ቡናን ማስተዋወቅንና አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን ማስፋትን ያለመው ጉባኤና ኤግዚቢሽን

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው የግብርና ምርቶች መካከል ቡና አንዱ ነው፡፡ በርካታ የቡና ቤተሰቦችን ያቀፈ ሲሆን፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳዎቹም ከፍተኛ ናቸው፡፡

ቡና በአገሪቱ ያለውን የላቀ ኢኮኖሚያዊ ድርሻ ማሳደግ እንዲቻል በልማቱም በግብይቱም በኩል የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎች በቡናና ሻይ ባለስልጣን በኩል ተሰርተዋል፡፡ የባለስልጣኑ መረጃ እንደሚያመላክተውም፤ በሪፎርም ሥራውም ሀገርን፣ የአርሶ አደሩን እና ሌሎች በቡና ዘርፍ የተሰማሩ ተዋንያንን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተደረገው ጥረት ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏል፡፡

ባለፉት ዓመታት በቡና ግብይት በኩል ከተመዘገቡ ውጤቶች መካከል ወደ ውጪ ከተላከ ቡና የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ እየጨመረ የመጣበት ሁኔታ ይጠቀሳል። እስከ 2014 በጀት ዓመት ድረስ በመቶ ሚለዮኖች ዶላር ይገኝበት ነበር፤ ይህም በወቅቱ ከፍተኛ መሆኑ ይገለጻል፡፡

ይህ ገቢ በ2014 በጀት ዓመት አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ደርሷል፡፡ ይህም ስኬት በቡና የወጪ ንግድ ታሪክ የመጀመሪያው የተባለው መሆንም ችሏል፡፡ በ2015 በጀት ዓመት ከዚህ በላይ ገቢ ለማግኘት ቢታቀድም፣ በዓለም ገበያ የቡና ዋጋ መውደቅ ጋር በተያዘ እቅዱን ማሳካት ባይቻልም አንድ ነጥብ 33 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ማግኘት ተችሏል፡፡

ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ቡና ግብይት እጅግ በጣም የተንዛዛና ምንም እሴት የማይጨምሩ ተዋንያኖች የበዙበት የግብይት ሥርዓት የነበረ ሲሆን፣ ባለፉት ዓመታት የተካሄደውን ሪፎርም ተከትሎ ይህንን የግብይት ሥርዓት ማሳጠር ተችሏል፡፡ ምርቱንም በቀጥታ ከአርሶ አደር ወደ አቅራቢ፤ ከአቅራቢ ደግሞ ወደ ላኪ ማድረስ የተቻለበት ስርዓት ተዘርግቷል፡፡ አርሶ አደሮች በቀጥታ ቡና ለውጭ ገበያ የሚልኩበት ስርዓትም ተፈጥሯል፡፡ እነዚህን ሁሉ ተግባራት ተከትሎ ወደ ውጪ የሚላከው የቡና መጠንና የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ጨምሯል፡፡ ሀገሪቱ ወደ ውጭ ከሚላክ ቡና በ2016 በጀት ዓመትም አንድ ነጥብ 75 ቢሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት አቅዳለች፡፡

በቀጣይም ይህን ተጠቃሚነት ይበልጥ ማረጋገጥ ይገባል፡፡ ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግና ቡናን በከፍተኛ ጥራት ከማዘጋጀት በተጨማሪ አንዳንዴ በውጭ ገበያው ላይ የሚታየውን ተግዳሮት አሸንፎ ለመውጣት የኢትዮጵያን ቡና ለዓለም ገበያ በማስተዋወቅ ሰፊ ገበያ ማግኘት የሚያስችል ሥራ በስፋት መሥራትም ይኖርበታል፡፡

