መስፍን ኩሳ እና አዲስ ግዛው ጓደኛሞች ናቸው። ሁለቱም ኑሯቸው ጎዳና ላይ መሆኑ፤ አብረው መራባቸው እና አንድ ላይ መብላት መጠጣታቸው ይበልጥ አቀራርቧቸዋል። ሐምሌ 9 ቀን 2012 ዓ.ም እሁድ መሆኑን ተከትሎ፤ ሁለቱም መዝናናት ፈልገዋል። ማደሪያቸው አዲስ አበባ ከመስቀል አደባባይ በስተግራ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን አቅራቢያ መኪና ማጠቢያው አካባቢ ሲሆን፤ በዕለቱ ብዙም ሳይርቁ ጠጅ መጠጣት ፈለጉ።
በግምት ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ሲሆን፤ ከፍላሚንጎ ጀርባ ወዳለው ጤናዳም ጠጅ ቤት ገብተው ሁለት ሁለት ብርሌ ጠጅ ጠጡ። የጠጡበትን ሂሳብ መስፍን ከፍሎ ወደ ማደሪያቸው ሲሔዱ፤ ከእስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት የአውቶቡስ ፌርማታው ወንበር ላይ በስምም ሆነ በመልክ የማያውቁት መካከለኛ ቁመት ያለው ሰው ተቀምጦ አገኙ። ሰውየው ለአዲስ ግዛው ሰላምታ ሰጠ። አዲስ ግዛው ግን ለቀረበለት ሰላምታ ምላሽ አልሰጠም። በሌላ በኩል መስፍን ኩሳ ለአዲሱ ሰው ሰላምታ አቀረበ፤ አዲሱ ሰው ግን መስፍንን ለማነጋገር አልፈለገም። ትተውት ‹‹ወደ ማደሪያችን እንሂድ›› ተባብለው ከአካባቢው ዘወር አሉ።
ሌላኛው የጎዳና ላይ ነዋሪ ዳንኤል ኃይሉ
ዳንኤል ኃይሉ በ1990 ዓ.ም ከአቶ ኃይሉ ተፈራ እና ከወይዘሮ ብርቱካን ወልደኪዳን በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን አቦምሳ ቀበሌ ውስጥ ተወለደ። በአቦምሳ ትምህርት ቤት ከ1996 እስከ 2004 ዓ.ም 8ኛ ክፍል እስከሚደርስ ትምህርቱን ተከታትሏል። አባቱ ሕይወታቸው ማለፉን ተከትሎ ትምህርት ያቋረጠ ሲሆን፤ ራሱን ለመቻል ወደ ንግድ ሥራ ገብቶ ነበር። ነገር ግን ሊሳካለት አልቻለም። በ2007 ዓ.ም ሕይወትን በተሻለ መልኩ ለመምራት ያመቻል ብሎ ወዳመነባት ወደ አዲስ አበባ ከተማ ለመግባት ወሰነ። አስቦም አላበቃ ተሳፍሮ አዲስ አበባ ገባ።
አዲስ አበባ ከተማ ላይ መኖር እንደገመተው ቀላል አልነበረም። ማደሪያ ማግኘት እና የሚቀምሰውን ጎርሶ ማደር አዳጋች ሆነ። ውሎ እና አዳሩን ጎዳና ላይ አደረገ። በጎዳና ሕይወቱ ከሌሎች የጎዳና ነዋሪዎች ጋር መጋጨት የተለመደ ነው። እሁድ ሃምሌ 9 ቀን 2012 ዓ.ም ብርድ ብርድ ሲለው ከወንድማማቾች ጠጅ ቤት ጠጅ ገዝቶ፤ እስጢፋኖስ በር ላይ ያለው የአውቶቡስ ፌርማታ ስር ተቀምጦ ሲጠጣ መስፍን ኩሳ እና አዲስ ግዛው ወደ እርሱ ተጠጉ። እርሱም ለጊዜው በአይኑ ገርምመውት እርሱም አተኩሮ አይቷቸው አለፉት።
ምሽት አምስት ሰዓት
