
አዲስ አበባ፦ ሃይማኖታዊ በዓላትን ስናከብር የኢትዮጵያን ታሪክ በሚመጥን መልኩ መሆን እንዳለበት የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር አደም ካሚል ገለጹ።
የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አደም ካሚል የመውሊድ በዓልን አስመልክተው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊ እውቅና በጥንታዊ ስልጣኔ፣ በባህላዊ ቅርስ እና በስፖርት የበላይነት ላይ የተመሰረተ ነው። ይህች የምስራቅ አፍሪካ ሀገር ዓለምን በመማረክ በርካታ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ዓለም አቀፋዊ አድናቆት አትርፋለች።
ሃይማኖታዊ በዓላትም የኢትዮጵያ ድምቀቶች፣ የቱሪስት መስህቦች እና የሀገር ገጽታዎች ናቸው ያሉት ፕሮፌሰር አደም፤ በዓላቱን ስናከብር የኢትዮጵያን ታሪክ በሚመጥን መልኩ ሊሆን እንደሚገባና የበዓሉን ታሪክ ማወቅ እንደሚያስፈልግ ሁሉም ዜጋ ሊያውቅ ይገባል ብለዋል።
እንደ ፕሮፌሰር አደም ገለፃ፤ በሺህዎች የሚቆጠሩ ዓመታትን ያስቆጠረ ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ በሰው ልጅ ህልውና ውስጥ ካሉት ጥንታዊ ስፍራዎች አንዷ ምስክር ናት። ኢትዮጵያ ከባህላዊ እና ስፖርታዊ እንቅስቃሴዋ ባሻገር የአፍሪካ ኅብረት እና የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ዩኔሲኤ) ዋና መስሪያ ቤት በመሆን ፖለቲካዊ ጠቀሜታ አላት።
ሀገሪቱ በአህጉራዊ ዲፕሎማሲ እና በሰላም ማስከበር ሥራዎች በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ሚና ከፍተኛ ነው። ይህን በመረዳት ሃይማኖታዊ በዓላትን ይበልጥ ለዓለም ለማስተዋወቀ አንድነትን፣ ፍቅርን እና ሀገራዊ ሰላምን ማስጠበቅ ያስፈልጋል ብለዋል።
የነብዩ መሐመድ አስተምህሮቶች የሚያተኩሩት ልዩነትን አክብሮ በመቻቻል አብሮ በመኖር፤ በእኩልነት፤ ሌላውን ሰው እንደራስ አድርጎ በመውደድ፤ ለሰው ልጅ ፍቅርን በማሳየት፤ ተፈጥሮን በመንከባከብ እና ሥራ ወዳድነት የመሳሰሉት ላይ በመሆኑ ለሀገራችን አንድነትና መተሳሰብ እጅግ ጠቃሚ እንደሆኑም ገልጸዋል።
ባህልና ሃይማኖታዊ እሴቶቻችን በሁሉም ሃይማኖቶች ውስጥ ይንጸባረቃሉ ያሉት ፕሮፌሰር አደም፤ የአንዱ እሴት ለሌላው ክብርና መድመቂያው ነው። የእስልምና እምነት አሻራ የሆኑትን እንደ አልነጃሺ እና የሀረር ጀጎል መስጊድ ያሉትን መጠበቅና መንከባከብ ይጠበቅብናል ብለዋል።
በዓሉ ለሰው ልጆች ሁሉ መልካም ነገሮች የሚደረጉበት፤ አቅመ ደካሞች የሚረዱበት በልዩ ልዩ ምክንያት ወገኖቻቸውን አጥተው በሀዘን ላይ የሚገኙትን የማፅናናት ሥራ የሚሰራበት፤ የታመሙት የሚጎበኙበት፤ ዘመድ ጎረቤት የሚገናኙበት፤ ፍቅር እና አክብሮት የሚገለጽበት፤ በአጠቃላይ ሰዎች በጎ ተግባራትን የሚያከናውኑበት በመሆኑ ይህንኑ ማድረግ ይገባልም ብለዋል።
መልካም እሴቶቻችንን ለቀጣይ ትውልዶች ማስተማር እና ማስተላለፍ አለብን ያሉት ፕሮፌሰር አደም፤ መንፈሳዊም ሆኑ ቁሳዊ እሴቶቻችን ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ ተባብረን መስራት ይኖርብናል ብለዋል፤ መውሊድን እና መሰል በዓላትን ስናከብር ሃይማኖት መሰረቱ ሰላም በመሆኑ ስለፍቅርና አንድነት በመስበክ ማኅበራዊ ኃላፊነትን መወጣት እንደሚገባም አሳስበዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን መስከረም 15 ቀን 2016 ዓ.ም