ለዚህም በመጪው የካቲት በአዲስ አበባ ከተማ የሚካሄደው 20ኛው የአፍሪካ ባለ ልዩ ጣዕም የቡናዎች እና የኢንተር አፍሪካን ኮፊ ኦርጋናይዜሽን (IACO) ጉባኤና ኤግዚቢሽንን ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑ በቅርቡ በተሰጠ መግለጫ ላይ ተመልክቷል፡፡ ‹‹የአፍሪካ የቡና ሳምንት›› በሚል መሪ ሃሳብ ለተከታታይ አምስት ቀናት የሚካሄደው ይህ ጉባኤና ኤግዚቢሽን የኢትዮጵያን ቡና በአፍሪካ እና በዓለም ገበያ ይበልጥ ለማስተዋወቅ ከፍተኛ እድል እንደሚፈጥር ታምኖበታል፡፡

የኢትዮጵያ ቡና ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ግዛት ወርቁ፤ የዓለም የቡና ዋጋ እየወረደ በመጣበት በዚህ ጊዜ ጉባኤና ኢግዚቢሽኑ በኢትዮጵያ መካሄዱ ትልቅ ዕድል እንደሚመጣ ይናገራሉ፡፡ አሁን ላይ የቡና ምርትና ምርታማነት ያደገ ቢሆንም ዓለም አቀፍ የቡና ዋጋ የወረደበት ጊዜ ነው ያሉት አቶ ግዛት፣ ኤግዚቢሽንና ባዛሩ መዘጋጀቱ ወቅታዊና እጅግ ጠቃሚ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡ ለኢትዮጵያ ቡና በርካታ የገበያ ዕድሎችን ይዞ እንደሚመጣም አመላክተዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የቡና መገኛ እንደመሆኗ ሰፊ የሆነ የማስተዋወቅ ሥራን መሥራት ይገባል፡፡ ይህ ወቅት ደግሞ የኢትዮጵያን ቡና በስፋት የማስተዋወቅ እንዲሁም አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን ለማግኘት ጥረት የሚደረግበት ጊዜ ነው፡፡

ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ዘንድሮ የዓለም የቡና ዋጋ በከፍተኛ መጠን መውረዱን የጠቀሱት አቶ ግዛት፤ በአንጻሩ በኢትዮጵያ ቡና ከገበሬዎች የሚገዛበት እንዲሁም አቅራቢዎችና ላኪዎች የሚሻሻጡበት ዋጋ እጅግ ውድ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ግብይቱ ከዓለም ዋጋ ጋር ተናብቦ መሄድ እንዳለበትም አስገንዘበው፤ መንግሥትም እሴት የማይጨምሩ ደላሎችን ከመሀል በማስወጣት የቡና ገበያ በዓለም የገበያ ዋጋ እንዲመራ ማድረግ እንደሚጠበቅበት ነው ያስገነዘቡት፡፡

ጉባኤና ኢግዚቢሽኑ እጅግ አስፈላጊና ወሳኝ በሆነ ወቅት ላይ መምጣቱንም ዋና ስራ አስኪያጁ ጠቅሰው፣ ዘርፈ ብዙ ዕድሎች እንዳሉትም ይናገራሉ፡፡ የካቲት ወር ማለት የኢትዮጵያ ቡና የምርት ጊዜውን አጠናቅቆ ወደ ገበያ የሚወጣበት ጊዜ በመሆኑ ይህም ጥሩ አጋጣሚ እንደሆነ አንስተዋል፡፡

እሳቸው እንደገለጹት፤ በዚህ ጊዜ አዲስ አበባ ከተማ ላይ የቡና ሳምንትን ማክበር ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። ይህም የኢትዮጵያ ቡናን ለዓለም ገበያ በጥሩ ሁኔታ ከማስተዋወቅ ባለፈ ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና በጥሩ ዋጋ መሸጥ ያስችላል፡፡

ቡና እጅግ ስስና ተለዋዋጭ ገበያ ያለው መሆኑን የጠቀሱት አቶ ግዛት፤ የቡና ዋጋ በተለያየ ምክንያት ከፍና ዝቅ የሚልና በአሁኑ ወቅትም ዋጋው እየወረደ እንደመጣ ጠቁመዋል፡፡ ይሁንና አሁን የተፈጠረውን አጋጣሚ በመጠቀም የኢትዮጵያ ቡናን በሚገባ ማስተዋወቅና አዳዲስ ገዢዎችንም በማፈላለግ ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና በተሻለ ዋጋ ለመሸጥ በዚህ ወቅት ሰፊ ሥራ መሥራት ከሚመለከታቸው አካላት በሙሉ እንደሚጠበቅ አመላክተዋል፡፡