መስፍን ከጓደኛው ጋር ጠጅ ጠጥተው ወደ ማደሪያቸው ሲገቡ ራበው። አጠገባቸው ሸራ ወጥሮ ወደሚተኛው ጓደኛቸው ምግብ ሲጠይቅ፤ አያሌው ደምሴ በቅፅል ስሙ ራስታው የተሰኘው ሌላኛው የጎዳና ላይ ነዋሪ ጎረቤታቸው የሚበላ አምጥቶ ለእነርሱም በጥቁር ፌስታል እንዳስቀመጠላቸው ነገራቸው። ሁለቱም ‹‹መኝታችንን አመቻችተንና አልጋ አነጣጥፈን፤ እንበላለን።›› ተባብለው የተቀመጠላቸውን ምግብ በጥቁር ፌስታል በራቸው ላይ አስቀምጠው ሁለቱም በሸራ ወደ ተወጠረው ማደሪያቸው ገቡ። መስፍን አልጋውን አስተካክሎ ጨርሶ ሲወጣ፤ ጓደኛውን አላገኘውም። የጓደኛውን ስም ቢጠራም ምላሽ የሚሰጠው አጣ። ርቦታል ለመብላት እየተቻኮለ ጓደኛውን ፍለጋ ሲዟዟር ወደ ቤተክርስቲያኑ ተመለከተ። ጓደኛው አዲስ አውቶቢስ ፌርማታው ጋር ሔዶ ቀድሞ ካገኙት ሰው ጋር እየታገለ መሆኑን ተመለከተ።
ዳንኤል በዛች ሰዓት
ዳንኤል ብርድ ተጫጭኖታልና በሃይላንድ የያዘውን ጠጅ እየተጎነጨ ብቻውን ሲተክዝ፤ በአይን የሚያውቀው እና ስሙን በውል የማያውቀው ከጓደኛው ጋር በዓይኑ ገርምሞት ያለፈው አዲስ ግዛው ከመኪናው ማጠቢያ በኩል ወደ እርሱ ሲጠጋ ተመለከተ። አዲስ እየቀረበው ሲመጣ ረዥም የእንጨት እጄታ ያለው ቢላዋ ይዞ ነበር። ዳንኤል አጠገብ መጥቶ ሲቀመጥ፤ ዳንኤል ሁኔታው ስላላማረው ተነስቶ ወደ ማደሪያው ወደ ድልድዩ ሲያመራ አዲስ ከኋላው ቢላዋውን ሰነዘረበት። ዳንኤል የተሰነዘረው ቢላዋ ሰውነቱ ጋር ከመድረሱ በፊት በመጠራጠሩ ዞሮ መታገል ጀመሩ። ዳንኤል ቢላዋውን መቀማት ቻለ። ዳንኤል ራሱን ለመከላከል ቢላዋውን ነጥቆ በድንጋጤ አዲስን ደረቱ ላይ ወጋው።
አዲስ አንዴ ደረቱ አካባቢ በመውጋቱ ወዲያው መሬት ላይ ሲወድቅ የተመለከተ ጓደኛው መስፍን፤ ተንደርድሮ ተጠግቶ ዳንኤልን በቡጢ ለመምታት ሰነዘረ። ሆኖም ዳንኤል በመስፍንም የሚመታ ዓይነት አልሆነም፤ የተሰነዘረበት ቡጢ ፊቱ ላይ እንዳያልፍ ተከላክሎ በድንጋጤ በድጋሚ አዲስን በወጋበት ቢላዋ መስፍንን ወጋበት። ዳንኤል ሁለቱም ላይ ጉዳት ካደረሰ በኋላ ደማቸው እየፈሰሰ ሲያይ፤ ሌሎች ሰዎች መጥተው እንዳያጠቁት በመስጋት ቢላዋውን እዛው ጥሎ ከማደሪያው በተቃራኒ አቅጣጫ ወደ ማስቀል አደባባይ ሮጠ።
የድረሱልኝ ጥሪ
መስፍን በበኩሉ የድረሱልኝ ጥሪውን በጩኸት ቢያስተጋባም፤ የመጣለት አልነበረም። ጓደኛው በጣም ተወግቶ ስለወደቀ እርሱን የሚያድነውን ለማፈላለግ ደሙን እያፈሰሰ ምግብ ወደ ሰጣቸው ጓደኛቸው ወደ አያሌው ደምሴ (ራስታው) ሔደ። እንቅልፍ ላይ የነበረው ራስታውን ቀሰቀሰው። ነገር ግን ራስታው እግሩን ታሞ ስለነበር፤ አዲስን ሃኪም ቤት መውሰድ አልችልም አለ። ሌላ ሰው ማግኘት ባለመቻላቸው፤ መስፍን ጓደኛው አዲስ እንዳይሞት በመስጋቱ ‹‹እንደምንም አሸክመኝ፤ እኔ እሸከመዋለሁ›› ብሎ መስፍን ጓደኛውን አዲስን ተሸክሞ ወደ ሃኪም ቤት ለመውሰድ ጥረት አደረገ።
ነገር ግን መስፍንም በመወጋቱ ጓደኛውን ተሸክሞ መጓዝ አልቻለም። ሲያቅተው አዲስን አስፓልት ላይ አስተኝቶ መጮህ ጀመረ። መስፍን እና ራስታው ጓደኛቸውን አዲስን አስፓልት ላይ አድርገው ቆመው ግራ ተጋብተው ሲያማትሩ በፓትሮል የሚዞሩ ፖሊሶች አገኙዋቸው። ሁለቱንም ወደ መሿለኪያ ጤና ጣቢያ ወሰዷቸው። በግምት ከምሽቱ 5 ሰዓት ከ30 ላይ በስለት የተወጋው አዲስ ስድስት ሰዓት ለመሆን አስር ደቂቃ ሲቀረው ህይወቱ አለፈ። ገዳይ ዳንኤል ኃይሉ አልተገኘም።
የመስፍን ኩሳ የምስክርነት ቃል
