
አዲስ አበባ፡- የትናንት አባቶች የኖሩበትን ኢትዮጵያዊ የአብሮነትና አንድነት ዕሴት ለትውልድ ማስተላለፍ ያስፈልጋል ሲሉ በኦሮሚያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበረሰብ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አብዱላኪም ሙሉ ገለጹ፡፡
አብሮነታችን ጌጣችን ነው በሚል መሪ ሃሳብ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ በኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አዘጋጅነት በኦሮሞ ባህል ማዕከል የውይይት መድረክ ተካሂዷል፡፡
በክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበረሰብ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አብዱልሀኪም ሙሉ እንደገለጹት፤ የትናንት አባቶች የኖሩበትን ኢትዮጵያዊ የአብሮነትና አንድነት ዕሴት ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየ ተግባር በመሆኑ ለቀጣዩ ትውልድ ማስቀጠል ያስፈልጋል፡፡
እንደ አቶ አብዱላኪም ገለጻ፤ የኦሮሞ ህዝብ አብሮ የመኖር ሌላውን የማቀፍ የማክበርና አብሮ የመስራት ባህል ያለው ህዝብ ነው፡፡
ኢትዮጵያዊ አብሮነትና አንድነት በታሪክ ውስጥ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገርና ሲገነባ የቆየ እሴት ነው ያሉት አቶ አብዱላኪም፤ እንደ ኢትዮጵያዊ አንድ በመሆን በአንድነትና በእኩልነት የሚኖርባት ሀገርን መፍጠር አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
ቀደምት ኢትዮጵያዊያን በሀዘንና በደስታ ጊዜ አብሮ በመኖር ከፍተኛ ማህበራዊ ትስስር ያላቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ ልዩነቶች ቢኖሩም እንኳን በደም የተጋመዱ፣ በጉርብትና አብረው የኖሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
እውነተኛ አብሮነትና አንድነት መምጣት የሚችለው በእኩልነት፣ በወንድማማችነትና በመደመር መሆኑን የገለጹት አስተባባሪው፤ እንደ ሀገር ያለውን እውቀት፣ማንነትና ባህል በማስተባበር መኖር የሚቻልባትን ሀገር መገንባት ይኖርብናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ በሚታዩት የእምነት፣ ቋንቋና የፖለቲካ አመለካከት ልዩነቶች ጸጋና ውበት መሆናቸውን ጠቅሰው፤ አንዱ የሌላውን ችግር መረዳት አብሮነትን ያጠነክራል ብለዋል፡፡
ጥላቻና መናናቅ መራራቅንና መለያየትን ከመፍጠር ውጪ አብሮነትንና አንድነት መፍጠር እንደማይችሉ በመግለጽ፤ ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመፍታት አብሮነትና አንድነት ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የክልሉ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ሁሴን ፈይሶ በበኩላቸው፤ የአብሮነት ቀን ሲከበር ኢትዮጵያ የተገነባችው በአብሮነት እሴት መሆኑን በማሰብ ጭምር ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝቦች ሀዘንም መከራም በጋራ በመኖርና በመቻቻል ዛሬ ላይ ደርሰዋል ያሉት አቶ ሁሴን፤ የኦሮሞ ህዝብም ከሌሎች ህዝቦች ጋር በመሆን በሀገራዊ ግንባታው ላይ የራሱን ድርሻ ተወጥቷል ብለዋል፡፡
እንደ ሀገር በሁሉም ዘርፍ አንድ መሆን ከተቻለ ጠንካራ ሀገር መገንባት እንደሚቻል ጠቅሰው፤የአብሮነት ቀን ሀገራዊ አንድነትንና አብሮነትን ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመርሀ ግብሩ ላይ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶና አባ ገዳዎችን ጨምሮ የብሔር ብሔረሰብ ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን መስከረም 5 ቀን 2016 ዓ.ም