በመግለጫው ላይ እንደተጠቆመው፤ ጉባኤና ኤግዚቢሽኑ በቡናና ሻይ ባለስልጣንና በግሉ ዘርፍ ብቻ አይደለም የተዘጋጀው፤ የመላ አፍሪካ የቡና ድርጅት/ ኢንተር አፍሪካ ኮፊ ኦርጋናይዜሽን/ እንዲሁም የአፍሪካ ባለ ልዩ ጣዕም ቡናዎች ማህበርም በዝግጀቱ ተሳትፈዋል።

ኤግዚቢሽንና ጉባኤውን የመንግሥት አካላት ከግሉ ዘርፍ ጋር ማዘጋጀታቸው ለገዢዎችም ሆነ ለሻጮች ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አቶ ግዛት ይገልጻሉ፡፡ የመንግሥት አካላት ምን አይነት ህግ እንዳወጡና የግሉ ዘርፍም ህጉን መሰረት በማድረግ እንዴት እየሸጠና እንዴት እየገዛ ነው የሚለውን ጭምር ለመረዳት እንደሚያስችል ነው ያመለከቱት፡፡

ሌላው ማስታወቂያ እንደመሆኑ እያንዳንዱ አምራችና ላኪ በኤግዚቢሽኑ ተገኝቶ ገበያ የሚያገኝበትም ይሆናል፡፡ ጉባኤና ኤግዚቢሽኑ ለኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ጥሩ የማስታወቂያ ዕድል ይፈጥራል፡፡ ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ፣ ከኤዢያ፣ ከጃፓንና ከሌሎች የዓለም አገራት ጭምር ቡና ገዢዎች ሻጮችን ለማግኘት ይመጣሉ፡፡ በጉባኤና ኤግዚቢሽኑ አጠቃላይ ከ100 ያላነሱ ጎብኚዎች የሚገኙ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያም ከ50 እስከ 60 የሚደርሱ ጎብኚዎች ተሳታፊ ይሆኑበታል፡፡ በተለይም ገዢዎችን የሚፈልጉ ቡና አምራችና ላኪዎች የኢትዮጵያ ቡናን በማስተዋወቅ ተሳታፊ ይሆኑበታል፡፡

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ዑመር በበኩላቸው እንዳሉት፤ ጉባኤና ኤግዚቢሽኑ የተለያዩ ፋይዳዎች ይኖሩታል፡፡ ጉባኤው እስፔሻሊቲ ኮፊ ኣት ኦሪጅን / “Specialty Cof­fee at Origin”/ በሚል መሪ ሃሳብ ይካሄዳል፡፡

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በዋናነት ሶስት ተልዕኮዎችን ይዞ እንደሚንቀሳቀስ አቶ ሻፊ ጠቅሰው፣ የቡና ምርትና ምርታማትን ማሳደግና ጥራትን ማስጠበቅ፣ ግብይቱን ማዘመንና የግብይቱ ተዋናዮችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ላይ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ እነዚህን በማቀናጀትና አርሶ አደሩን ተጠቃሚ በማድረግ አገሪቷ ከዘርፉ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ ማሳደግ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያን ቡና በተሻለ ጥራት አምርቶ ከፍ ባለ ዋጋ ለገበያ ማቅረብ እንዲቻል ጠቅሰው፣ ለዚህም ቡናውን ማስተዋወቅና ግብይቱን ማዘመን እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ በተለይም ግብይቱን በማዘመን ዓለም አቀፍ ለሆኑ ገዢዎች የኢትዮጵያን ቡና በተሻለ ዋጋ በመሸጥ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ተሠርተዋል ነው ያሉት፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ ቀደም ሲል በተለያዩ የዓለም አገራት በተለያዩ ኮንፍረንሶችና ኤግዚቢሽኖች ላይ በመሳተፍ እንዲሁም ኮንትራት በመፈራረም የኢትዮጵያን ቡና ከማስተዋወቅ ባለፈ በከፍተኛ ዋጋ እንዲሸጥ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ኮንፍረንሶችና ኤግዚቢሽኖች ወደ አገሪቱ እንዲመጡ በማድረግ የኢትዮጵያን ቡና ለማስተዋወቅ ዝግጅት ተደርጓል፡፡