ከአቶ ኩሳ ሳዴቦ እና ከታሪኬ ወርቅነሽ በ1990 ሐዋሳ ከተማ 03 ቀበሌ የተወለደው መስፍን ኩሳ፤ በሐዋሳ ቤተልሔም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሯል። የእናቱን ሞት ተከትሎ ትምህርት ያቋረጠው መስፍን፤ እስከ 2011 ዓ.ም እዛው ሐዋሳ ከተማ ላይ የጎዳና ሕይወትን ሲገፋ ቆይቷል። በ2012 ዓ.ም መስከረም ወር ላይ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በጎዳና ላይ መኖር የጀመረው ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ባንቢስ አካባቢ ነበር። ባንቢስ አካባቢ ብዙም ስላልተመቸው በዛው ክፍለ ከተማ እስጢፋኖስ አካባቢ ሸራ ወጥሮ መኖር ጀመረ።
አዲስ አበባ መጥቶ አንዳንዴ ሥራ ሲያገኝ የቀን ሠራተኛ ሆኖ ሕይወቱን ሲገፋ፤ አዲስ የሚባል ጓደኛ አገኘ። ሁለቱም ጓደኛሞች አብረው በጎዳና ላይ ሕይወታቸውን ሲገፉ፤ ልብስ ተቀያይረው እየለበሱ፤ አብረው እየጠጡ እና አብረው እየበሉ ነበር። በተለይ መስፍን እንደሚለው አንዳንዴ ብርድ ለመከላከል ጠጅ ይጠጣሉ። እሁድ ሐምሌ 9 ቀን 2012 ዓ.ም እንደለመዱት ጠጅ ጠጥተው ወደ ማደሪያቸው ተመለሱ።
በግምት ከምሽቱ 5 ሰዓት ተኩል አካባቢ፤ መስፍን ከጓደኛው አዲስ ጋር ምግብ ለመብላት ሲጠራው አላገኘውም። እርሱ መኪና ማጠቢያው አካባቢ ሆኖ ወደ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ሲመለከት፤ ጓደኛው አዲስ ከማያውቀው ሰው ጋር ሲታገል አየ። ይህን የተመለከተው መስፍን እየሮጠ ወደ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን አቅጣጫ ሲሔድ፤ በግምት 10 ሜትር ሲቀረው በመስፍን ያልታወቀው ሰው (ዳንኤል ሃይሉ ) አዲስን በግራ በኩል ደረቱን ወጋው።
አዲስ ወደቀ፤ መስፍን ጓደኛውን ለመርዳት ዳንኤል ሃይሉ ጋር እንደደረሰ እጁን ጨብጦ ቡጢ ሰነዘረ፤ ዳንኤል በመስፍንም የሚመታ ዓይነት አልነበረም። የተሰነዘረበትን ቡጢ አምልጦ በቀኝ እጁ የመስፍንን ግራ ጎን ቀበቶ ማሰሪያው አካባቢ ወግቶት ወደ መስቀል አደባባይ ሮጠ። መስፍን ከራስታው ጋር ተባብሮ አዲስን ለማሳከም ጥረት ቢያደርግም የአዲስ ሕይወት አለፈ።
መስፍን በምስክርነት ቃሉ ላይ እንዳብራራው፤ አዲስ መሞቱን ተከትሎ ለምርመራ ሆስፒታል ሲሔድ፤ መስፍን ኩሳ ደግሞ የህክምና እርዳታ ተደርጎለት ተሻለው። ነገር ግን በመጨረሻም መስፍን ጓደኛህ አዲስን ከተኛበት አስነስተህ ራት እንብላ በሚል ሰበብ ከማደሪያው አርቀህ በጋራ በምትጠቀሙበት ቢላዋ ገድለሀዋል በሚል በሰው መግደል ወንጀል ተከስሶ እስር ቤት ገባ።
የዳንኤል ኃይሉ የዕምነት ክህደት ቃል
ዳንኤል አዲስን እና መስፍንን ከወጋ በኋላ ከአካባቢው ተሠወረ። ዳንኤል እንደተናገረው፤ ድርጊቱን የፈፀመው ራሱን ለመከላከል ሲል ነው። ራሱን በመከላከል ሒደት ውስጥ የፈፀመው ድርጊትም ሕይወት እስከማጥፋት ይደርሳል ብሎ አልገመተም። ወደ አካባቢው ሲመለስ ግን የሰማው ዜና አስደንጋጭ ሆነበት። እርሱ በቢላዋ የወጋው አዲስ የመሞቱን ዜና ሲሰማ ያለማንም አስገዳጅ ህዳር 6 ቀን 2013 ዓ.ም በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ በመሔድ እጁን ሰጥቷል።
