ብቻ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ተገኝተው የሚያከብሩት በዓል ነው የሚለው ወጣት ከድር፤ ይህ ትልቅ ፌስቲቫል በምንም ሁኔታ በሚፈጠሩ አሉታዊ ነገሮች መጠልሸት እንደሌለበትና ለከተማዋ ተጨማሪ ጥቅምና ውበት ሆኖ ተከብሮ እንዲያልፍ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ይላል። በሌላ በኩል ደግሞ በበዓሉ ሰርጎ በመግባት ሁከትና ግርግር በመፍጠር በዓሉን ለማደፍረስ የሚንቀሳቀስ አካል ካለ ደግሞ በንቃት በመጠበቅ ለኢሬቻ በዓል ድምቀት የሚጠበቅበትን ለመወጣት ሁሉም ዝግጁ መሆን እንደሚጠበቅበት አስረድቷል፡፡

በዓሉ የሚከበረው አባ ገዳዎች ባስቀመጡት አቅጣጫ መሠረት ነው የሚለው ወጣት ከድር ይህ ማለት በዓሉ ላይ ይዞ መገኘት የተፈቀደውንና የተከለከለውን ነገር በደንብ በመገንዘብ አባ ገዳዎችን ትዕዛዝ ማክበር እንደሚያስፈልግ ተናግሯል፡፡ ወደ በዓሉ ማንኛውም ሰው ሲመጣ ኢሬቻን ለማክበር እንጂ ሌላ ዓላማ ይዞ መምጣት የለበትም ብሏል።

የኦሮሞ ባህል መከባበርን አንድነትን ፍትህን ነው የሚያስተምረው የሚለው ወጣት ከድር፤ በበዓሉ የሚገኙ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውን በሚያጠናክር መልኩ በአንድነት ማክበር ይጠበቅባቸዋል። ኢሬቻ ሰላም ዕርቅና ፍቅርን የሚሰብክ ነው፡፡ ይህንኑ እሴቱን በጠበቀ መልኩ ለማክበር መዘጋጀት ተገቢ እንደሆነ ገልጿል።

ወጣቶቹ ባስተላለፉት መልዕክት የኦሮሞ ሕዝብ ቱባ ባህል ከሚገለጽባቸው ሁነቶች አንዱ የሆነው የኢሬቻ በዓል ዓለም አቀፍ ተቀባይነቱን ከፍ ማድረግ በሚቻልበት መልኩ እንዲከበር ወጣቶች ኃላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የአዲስ አበባ ሕዝብ የተለመደ እንግዳ ተቀባይነቱን በማሳየት በዓሉን በደመቀ መልኩ ለማክበር መዘጋጀት እንደሚገባ ወጣቶቹ ተናግረዋል፡፡

ክብረአብ በላቸው

አዲስ ዘመን  መስከረም 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You