ጉባኤና ኤግዚቢሽኑ በቡና መገኛ በሆነችው አገር ኢትዮጵያ መካሄዱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ነው አቶ ሻፊም ያመለከቱት፡፡ በኤግዚቢሽኑ ላይ የተለያዩ ገዢዎች እንደሚገኙ ጠቅሰው፣ በዚህም ላይ የኢትዮጵያ ቡና ምን እንደሚመስል በሚገባ ማስተዋወቅ ይቻላል ብለዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ መድረኩ ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች አሉት፡፡ ከቡናው በተጨማሪም ጎብኚዎች ኢትዮጵያን በብዙ መልኩ የሚረዱበትና የቱሪስት ስበትን ማሳደግ የሚቻልበት አጋጣሚን ይፈጥራል፡፡ ግብይቶችንም ማካሄድ የሚቻልበትም ነው፡፡

ጉባኤና ኤግዚቢሽኑ የአፍሪካን ምርት በአፍሪካ እንዲሁም የአፍሪካን ምርት ወደ ዓለም አገራት መላክን ያጠናክራል ተብሏል፤ በተለይም ኢትዮጵያ ከፍተኛ መጠን ያለው የቡና ምርት የምትልክ በአፍሪካ ቀዳሚ አገር እንደመሆኗ በጉባኤና ኤግዚቢሽኑ ኢትዮጵያ ላይ መደረጉ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ ይህን ዕድል በሚገባ በመጠቀም ጥራትና ጥሩ ጣዕም ያለውን የኢትዮጵያ ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ የተሻለ ገቢ ለማግኘት የመደራደር አቅምን ማጎልበት የሚቻልበት አጋጣሚ ነው፡፡

በጉባኤና ኤግዚቢሽኑ በቡና መገኛ አገር ኢትዮጵያ ውስጥ መካሄዱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ያመላከቱት አቶ ሻፊ፤ የኢትዮጵያ ቡናን ከፍ ባለ ዋጋ መሸጥ የሚቻልበት ዕድል እንደሚፈጥርም ተናግረዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ በጉባኤና ኤግዚቢሽኑ መሳካትም ሰፊ ሥራ እየተሠራ ሲሆን፤ በተለይም በኢትዮጵያ አሁን በቡና ልማቱም ሆነ በግብይቱ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየሰሩ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያና ውስጥ ተገንብተው ወደ ስራ የገቡ ሜጋ ፕሮጀክቶችም የጎብኚዎችን ቀልብ ለመሳብ ፋይዳቸው ከፍተኛ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የቡና መገኛ አገር ከመሆኗ ባለፈ የተለያየ አይነት የቡና ጣዕም ያላት አገር ናት፡፡ የአገሪቱ መሬትና የአየር ሁኔታ ለቡና ምቹና ተስማሚ ነው፡፡ ይህም ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያየ ጣዕም ያላቸው ቡናዎች እንዲኖሩ አስችሏል፡፡ ለአብነትም የሊሙ፣ የጅማ፣ የሲዳማ፣ የጉጂና ሌሎችም የራሳቸው የሆነ ልዩ ጣዕም ያላቸው ቡናዎች ናቸው፡፡ ጎብኚዎችም እነዚህን የተለያየ ጣዕም ያላቸውን የቡና አይነቶች በሚገባ እንዲያውቁና እንዲረዱ በጉባኤና ኤግዚቢሽኑ ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡

በኢትዮጵያ ያለው የቡና አመራረት ዘይቤ ከሌላው ዓለም የተለየ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሻፊ፤ የተፈጥሮ ጣዕም ያለው የጫካ፣ የጋርደንና ከፊል ጫካ የሚባሉ የአመራረት ዘይቤዎች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡ ይህንንም አመራረት ተሳታፊዎች ጎብኝተውና ተመልክተው የኢትዮጵያ ቡና ከሌሎች አገራት የቡና አመራረት የሚለይበትን ምክንያት አንድ ሁለት ብለው በመለየት መረዳት ይችላሉ ሲሉ አብራርተዋል፡፡ በዚህ ጊዜ የኢትዮጵያ ቡና ጥራት፣ የተለያየ ጣዕም ያለውና በተለያየ አግሮ ኢኮሎጂ እንደሚመረት በማመልከት፣ ይህን ልዩ የሆነውን የኢትዮጵያ ቡና በተሻለ ዋጋ የመግዛት ፍላጎት በደንበኞች ዘንድ እንዲኖር ማድረግ እንደሚቻል አስታውቀዋል፡፡

የውጭ ገዢዎች ከላኪዎች ጋር በመነጋገርና ኮንትራት በመፈራረም የኢትዮጵያ ባለ ልዩ ጣዕም ቡና በተሻለ ዋጋ መሸጥ እንዲችል መድረኩ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ቡናው በተሻለ ዋጋ መሸጥ ሲችል አገሪቷ የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ትችላለች ብለዋል። እንዲህ አይነት ሰፊና ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችንና ኤግዚቢሽኖችን ማካሄድ እጅግ ወሳኝና አገሪቷን የሚጠቅምና የሚያስተዋውቅ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ገበያ ውስጥ ዘልቆ ለመግባትና ለመቆየት የሚያስችሉትን ሁለት ስትራቴጂ ነድፎ እየሠራ ይገኛል። አንደኛው ነባር ገበያ ውስጥ መቆየት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ አዳዲስ ገበያ ውስጥ መግባት ነው፡፡ አዳዲስ ገበያ ውስጥ ዘልቆ ለመግባትም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ አንዱና ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህም ቡናን መጎንደልና ቡናን በክላስተር የማምረት ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎንም የገበያ መዳረሻዎችን ማስፋት የግድ ይሆናል፡፡

የገበያ መዳረሻን ማስፋት ሲባልም አዳዲስ ገበያ ውስጥ መግባት ነው ያሉት አቶ ሻፊ፣ የውጭ ገበያው እንዳለ ሆኖ በአፍሪካ ገበያ ውስጥ መግባት እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡ ለዚህም ‹‹የአፍሪካ የቡና ሳምንት›› አንዱ መንገድ መሆኑን ጠቅሰው፣ ጥቂት የማይባሉ የአፍሪካ አገራት በተለይም ተቆልቶ የተፈጨ ቡና ከአውሮፓና አሜሪካ እንደሚያስገቡ ጠቅሰዋል፡፡ ይህንኑ ገበያ ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት በጉባኤና ኤግዚቢሽኑ ጥሩ ዕድል እንደሚፈጥርም አስረድተዋል፡፡

አብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት ቡና የለመዱ ባይሆኑም ቡና እንዲለምዱ ለማድረግም ጠቃሚ ነው ያሉት አቶ ሻፊ፤ ከአውሮፓ የሚያመጡትን ቡና ኢትዮጵያ ውስጥ የተመረተና ፕሮሰስ የተደረገውን ቡና እንዲገዙ ለማድረግ የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡

በጉባኤና ኤግዚቢሽኑ ላይ ዓለም አቀፍ የቡና ገዥዎች፣ ምሁራንና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የሚሳተፉ ሲሆን፤ ሁለት ሺ የሚጠጉ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ የቡና ቆይዎች፣ ነጋዴዎች፣ አምራቾች፣ ገዥዎች እና የዘርፉ ባለሙያዎች ጭምር በአንድ ጣሪያ ስር ተሰባስበው ዘላቂነት ባለው የፋይናንስ አቅርቦትና ፖሊሲዎች ላይ ውይይት እንደሚያካሂዱም ይጠበቃል።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን  መስከረም 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You