ዳንኤል የዕምነት ክህደት ቃሉን ሲሰጥ ከአዲስም ሆነ ከመስፍን ጋር የሚያጋጨው ምንም ምክንያት አልነበረውም። አዲስን በዓይን ከማወቅ ውጪ መስፍንን እንደውም አይቶት አያውቅም፤ በአጋጣሚ ያለምንም ምክንያት አዲስ ሽንኩርት መክተፊያ ቢላዋ ይዞ ሊወጋው በመሞከሩ ራሱን ለመከላከል ባደረገው ጥረት ሁለቱም ላይ ጉዳት አድርሷል። ይህንንም አምኖ ለፖሊስ ቃሉን ሰጥቷል።
የፖሊስ ምርመራ
በቅድሚያ አዲስ ህይወቱ ማለፉን ተከትሎ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪና የፎቶግራ ባለሞያ በአምቡላንስ መኪና ቦታው ላይ በመድረስ አስክሬኑን ባለበት ሁኔታ ፎቶ አነሱ። በመቀጠል አስክሬኑ ለምርመራ ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ የተወሰደ ሲሆን፤ መስፍንም የሕክምና ዕርዳታ ተደረገለት።
ምንም እንኳ የመጀመሪያው ተጠርጣሪ መስፍን ኩሳ ቢሆንም፤ ተከሳሽ ዳንኤል ሃይሉ ሕዳር 6 ቀን 2013 ዓ.ም በገዛ ፍቃዱ እጁን በመስጠቱ እና ወንጀሉን መፈፀሙን በማመኑ እስር ቤት ገባ። ፖሊስም ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የተፃፈ የአስክሬን የምርመራ ውጤት፤ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ራስ ደስታ ሆስፒታል ጤና ቢሮ የተፃፈ የአቶ መስፍን ኩሳ የህክምና ማስረጃ፤ የሟች አስክሬን እና ወንጀሉ የተፈፀመበትን ቦታ ለማሳየት የተነሳ ፎቶ ፤ ሶስት የሰው ምስክር አያይዞ በዕለቱ ማለትም በሐምሌ 9 ቀን 2012 በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት ወንጀል መፈፀሙን የሚያሳይ ማስረጃ በማደራጀት ፖሊስ ለአቃቤ ህግ አቀረበ።
አቃቤ ህግም የ29 ዓመቱ ዳንኤል በሐምሌ 9 ቀን 2012 ዓ.ም እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ተብሎ በሚጠራው አካባቢ፤ ሟች አዲስ ግዛውን በቢላዋ ደረቱ ላይ ወግቶታል። አቶ አዲስ በደረሰበት ጉዳት ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። ዳንኤል ከዚህ ተራ የግድይ ወንጀል በተጨማሪ፣ በአቶ መስፍን ኩሳ ላይም በተመሳሳይ መልኩ በቢላዋ ታፋውን ወግቶ ደሙን በማፍሰሱ እና በማቁሰሉ በቀላል የአካል ጉዳት የማድረስ ወንጀል ሊጠየቅ ይገባል ሲል አቃቢ ህግ ክስ መስርቶበታል።
ውሳኔ
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድቤት በጥር 26 ቀን 2014 ዓ.ም በዋለው ችሎት ክስ እና ማስረጃውን ከሕግ ጋር አገናዝቦ በሰጠው ውሳኔ፤ ዳንኤል ኃይሉ በፈፀመው የሰው መግደል ወንጀል የ14 ዓመት ፅኑ እስራት ይገባዋል ሲል ፈርዶበታል።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን መስከረም 12 ቀን 2016 ዓ.ም